ኮሮናቫይረስ፡ ሳይታወቅ ለዓመታት በሌሊት ወፎች ውስጥ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰው ልጆች ላይ ጉዳት እያስከተለ ያለው ኮሮናቫይረስ ለበርካታ ዓመታት ሳይታወቅ በሌሊት ወፎች ሰውነት ውስጥ እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ።
ኮቪድ-19ን የሚያስከትለው ቫይረስ በሌሊት ወፎች ላይ ከታየ ከ40 እስከ 70 ዓመታት አልፈዋል።
ወደ ሰው ልጆች ከተሻረገ ጥቂት ጊዜው መሆኑን ሳይንቲስቶች ይናገራሉ። መረጃው፤ ኮቪድ-19 በሰው የተሠራና ከቤተ ሙከራ አምልጦ የወጣ ነው የሚለው የሴራ ትንተና ላይ እውነትን የተመረኮዘ ስለመሆኑ ጥያቄ ያጭራል።
ፕ/ር ዴቪድ ሮበርትሰን በግላስጎው ዩኒቨርስቲ ነው የሚሠሩት። የሳቸው ጥናት ‘ኔቸር ማይክሮባዮሎጂ’ በተባለ መጽሔት ላይ ታትሟል።
ፕ/ር ዴቪድ እንደሚናገሩት፤ ሳርስ-ኮቭ-2 ከሌሊት ወፎች ቫይረስ ጋር የዘረ መል ተመሳሳይነት ቢኖረውም፤ አንዳቸው ከሌላቸው የበርካታ ዓሠርታት ልዩነት አላቸው።
“እነዚህ ሰውን ሊይዙ የሚችሉ ቫይረሶች ዘለግ ላለ ጊዜ እንደኖሩ ጥናቱ ያሳያል” ይላሉ።
ቫይረሱ መቼ እና እንዴት ወደ ሰው ልጆች እንደተሸጋገረ መታወቅ እንዳለበት ተመራማሪው ያስረዳሉ።
“በሌሊት ወፎች ላይ ቫይረሱ እንዳለ ካወቅን ለመቆጣጠር መሞከር አለብን።”
ለወደፊቱ ወረርሽኞች እንዳይቀሰቀሱ፤ ሰዎች የሚገጥሟቸው ህመሞች የቅርብ ክትትል እንደሚያሻቸው ጥናቱ ያሳያል። ከዱር የሌሊት ወፎች ላይ ናሙና ተወስዶ ምርመራ መካሄድም አለበት።
ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፤ “እነዚህ ቫይረሶች ዓመታት አስቆጥረዋል ማለት ሰዎችን ጨምሮ ሌላም መኖሪያቸው የሚያደርጉት አካል አግኝተዋል ማለት ነው።”
በጥናቱ፤ የሳርስ-ኮቭ-2 ዘረ መል ተቀራራቢው ከሆኑ የሌሊት ወፍ ላይ ያሉ ቫይረሶች ማለትም አርኤቲጂ13 እንዲሁም ከሌሎች ጋር ንጽጽር ተደርጓል።
ሁለቱ አይነቶች በምን ወቅት ላይ ተመሳሳይ የዘር ግንድ እንደነበራቸውም ተጠንቷል። በዚህ መሠረትም ሁሉቱ ዓይነቶች ከአስርታት በፊት በተለያየ የእድገት ሁኔታ ማለፋቸው ተደርሶበታል።
በሪዲንግ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ፕ/ር ማርክ ፓጌል በጥናቱ ባይሳተፉም፤ ሰዎችን ሊጎዱ የሚችሉ ኮሮናቫይረሶች ሳይታወቁ በሌሊት ወፎች ላይ ከ40 እስከ 70 ዓመታት መኖራቸውን ምርምሩ እንደሚያሳይ ይስማማሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ከእንስሳት ወደ ሰዎች የሚተላለፉ በሽታዎች ምን ያህል አደገኛ እንደሆኑ ጥናቱ ያሳያል። እንስሳት ውስጥ በጥገኝነት የሚኖሩና ለሰው ልጅ ጎጂ የሆኑ፤ እስካሁን ድረስ ግን ያልታወቁ ሌሎች ቫይረሶችም ሊኖሩ ይችላሉ።”
ቫይረሶቹ ወደ ሌሎች የዱር እንስሳት ተላልፈው ሊሆን ይችላል። በተለይም በሕገ ወጥ የእንስሳት ዝውውር ሳቢያ እርስ በእርስ የተቀራረቡ እንስሳት የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።
እስካሁን ድረስ ያለው መረጃ እንደሚያሳየው ግን የቫይረስ ዋነኛ ተሸካሚ የሆኑት የሌሊት ወፎች ናቸው።
ከዚህ ቀደም የሰሠሩ ጥናቶች ፓንጎሎኖች ለሳርስ-ኮቭ-2 ዝግመተ ለውጥ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ያሳያል። አሁን ግን ይህ ትክክል እንዳልሆነ ተደርሶበታል።
ቻይናን መዳረሻው ባደረገ ሕገ ወጥ የዱር እንስሳት ንግድ ወቅት ፓንጎሊኖች ከሌሎች እንስሳት ጋር ንክኪ ነበራቸው። ስለዚህም ፓንጎሊኖች ለቫይረሱ የተጋለጡት በቅርቡ ነው።


















