ጭምብል የማይለብሱ የአሜሪካ የሕግ መምሪያው ምክር ቤት አባላት ይባረራሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ የሕግ መምሪያው ምክር ቤት እንደራሴዎች ጭምብል እንዲለብሱ ታዘዙ፡፡
እንደራሴዎቹ ብቻም ሳይሆን ሁሉም የምክር ቤቱ ሠራተኞችም ይህንኑ ደንብ ካልተከተሉ ሊባረሩ እንደሚችሉ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ናንሲ ፒሎሲ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
በአሜሪካ ጭምብል የመልበሱ ነገር ብዙ ሲያጨቃጭቅ ነው የሰነበተው፡፡ ግማሾች አለመልበስ መብታችን ነው ይላሉ፡፡ ትራምፕም ቢሆን ጭምብል ማጥለቅ ይቀፋቸዋል፡፡ እምብዛምም ይህን ሲያበረታቱ አይታዩም፡፡
አሁን በዚያ አገር በኮቪድ-19 ምክንያት የሟቾች ቁጥር 150ሺህ ማለፉን ተከትሎ ጠበቅ ያሉ መመሪያዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡ መመሪያዎቹ ከሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላት የጀመሩ ይመስላል፡፡
አፈ ጉባኤ ናንሲ ፒሎሲ ጭምብል የማይለብሱ እንደራሴዎችን ጭምር ከምክር ቤት ለማስወጣት የዛቱት የተከበሩ የምክር ቤቱ አባል ሪፐብሊካኑ ሉዊ ጎህመርት ትናንትና በኮሮና መያዛቸውን ተከትሎ ነው፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሉዊ ጎህመርት የቴክሳስ ተወካይ ሲሆኑ በካፒቶሎ ሂል (የሁለቱ ምክር ቤቶች መቀመጫ ግቢ) ያለ ጭምብል ሽር ጉድ ሲሉ ነበር ተብሏል፡፡
እንዲያውም ከትናንት በስቲያ የፌዴራል አቃቢ ሕግ ዊሊያም ባር በምክር ቤት ለብርቱ ጥያቄ በቀረቡበት ወቅት እርሳቸው ያለ ጭምብል ነበር ቁጭ ያሉት፡፡
የተከበሩ ሉዊ ጎህመርት ጭምብል አላጠልቅም፣ መብቴ ነው ሲሉ ያስቸግሩም ነበር፡፡ ትናንት ማምሻውን ‹‹ወገኖቼ፣ በዉሃን ቫይረስ ሳልያዝ አልቀረሁም› ሲሉ በቪዲዮ በቫይረሱ መለከፋቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ከርሳቸው ጋር ወዲያ ወዲህ ሲሉ የነበሩ ሰዎች በሙሉ ወሸባ ይገባሉ ተብሏል፡፡
የፌዴራል አቃቢ ሕግ ዊሊያም ባር ከተከበሩ ሉዊ ጎህመርት ጋር በቅርብ ተነካክተው ይሆናል በሚል አስቸኳይ ምርመራ እንዲያደርጉ ተብሏል፡፡
የተከበሩ ሊዊ ጉህመርት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ወደ ቴክሳስ ለመጓዝ ቀጠሮ ነበራቸው፡፡
ምርመራ ማድረጋቸው በጀ እንጂ ከትራምፕ ጋር በአንድ አውሮፕላን እንደ እቅዳቸው ተሳፍረው ቢሆን ኖሮ ትራምፕም ጭምብል ማጥለቅ ስለማይወዱ ፕሬዝዳንቱ በተህዋሲው ሊለከፉ ይችሉ ነበር ተብሏል፡፡
የካሊፎርኒያ ተወካይ አፈጉባኤ ወ/ሮ ናንሲ ፒሎሲ እንደተናገሩት እንደራሴዎች ተራቸው ደርሶ ንግግር ለማድረግ ሲፈልጉ ብቻ ጭምብላቸውን ዝቅ ማድረግ ይችላሉ፡፡
ከዚያ ሌላ ያለ ጭምብል የታየ ሰው አባራለሁ ብለዋል፡፡
እስከዛሬ 10 የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት በኮቪድ ተህዋሲ ተይዘዋል፡፡ ከነዚህ መሀል ሦስቱ ዲሞክራቶች ሰባቱ ሪፐብሊካን ናቸው፡፡













