ጆን ፖምቤ ማጉፉሊ፡ ኮሮናቫይረስንና ኢምፔሪያሊዝምን 'እንደመስሳለን' የሚሉት አወዛጋቢው ጆን ማጉፉሊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ማን ይመስላቸዋል ከተባለ የብራዚሉ ጃይ ቦልሶናሮ፣ ወይም የፊሊፒንሱ ዲቶርቴ ወይም በትንሽ በትንሹ የአሜሪካው ትራምፕ?
ሁሉንም የሚያመሳስላቸው አወዛጋቢ መሪዎች መሆናቸው ነው። እንደመጣላቸው ይናገራሉ? ለጋዜጠኛ ይመቻሉ፤ የዜና ርዕስ ይሆናሉ፣ ተቺዎቻቸውን ከፍ ዝቅ አድርገው ይሳደባሉ።
ጆን ማጉፉሊ ኢምፔሪያሊስቶችን መስደብ ቁርስ፣ ምሳ እራታቸው ነበር።
ኮሮናቫይረስ ከመጣ ወዲህ ደግሞ ሰውየው በዓለም ሚዲያ ጭምር ትኩረት አግኝተዋል። የሚናገሩት ከሳይንስ ጋር ይጣረሳል።
"ኮሮናቫይረስ የሚባልን ነገር ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በጸሎት ድምጥማጡን አጥፍተነዋል" ብለው ነበር።
ማጉፉሊ ምንም ቢሉ ሕዝባቸው መገረም የተወ ይመስላል ነበር።
ራሳቸውን ብርቱ አፍሪካዊ ብሔርተኛ፣ ታንዛኒያዊ አርበኛና ጥብቅ የካቶሊክ አማኝ አድርገው ነበር የሚያስቀምጡት።
የውጭ ኃይሎችን እከሌ ከእከሌ ሳይለዩ የምሥራቅ አፍሪካ በዝባዦች ይሏቸዋል።
"ታላቁ የታንዛኒያ ሕዝብ ሆይ! እንድትረዳልኝ የምፈልገው ታላቅ ፕሬዝዳንት፣ የማይናወጽ ፕሬዝዳንት ባለቤት እንደሆንክ ነው። እኔ መሪህ ማንንም አልፈራም፤ ለማንም አልንበረከክም" ብለው ነበር በመጋቢት 2018 (እ.ኤ.አ)።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነጮችን በጥርጣሬ ማየት
በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በመላው ታንዛኒያ በተካሄደው ምርጫ እንደተጠበቀው ማጉፉሊ ተመርጠው መንበራቸው ለቀጣይ 5 ዓመታት ተደላድሎ ነበር።
በርካታ ታንዛኒያዊያን መሪያቸው የአገራቸውን ጥቅም እያስከበሩላቸው የሚገኙ አርበኛ አድርገው ነበር የሚመለከቷቸው።
ለምሳሌ የማጉፉሊ አንዱ ፈተና ሆኖ የቆየው "ባሪክ ጎልድ ኮርፖሬሽን" የተሰኘ የካናዳ የማዕድን ድርጅት ነበር።
ማጉፉሊ ድንገት ተነሱና የዚህ ማዕድን ቆፋሪ ድርጅት ከሦስት የወርቅ ማዕድን ቁፋሮዎች የሚያገኘው 70 ከመቶ ድርሻ ለታንዛኒያ መንግሥት ገቢ ካላደረገ "ተጭበርብረናል" አሉ።
የኩባንያውን ኃላፊዎች "ያን ካላደረጋችሁ ታንዛኒያን እየበዘበዛችኋት እንደሆነ ነው የምቆጥረው" አሉ።
ኩባንያው መጀመሪያ "እንዴት ተደርጎ፣ ሞቼ ነው ኖሬ!" አለ። በኋላ ግን ተለሳለሰ።
ዘለግ ያለ ጊዜን ከወሰደ ድርድር በኋላ ድርጅቱና ማጉፉሊ ከስምምነት ደረሱ። መንግሥትም ከኮርፖሬሽኑ ድርሻ 16 ከመቶ ለመውሰድ ተስማማ።
ማጉፉሊ ድርድሩ በአንዲት ላምና በአንዲት ጥንቸል መካከል የተደረገ ነበር ሲሉ ተናገሩ።
በእርግጥም የድርድሩ ውጤት ከዚህ በኋላ የውጭ ድርጅቶች ታንዛንያን በኢንቨስትመንት ስም መበዝበዝ እንደማይችሉ ጥቆማ የሰጠ ነበር።
ማጉፉሊ ድርድሩ እስኪሰምር ድረስ የዚህን ድርጅት ምርቶች ወደ ውጭ እንዳይላኩ አግደው ቆይተው ነበር።
የባሪክ ወርቅ ማዕድን ሥራ አስኪያጅ ማርክ ብሪስቶ ስምምነቱን ሲፈረሙ የማጉፉሊን እጅ ከጨበጡ በኋላ እንደተናገሩት "አሁን የተፈራረምነው ነገር የማዕድን ኢንዱስትሪውን ወደፊት የሚፈትን ነው" ማለታቸው ይነገራል።
ማጉፉሊ በተራቸው ተነስተው ምላሽ ሰጡ፤ "ለዚህ ስምምነት መሳካት ታላቁን አምላኬን አመሰግነዋለሁ።"
ማጉፉሊ ከዚህ የማዕድን ኩባንያ ጋር ብቻ አይደለም ጠብ ውስጥ ገብተው የነበረው።
ከቻይና ጋር በተመሳሳይ ሁለት ስምምነቶችን ሰርዘዋል።
አንዱ የታንዛኒያ የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ባቡር መስመር ነው። ይህ መስመር የንግድ መናኸሪያዋን ዳሬሰላምን ከዋና ከተማዋ ዶዶማ የሚያገናኝ 500 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ነበር።
ሁለተኛው በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ ወደብ የባጋሞዮ ግንባታ ሲሆን ይህ ቦታ በአንድ ወቅት የጀርመን የምሥራቅ አፍሪካ ቅኝ የነበረው ግዛት ዋና መናኸሪያ ነበር። ይህ ፕሮጀክት 10 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ ስምምነት የተደረገበት ነበር።
ማጉፉሊ ከእርሳቸው ቀድመው ፕሬዝዳንት የነበሩት ጃካያ ኪክዌቴ ይህ ከቻይና ጋር ፈርመውት የነበረውን የወደብ ግንባታ ስምምነት "እብደት" ብለውታል።
"እንዲህ ዓይነት ስምምነት የሚቀበለው እብድ ሰው ብቻ ነው" በማለት።
ያን ስምምነት የፈረመውን አስተዳደር "ስግብግቦች" እንዲሁም "ታንዛኒያን ማስቀደም ያልቻሉና አገሪቱን ያሽመደመዱ" ሲሉ ነበር የጠሯቸው።
ማጉፉሊ ዋንኛ የታንዛኒያ ጠላት አድርገው የሚያስቀምጡት ምዕራባዊያንን ነው።
ቀጥለው ደግሞ ለምዕራባዊያን የሚያጎበደዱ "አሻንጉሊቶች" የሚሏቸውን የአገራቸውን ሰዎች ነው። ቀጥለው መርማሪ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎችና ተቃዋሚዎቻቸውንም አይወዷቸውም። የነጭ አሽከር ይሏቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የተግባር ሰው?
ታንዛኒያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ታቢት ጃኮብ ለቢቢሲ እንደተናገረው ማጉፉሊ ሥልጣኑን ሁሉ በእጃቸው አስገብተውም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ የምዕራባዊያን ነገር ያባንናቸዋል። ብሔርተኝነታቸው መስመሩን ይስትና የሕዝበኝነት መስመርን ይይዛል።
ተቃዋሚዎችን ማስጨነቅ፤ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማጥበብ፣ ጋዜጠኞችን መከታተልና በደኅንነት ቅኝት ውስጥ እንዲቆዩ ማድረግ ማጉፉሊ የሚያሳዩት ባህሪ ነው። የሚመነጨውም ከፍርሃት ነው ይላሉ።
ታንዛኒያዊው ጸሐፊ ኤልሲ ኢያኩዜ እንደሚለው ደግሞ ማጉፉሊ የሚመሩት በአንዳች እርሳቸው በሚያምኑት ርዕዮተ ዓለም የተቀኘ ቢሆንም ፍጹም የተግባር ሰው ናቸው።
"ሰውየው ውይይት አይፈልግም ተግባር እንጂ" ይላል ኢያኩዜ።
ወደ አውሮፓ የማይጓዘው ርዕሰ ብሔር
በስዋሂሊ "በቡሩ" ማለት ወንድ ፍየል ማለት ነው። ይህን ቃል ዝነኛ ያደረጉት ማጉፉሊ ናቸው። ቃሉን የሚጠቀሙበት የምዕራቡን የኢምፔሪያሊስት ኃይል ለመጥራት ነው። "ወንድ ፍየሎች" እያሉ።
ማጉፉሊ ወደ ሥልጣን ከመጡ አንድም ጊዜ ወደ ምዕራብ ዓለም ተጉዘው አያውቁም። አንድም ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ስብሰባ ታድመው አያውቁም። ይህ የሚገርም ነገር ነው።
ሆኖም የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ላይ ይገኛሉ። ጥቂት የአፍሪካ አገራትንም ጎብኝተው ያውቃሉ። ከእነዚህ መካከል ኡጋንዳና ሩዋንዳ ይገኙበታል። ሁለቱም አገራት እንደ ማጉፉሊ ሁሉ የምዕራቡን ዓለም የሚመለቱት በጥርጣሬ ነው።
ማጉፉሊ በአካባቢው አገራት ስብሰባም አይገኙም። ከዛምቢያና ከኬንያ ጋር በኮሮናቫይረስ ምክንያት ድንበር ለምን ይዘጋል ሲሉ ተቃቅረው ነበር።
ከኡጋንዳው ዩዌሪ ሙሴቬኒም ጋር እንዲሁ።
አዛውንቱ ሙሴቬኒ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በኮሮናቫይረስ ላይ በአንድነት መሥራት እንዳለባቸው ሲገልጹ "እኛ የምሥራቅ አፍሪካ አገር ሕዝቦች ከአንድ እናትና አባት የተወለድን ቤተሰብ" እንደማለት ነን ብለው ነበር። ስለዚህ ልክ እንደ ቤተሰብ እርስበርስ ትብብር ያሻናል ማለታቸው ነው።
ማጉፉሊ ግን ይህን የሙሴቬኒን ሐሳብ በትወልድ አካባቢያቸው አንድ ቤተክርስቲያ ውስጥ ባደረጉት ንግግር ውደቅ አድርገውታል። "ትብብር ዕድገት ለማምጣት እንጂ በሽታው ለማስወገድ አይሆንም። በሽታ የማስወገድ ነገር የግል ጉዳይ ነው" ብለው ነበር።
ኡጋንዳም ሆነች ሩዋንዳ ቫይረሱን ለመቆጣጠር የእንቅስቃሴ ገደብ አበጅተዋል። ከቤት አትውጡ ብለዋል፤ ይነስም ይብዛ። ማጉፉሊ በበኩላቸው "ከቤት ውጡ" ነበር የሚሉት።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ማጉፉሊ እየተገለሉ ነበር?
የማጉፉሊ ተቃዋሚዎች ታንዛኒያ የተጨናነቁ ከተሞች የእቅስቃሴ ገደብ ልታደርግባቸው ይገባ ነበር ብለው ይተቿቸዋል። ነገር ግን ማጉፉሊ የእንቅስቃሴ ገደብ ያላደረጉ ብቸኛው መሪ ተደርገው ነው የሚሳሉት።
የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) ባወጣው አንድ ጥናት ግን እንደ ታንዛኒያ ሁሉ በርካታ አገራት የቤት ውስጥ መቀመጥን ግዳጅ አላደረጉም። እንዲያውም ከአፍሪካ አገራት ሲሶዎቹ ይህን አላደረጉም።
እርግጥ ነው ኮሮናቫይረስ ባለፈው ዓመት ኅዳር አጋማሽ ላይ ሲከሰት ታንዛኒያ ትምሀርት ቤቶችን ዘግታ ነበር። ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችንም አግዳ ነበር። እንዲያውም ማንም ሳይጀምረው ገና በትኩሱ ነበር ማጉፉሊ ሰው አልጨብጥም ያሉት።
ከተቃዋሚው መሪ ማአሊም ሰይፍ ሻሪፍ ሀማድ ጋር የእግር መጨባበጥ አድርገው ይኸው ዜና ሆኖ ነበር፤ ያኔ።
ይህ የሆነው ብዙ ሰዎች ገና በእጅ መጨባበጥ ባላቆሙበት ጊዜ ነበር።
ያም ሆኖ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ማሺዲሶ ሞዎቲ ታንዛኒያ ቫይረሱን ለመከላከል ያሳየችውን ዳተኝነት ተችተዋል።
ማጉፉሊ ከሠሯቸው ስህተቶች ምናልባትም አንዱ የእምነት ቦታዎች እንዳይዘጉ ማድረጋቸው ሲሆን፤ በጸሎት ወቅትም ተገቢውን ማኅበራዊ ርቀት ለመጠበቅ መመሪያ አላስተላለፉም።
ማጉፉሊ ግን ግድ የላቸውም፤ እንዲያውም "ኮሮናቫይረስ ሰይጣን ነው። በክርስቶስ መንፈስ ላይ ሊጸና አይችልም" ብለው ነበር።
አንዲህ የሚሉት ማጉፉሊ በኬሚስትሪ የዶክትሬት ዲግሪ ነበራቸው። ዶ/ር ማጉፉሊ ይባሉ ነበር እኛ ጋ ቢሆን። ጥብቅ የካቶሊክ እምነት ተከታይም ናቸው።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ማጉፉሊ ለቤተክርስቲያን ምዕመናን ባደረጉት ንግግር "እንኳን ደስ ያላችሁ! ኮሮናቫይረስ ከአገራችን ጠፋላችሁ! ክብር ለጌታ!" ብለው ነበር።
ይህንን ካሉ ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ቫይረሱ አልጠፋም እጃችሁን በደንብ ታጠቡ ብለዋል።
ከዚያ በኋላ ደግሞ የአገሪቱ ፓርላማ ከመበቱኑ በፊት "አምላካችን አገራችን ታንዛኒያን ከቫይረሱ ታድጓታል። አሁንም ሁሉም ትምህርት ቤቶች ይከፈታሉ፤ ሕይወት እንደ ቀድሞው ይቀጥላል" አሉ።

የፎቶው ባለመብት, Tanzanian presidency
በሴራ ያምኑ ይሆን?
ማጋፉሊ ከዚያ በፊት ባደረጉት ሌላ ንግግር ኮሮናቫይረስ ምዕራባዊያን የሸረቡት ሴራ ነው ብለው ነበር።
ማጉፉሊ የምርመራ መሣሪዎች አስተማማኝነትም ላይ ጥያቄ አንስተው ያውቃሉ።
"ብዙውን ጊዜ ሁሉም ከውጭ የሚገባ ነገር ትክክል ነው ብላችሁ መውሰድ አይኖባቸሁም። ብዙ መጨበርበር አለ፤ ብዙ መታለል አለ፤ ይህ ጦርነት ነው፣ የሴራ ጦርነት" ብለው ነበር ለሕዝባቸው።
ማጉፉሊ ብረት ነው
ማጉፉሊ አገር በቀል የባሕል መድኃኒቶች ፈውስ ስለመሆናቸው ብዙ ብለዋል።
እንፋሎትን ጨምሮ ሌሎች ተክሎችም ይፈውሳሉ ሲሉ ተናግረዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ግን ይህን የሚያረጋግጥ ምንም መረጃ የለም ይላል።
"ማጉፉሊ አብዛኛዎቹን የአፍሪካ አገራትን አጋር አድርጎ ነው የሚያያቸው፤ ለኮሮናቫይረስ መድኃኒት ከተገኘም ከአፍሪካ አገራት ቢሆን ነው የሚመርጠው፤ ከምዕራብ የሚመጣን ነገር አያምንም" ይላሉ የታንዛኒያ የፖለቲካ ተንታኝ ዳን ፓጄት።
ነገር ግን የባህል መድኃኒትን በተመለከተ የብዙ አፍሪካዊያን የሕይወት ዘይቤ በመሆኑ በዚያ ላይ እምነት ማሳደራቸው የሚደንቅ አይደለም።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያትተው 80 ከመቶ አፍሪካዊ የባሕል መድኃኒት ይጠቀማል።
በ2015 እንደ አውሮፓዊያኑ የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሥልጣን ለማጉፉሊ ሲያስረክቡ እንዲህ አሉ፤ "እኔስ እየሄድኩ ነው፤ እኔን የሚተካኝ ግን "ቹማ" ነው" ቹማ በስዋሂሊ ቅጥቅጥ ብረት ማለት ነው።
ትክክለኛ አገላለጽ ይመስላል። ማጉፉሊ ለወዳጆቸው ብረት ሆነው ነው የሚታዩት፤ ለጠላቶቻቸው ግን ልምጭ።
ማጉፉሉ ለሳምንታት ከሕዝብ ዕይታ በተሰወሩበት ጊዜ ተቃዋሚዎቻቸው ጤና እንዳልሆኑ ሲናገሩ ቆይተዋል።
አንዳንዶችም ሲያጣጥሉት በነበረው የኮረናቫይረስ ተይዘው ኬንያና ሕንድ ለህክምና እንደተወሰዱ በእርግጠኝነት ሲናገሩ ጽህፈት ቤታቸው ግን ፕሬዝዳንቱ ሰላም እንደሆኑና ሥራቸውን እየከወኑ መሆናቸውን በመግለጽ ሲያስተባብሉ ነበር።
ነግ ግን መጨረሻ ላይ የተፈራው እውነት ሆኖ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት የማጉፉሊን ዜና ዕረፍት ረቡዕ ምሽት ለሕዝባቸው አረዱ።












