ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካ በዳሬሰላም በቫይረሱ የመያዝ እድል "ከፍተኛ" ነው አለች

ታንዛንያ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በታንዛንያ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ መንግሥት አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር መግለፁን ማቆሙን ተከትሎ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች "በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር" ይችላል ሲል አስጠነቀቀ።

በተጨማሪም በዳሬሰላም በኮሮናቫይረስ የመያዝ እድሉ " እጅግ በጣም ከፍተኛ" መሆኑን አስታውቋል።

የአሜሪካ ኤምባሲ በታንዛንያ የሚኖሩ አሜሪካውያንን በቤታቸው እንዲቆዩ እና አብረዋቸው ከሚኖሩ ውጪ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲቀንሱ መክሯል።

በዳሬሰላም የሚገኙ ሆስፒታሎች በሕሙማን መጨናነቃቸውን የገለፀው ኤምባሲው፣ የአገሪቱ ጤና ስርዓት አቅም ውስን በመሆኑ ሕሙማን ምናልባት አፋጣኝ ሕክምና ካለማግኘት የተነሳ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችልም ገልጿል።

ቢቢሲ ኤምባሲውን በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን መረጃ የጠየቀ ሲሆን ከታንዛንያ ጤና ሚኒስቴር መውሰዱን ገልጿል።

የታንዛንያ መንግሥት የአሜሪካ ኤምባሲ ላወጣው መግለጫ ያለውን አስተያየት ቢቢሲ ቢጠይቅም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ የጤናውን ቀውስ የአካባቢ ጤና ባለሥልጣናት እያጋነኑት መሆኑን ተናግረዋል።

በታንዛንያ ለመጨረሻ ጊዜ በቫይረሱ የተያዘ ሰው መገኘቱ የተገለፀው ከአስራ አምስት ቀን በፊት ሲሆን በወቅቱ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 509 ደርሶ ነበር።

ከእነዚህም መካከል 21 ሰዎች መሞታቸው በወቅቱ ተገልጿል።

የታንዛንያ ባለስልጣናት የወረርሽኙን መጠን ዝቅ አድርገው ቢያቀርቡትም፣ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ በምሽት የሚደረጉ ቀብሮች መታየታቸውን ተከትሎ አንዳንዶች መንግሥትን እንዲጠይቁ አስገድዷቸዋል።

ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ለኮሮናቫይረስ የሰጡት ምላሽ እጅግ አነስተኛ ነው በሚል፣ እንዲሁም ቤተ እምነቶች እንዳይዘጉ እንዲሁም ፀሎት ቫይረሱን "ያሸንፈዋል" ማለታቸው በበርካቶች ትችት አስከትሎባቸዋል።

ፕሬዝዳንቱ የማዳጋስካሩ ፕሬዝዳንት ኮቪድ-19 ሕሙማንን ይፈውሳል ሲሉ ያስተዋወቁትን ከእጽዋት የተቀመመ መድሃኒት ካዘዙ የአፍሪካ አገራት መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።

ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት ፍተሻ ያልተደረገበትን መድሃኒት እንዳይጠቀሙ አስጠንቅቋል።

ከዚህ ቀደም ግን የታንዛንያ መንግሥት የሚቀርቡበትን ትችቶችና ክሶች ሁሉ ሲያጣጥል መቆየቱ ይታወሳል።

ኮሮና
Banner