ከጎረቤት አገራት ጋር የሚዋሰኑ ክልሎችና የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያው ግለሰብ ከተገኘ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎች ቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እየተገኙ ነው።
በተለይ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በምትዋሰንባቸው አካባቢዎች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ደግሞ አሳሳቢ ሆኗል።
"ስጋቱ ይህ ነው ብሎ መግለጽ ይከብዳል" ያሉት የመተማ ወረዳ የጤና ጥበቃ ጽህፈት ኃላፊ አቶ በቃሉ እውነቱ ". . . በጣም ከባድ ነው። ቁጥሩ መጨመሩ አስፈሪ ነው። ከሱዳን በማሽላ አጨዳ እና በጥጥ ለቀማ ተሠማርተው ብዙዎች እየገቡ ነው። ከሚያዝያ 22 ጀምሮ 360 ሰዎችን ለይቶ ማቆያ አስገብተናል" ብለዋል።
እስካሁን ድረስ ከፌደራል እና ከክልል ምንም ድጋፍ ያለመኖሩን ጠቅሰው "የእነሱ ድጋፍ ካልተጨመረበት ከባድ ነው። በቀን 100 ወይም 200 የቀን ሠራተኛ ይገባል። . . . ። እስካሁን የመጣልን ነገር የለም" ብለዋል።
በተመሳሳይ ስጋት እንዳለባቸው የገለጹልን ደግሞ የባቲ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሞሃመድ አብዱ ናቸው።
"በጣም ስጋት አለን. . . " ያሉት አቶ ሞሃመድ ቀደመው ወደ ሥራ መግባታቸውንና አፋር እና አማራ ክልል ድንበር ላይ የሙቀት ልየታ በአግባቡ እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል። ለህብረተሰቡ መረጃ በመስጠት ከጅቡቲ የተመለሱ ሰዎችን እንዲጠቁም በማድረግ እየሠሩ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።
"የክልል እና የፌደራል መንግስት እገዛ የለም። ሰሞኑን ለሱፐርቪዥን (ለቁጥጥር) መጥተው ነግረናቸዋል። ቦታው ስትራቴጂክ ነው ምስራቅ አማራን ጠቅላላ የሚያገናኝ ዋና መንገድ ነው" ሲሉ ገልጸዋል አቶ ሞሃመድ።
እንደ አቶ ሞሃመድ ከሆነ ሌላው ስጋት ከጅቡቲ የሚመጡ ሰዎች መረጃ መደበቃቸው ነው። ይህ ደግሞ ሥራቸው ላይ እንቅፋት ሆኗል። ከጀቡቲ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በእግር በመሻገር ወደ ከተሞች የሚገቡ መኖራቸውን አቶ ሞሃመድ ጨምረው ያስረዳሉ።
"ከዚያ ወደ ከተማ መጥቶ ከሚሴ መኪና ተሳፍሮ ይመጣል። የጉዞ ታሪክ ሲጠየቅ ከሚሴ ወይም ከሎጊያ ምናምን ይላል። ከጅቡቲ ነው የመጣሁት ብሎ አይናገርም። ይሄን ማወቅ ስለማይቻል ጎጥ እና ቀበሌ ወይም ከተማቸው ሲገቡ ሰዎች ጥቆማ ይሰጣሉ። በዚያ ጥቆማ ማቆያ እያስገባን ነው።" አብዛኛዎቹ ሲመጡ የጉዞ ታሪክ ሲጠየቁ ከሚሴ ወይም ሎጊያ ይላሉ እንጂ ከጅቡቲ አይሉም በማለት ያለው ክፍተት የፈጠረውን ችግር ያስረዳሉ።
የሶማሌ ክልልም ከጎረቤት አገራት በሚመጡ ሰዎች ተመሳሳይ ስጋት መፈጠሩን የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዩሱፍ መሐመድ በተለይ ለቢቢሲ ገልጸዋል። "ከፍተኛ ስጋት አለ። እስካሁን ያስመዘገብናቸው 22 በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ከጎረቤት አገራት የመጡ ናቸው። ለይቶ ማቆያ ላይ ያገኘናቸው ናቸው።" ብለውናል።
ሌላው ስጋት ያንዣበበት የአፋር ክልል ነው። የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ያሲን ሃቢብ "ጥሩ አይደለም። ስጋቶች አሉ" ሲሉ ይናገራሉ። ከጅቡቲ የሚመለሱ ሰዎች አሁንም እንዳሉ ጠቅሰው "540 ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ" ሲሉ የስጋቱን ደረጃ ያስቀምጣሉ።
በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉትን ለ14 ቀናት ከማቆየት ሌላ በክልሉ ሥራ በጀመረው ቤተ ሙከራ ምርመራ አድርገው፣ ከቫይረሱ ነጻ የሆኑትን ወደ ቀያቸው እንደሚመልሱ ይናገራሉ። እስካሁንም 241 ናሙና ተወስዶ 238ቱ ነጻ መሆናቸው ሲረጋገጥ ቀሪዎቹ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
"ስጋቱን አውቆ የክልሉ መንግሥት ሁሉም ከፍተኛ አመራር በ34 ወረዳ እና 5 ከተማ አስተዳደሮች ላይ ተመድበው እየሠሩ ነው" ብለዋል።
ስለወረርሽኙ ትምህርት ከመስጠት ባለፈ በአፋር ህዝብ ዘንድ ያለው መረጃ የመለዋወጥ ባህልን ተጠቅመው "ህዝቡ በእግር የሚገቡትን ሰዎች በመለየት ትልቅ ድጋፍ እና ትብብር እያደረገ ነው። በዚሁ ከ21 በላይ ሰዎች ተጠቁመው ከእነዚያ መካከል አንዱ በቫይረሱ መያዙ ተረጋግጧል። ህዝብ በጣም ትልቅ አገልግሎት እየሰጠ ነው" ብለዋል።
በትግራይ ክልል ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተረጋገጠባቸው ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ አሸከርካሪዎች እና ረዳቶች መሆናቸው በዚህ ረገድ ምን እየተሠራ እንደሆነ ጠይቀን ነበር።
"በክልል ደረጃ ምርመራ ጀምረናል" ያሉን ዶ/ር የሱፍ "ሾፌሮች እና ረዳቶች ለብቻቸው ለይቶ ማቆያ እንዲዘጋጅላቸው የሚያርፉበት እና የሚመገቡበት ሆቴል ለብቻ ተለይቶ ጥንቃቄ እየተደረገ ዕቃ ማመላለሱንም እንዲያከናውኑ የተወሰነ ውሳኔ ስላለ እሱን ተግባራዊ እናደርጋለን" ብለዋል።
አቶ ያሲን በበኩላቸው የአሸከርካሪዎችን እና ረዳቶቻቸውን ሙቀት ከመለካት ባለፈ መኪኖቻቸውም መድኃኒት እንዲረጩ እየተደረገ መሆኑነን ገልፀዋል።
"ጋላፊ ላይ ሙቀት ልየታ አለን። ከ14 በላይ ሾፌሮች ማቆያ አስገብተናል። ሙቀታቸው ከፍ ያለባቸውን ሰዎች ለ14 ቀናት እንዲቀመጡ በማድረግ መርምረን ነጻ መሆናቸውን አረጋግጠን እንዲወጡ እናደርጋለን። ሙሉ ለሙሉ መንገዱን መዝጋት የአገሪቱ ጉሮሮ ስለሆነ አደገኛ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ዶ/ር የሱፍ እንዳሉት ከተለያዩ አካላት ድጋፍ እያገኙ ሲሆን፣ ያለውን ድጋፍ ለማስቀተል እና ክፍተቶችን ለመሙላት መነጋገራቸውን አስታውቀዋል። "ማን ምን መስራት አለበት በሚል እስካሁን ቴክኒካል እና የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር። ይህ ግን በቂ እንዳልሆነ እና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ካለው የድንበር አካባቢ እንቅስቃሴ እና የቦርደር ስፋት አኳያ ጎረቤት ሃገራት ቁጥሩ ከመጨመር አንጻር ትልቅ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተስማምተናል" ብለዋል።
ከፌደራል መንግሥት የባለሙያ እና ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የገለጹት አቶ ያሲን በበኩላቸው "በሁሉም ረገድ ድጋፎች አሉ። ግን በቂ ነው፤ አጥጋቢ ነው ሳይሆን ጊዜው አደገኛ ስለሆነ ያሉትን ድጋፎች በመያዝ እኛም ክልሉ በመደበው በጀት ያሉትን ግብአቶች ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው" ሲሉ ገልጸዋል።














