ኮሮናቫይረስ፡ ዉሃን ለ11 ሚሊዮን ነዋሪዎቿ በሙሉ የኮቪድ-19 ምርመራ ልታደርግ ነው

የዉሃን ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቻይናዋ ዉሃን ከተማ አስራ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ነዋሪዋን የኮሮናቫይረስ ምርመራ ልታደርግ ዕቅድ እያዘጋጀት መሆኑ ተነገረ።

ዕቅዱ ገና በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ያለ ቢሆንም በከተማዋ ያሉ ሁሉም አካባቢያዊ አስተዳደሮች በአስር ቀናት ውስጥ ምርመራውን አድርጎ ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ዝርዝር እንዲያቀርቡ ታዘዋል።

ይህ ሃሳብ የቀረበው የኮሮናቫይረስ መነሻ በሆነችው ዉሃን ከተማ ውስጥ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ስድስት ሰዎች ላይ ቫይረሱ ከተገኘባቸው በኋላ ነው። ከዚህ በፊት ለአንድ ወር ያህል አንድም በሽታው ያለበት አዲስ ሰው አልተገኘም ነበር።

ዉሃን በወረርሽኙ ምክንያት ለአስራ አንድ ሳምንታት ጥብቅ በሆነ የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ቆይታ በሚያዝያ ወር ሁለተኛ ሳምንት ላይ ነበር የተከፈተችው።

ለተወሰኑ ሳምንታትም ትምህርት ቤቶች ተከፍተው፣ የንግድ ተቋማት ሥራ ጀምረው እንዲሁም የሕዝብ መጓጓዣዎችም አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው ህይወት ወደ ነበረችበት መመለስ ጀምራ ነበር።

ነገር ግን ከቅርብ ቀናት ወዲህ በተወሰኑ የመኖሪያ አካባቢዎች በርከት ያሉ አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው ከተማዋ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴዋ ለመመለስ እያደረገችው የነበረውን ጥረት ስጋት ላይ ጥሎታል።

ዉሃን ሁሉንም የከተማዋን ነዋሪ ለመመርመር ባወጣችው ዕቅድ መሰረት ሁሉም የከተማዋ ከፍል በአስር ቀናት ውስጥ ምርመራው አድርጎ ለማጠናቀቅ የሚያስችለውን ዕቅድ እስከ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ እንዲያርቡ ታዝዘዋል።

ምርመራ ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ የሚተነትነው ዕቅድ "የ10 ቀናት ፍልሚያ" የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ መርመራው በዕድሜ ለገፉ ሰዎችና ተጠጋግተው ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች ቅድሚያ እንደሚሰጥም ተገልጿል።

ነገር ግን የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው በርካታ የጤና ባለሙያዎች የታቀደው ሁሉንም የከተማዋን ነዋሪ ለመመርመር የተያዘው ግዙፍ ዕቅድ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ አዋጪ እንዳልሆነ እየተናገሩ ነው።

በዉሃን ዩኒቨርስቲ ዦንግናን ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው የጽኑ ህሙማን ክፍል ኃላፊ የሆኑት ፔንግ ዢዮንግ እንዳሉት፤ ምርመራው በተለይ የጤና ባለሙያዎችን፣ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑና በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ባላቸው ሰዎች ላይ ቢያተኩር መልካም እንደሆነ መክረዋል።

ሌላ የዉሃን ዩኒቨርስቲ ኃላፊ ደግሞ፤ እስካሁን ከ3 እስከ 5 ሚሊዮን የሚደርሰው የከተማዋ ነዋሪ በመመርመሩ የቀሩትን ከ6 አስከ 8 ሚሊዮን የሚደርሱትን ሰዎች በ10 ቀናት ውስጥ መርምሮ ለማጠናቀቅ እንደሚቻል አመልክተዋል።

ኮሮና
Banner