ኮሮናቫይረስ፡ ምስጢራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት እየረዳ ነው

ለቀብር የተዘጋጁ የእሬሳ ሳጥኖች

የፎቶው ባለመብት, SINOXOLO FUNERAL DIRECTORS

የምስሉ መግለጫ, በደቡብ አፍሪካ ቀብር ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ገደብ ተጥሎበታል

ደቡብ አፍሪካ ያወጣችው ሰዎች እንዳይሰበሰቡ የሚከለክለው ሕግ ዜጎች በርካታ ልማዶቻቸውን እንዲተዉ ያስገደዳቸው ቢሆንም አንድ የተረሳ ምስጢራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ግን እንዲያስራራ አድርጓል።

በቅርቡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በአንድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኙ 40 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘው ነበር።

ወርሀ መጋቢት ላይ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በመላው አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጃቸውና ሰዎች በአንድ ቦታ ላይ እንዳይሰበሰቡ ከመከልከላቸው አንድ ሳምንት በፊት በሰሜናዊ ኬፕ ታውን የማጆላ መንደር ነዋሪዎች የሆኑ 100 ሰዎች በአንድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ታድመው ነበር።

በዚህም ሳቢያ በአሁኑ ጊዜ ይህች መንደር የአገሪቱ የኮሮናቫይረስ ማዕከል ሆናለች። በመንደሪቱ የነበረውን የቀብር ሥነ ሥርዓት የታደሙና በሌሎች ሁለት ከተሞች በተመሳሳይ ሥርዓት ላይ ተካፋይ የነበሩት 200 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በመላው አገሪቱ ካለው ቁጥር በቀብር ላይ በበሽታው የተያዙ ሰዎች አንድ አራተኛውን ይይዛሉ።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ተብሎ በወጣው ሕግ መሰረት በአንድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ 50 ሰዎች መታደም እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን ለአንዳንዶች ግን ይህ ቁጥር አሁንም ትንሽ ነው።

የሰሜናዊ ኬፕ ታውን አውራጃ ጤና ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ሲዝዌ ኩፔሎ እንደሚሉት ሰው የሞተባቸው ቤተሰቦች ሕጉን በመተላለፍ የቫይረሱን ስርጭት እያባባሱት ነው።

"በአውራጃዋ ያለው የቀብር ሥነ ሥርዓት አፈጻጸም በጣም አሳስቦናል" ብለዋል።

"የአካባቢው አዛውንት መሪዎች ባቀረቡት ሀሳብ መሰረት ሁሉም ሟቾች ተመሳሳይ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲኖራቸው ተስማምተናል። ሁሉም ከአስከሬን ማቆያ ተወስደው ወዲያው እንዲቀበሩ የቀረበው ሀሳብ አስማምቶን ነበር።"

ነገር ግን ማኅበረሰቡ ለብዙ ዓመታት ሲተገብረው የነበረውን የቀብር ሥነ ሥርዓትና ሌሎች ማኅበራዊ ክንውኖችን በአንድ ጊዜ ለመተው ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም።

ከቀብር በኋላ የተሰበሰቡ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የምስሉ መግለጫ, ከቀበር በኋላ ተሰብስቦ መመገብና አብሮ መቆየት የተለመደ ባህል ነው

የባህል ጥናት ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ሶማዶዳ ፊኬኒ እንደሚሉት እንደዚህ አይነት ክንውኖች በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውና የአንድን ሰው የህይወት ጉዞ የሚዘክሩ ናቸው።

"በተለይ አፍሪካውያን እነዚህን ክንውኖች ማኅበራዊ መስተጋብር ለመፍጠርና የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ለማሳለጥ ይጠቀሙባቸዋል። የቀብር ሥነ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን እንደ ሠርግ፤ ሐይማኖታዊ ሥነ ሠርዓቶችና ሌሎችም ከዚህ ውስጥ ይካተታሉ።"

በበርካታ የአፍሪካ አገራት አንድ ግለሰብ ሲሞት ቤተሰቦችና ዘመድ አዝማድ የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ለመታደምና የቅርብ ቤተሰቦችን ለማጽናናት ረጅም ርቀት ተጉዘው ቀብር ላይ ይገኛሉ።

ጓደኛና ጎረቤት ደግሞ በተደጋጋሚ ወደ ሟች ቤተሰቦች በመሄድ ለማጽናናት ይሞክራሉ፤ በቻሉት መጠንም እርዳታ ለማድረግም ይጥራሉ።

ለማጽናናት የሚመጣውን ሰው ለማስተናገድ ደግሞ ከብት ይታረዳል እንዲሁም ሌሎች አይነት ምግቦች ይሰራሉ። በዚህ ወቅት ደግሞ የምግብ መስሪያ እቃዎችና መመገቢያዎች በበርካታ ሰዎች እጅ ይነካካሉ።

በተጨማሪም የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ሲፈጸመም ለመቃብር ቦታ መቆፈሪያነት ጥቅም ላይ የሚውሉት መሳሪያዎችም በብዙ ሰዎች እጅ ይገባሉ።

በተጨማሪም ለማጽናናት የሚመጣው ሰው ቤተሰቡን እያቀፈ ነው ሀዘኑን የሚገልጸው። ቤተሰቡ ከሚያውቃቸውና ከሚቀርባቸው ሰዎች በተጨማሪ ደግሞ መንገደኛ እንኳን የለቅሶ ድምጽ ሲሰማ ገብቶ ማጽናናት የተለመደ ነው።

እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ታዲያ የኮሮናቫይረስን ለማስተላለፍ በእጅጉ የተመቹ ናቸው።

አንድ ቄስ በቀብር ስፍራ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Sinoxolo Funeral Directors

የምስሉ መግለጫ, የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ጥቂት ሰው ብቻ የሚገኝባቸው ሆነዋል

በዚህ መልኩ የሚተላለፈውን የኮሮረናቫይረስ ለመግታት ደግሞ የአካባቢው ንጉሥ ዝዌሎዙኮ ማቲዋኔ፤ በርካታ ሰዎች ታድመውባቸው የሚፈጽሙትን የቀብር ሥነ ሥርዓት በመከልከል ‘ኡኩቁሼካ’ የሚባለው ምስጢራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተመልሶ ተግባራዊ እንዲሆን አዘዋል።

የንጉሡ ቃል አቀባይ ንኮሲ ራኑጋ እንዳለው ውሳኔው የተላለፈው ከሌሎች የአካባቢው መሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ ነው።

ማኅበረሰባችንን ከከባድ ወረርሽኝ ለመከላከል ነው ጥረት እያደረግን ያለነው። በዚህ የቀብር ሥነ ሥርዓት መሰረት ሟች በመጀመሪያው አልያም በሁለተኛው ቀን እንዲቀበር ይደረጋል። በተጨማሪም ግለሰቡ ሲሞት አጠገቡ የነበሩ ሰዎች ብቻ ናቸው በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘት የሚችሉት።"

በንጉሡ ግዛት ስር የሚገኙት የቁምቡ፣ ትሶሎ፣ ኡግዬ፣ ማክሊር እና ሌሎች አጎራባች ከተሞች ይህንን የቀብር ሥነ ሥርዓት እየፈጸሙ ይገኛሉ።

"ወደዚህ ባህላዊና ምስጢራዊ ቀብር ሥነ ሥርዓት መመለሳችን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ቤተሰቦችም ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ በኋላ በአግባቡ እራሳቸውን እንዲያጸዱ ይሄው ባህል ያስገድዳል።"

ሌላው ቀርቶ አንድ አባሉ የሞተበት ቤተሰብ የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ለማስፈጸም ቀላል የማይባል ገንዘብ ነበር የሚያወጣው። በተለይ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በታገደበት በዚህ ወቅት ቤተሰቦች ሥራ ሰርተው ገንዘብ ማግኘት አይችሉም።

ቃል አቀባዩ እንደሚሉት አንዳንድ ቤተሰቦች እንዲያውም ብዙ ሰው የሚታደምበት የቀብር ሥርዓት ለመፈጸም ብዙ ገንዘብ ከቤተሰብና ጎረቤት ይበደራሉ።

ስለዚህ አሁን ተግባራዊ እየተደረገ ቆየት ያለው ባህላዊ የቀብር ሥርዓት የቫይረሱን ስርጭት ከመግታት ባለፈ ቤተሰቦች የሚያጋጥማቸውን ኢኮኖሚያዊ ጫናም ቀለል ያደርገዋል።

በአሁኑ ሰዓት አዲስ አይነት የቀብር ሥርዓት ማካሄድ አስፈላጊ የሆነው በገጠሪቱ የደቡብ አፍሪካ ክፍል ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ተተሞች ውስጥ ጭምር ነው።

በዚህ የወረርሽኝ ጊዜ በተለይ በበርካታ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ያለው የመቃብር ስፍራ ውስንነት ባለስልጣናት ብዙ ሰዎችን በአንድ ቦታ ላይ እስከ መቅበር ሊያደርስ እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

ስለዚህም ይህ አይነነቱ ምስጢራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋትን ከመግታት ባሻገር በሟች ቤተሰብና የሐዘን ሥነ ሥርዓቱን በሚታደሙ ሰዎች ላይ የሚኖረውን የወጪ ጫና ያቀላል ተብሎ ይታሰባል።

ኮሮና
Banner