ኮሮና ቫይረስ፦ የወባ መድሃኒቶች ለምን ገነኑ?

በፈረንሳይ የሚገኝ መድኃኒት መደብር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሮና ቫይረስ ወርርሽኝ በአለም በሰፊው መዛመት የሰው ልጅን ባሸበረበት በአሁኑ ወቅት መድኃኒቱን ለማግኘት የተለያዩ አገራት ሳይንሳዊ ምርምሮችንና ሙከራዎችን አቀላጥፈው በመስራት ላይ ናቸው።

ከዚሁም ጋር ተያይዞ የኮሮናቫይረስን ለማዳን ፀረ - ወባ መድኃኒቶች ጥቅም አላቸው በሚልም ክሎሮኪንና ሃይድሮክሲክሎሮኪን ተፈላጊነትም በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ነው።

ምንም እንኳን የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ለፈዋሽነታቸው ምንም አይነት ማስረጃ የለም ቢልም አንዳንድ አገራት በፀና ለታመሙ የኮሮና ህሙማንን ለማከም እንጠቀምበታለን በማለት ላይ ናቸው።

ስለ መድሃኒቶቹ ምን ያህል እናውቃለን?

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ በሚያደርጓቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች "እነዚህን መድሃኒቶች ብትሞክሯቸው ምንድን ነው የምታጡት?" ሲሉ ተደምጠዋል።

የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ጄይር ቦልሶናሮም "መድሃኒቶቹ እየሰሩ ነው፤ ያድናሉም" ማለታቸውን ተከትሎ ሃሰተኛ መረጃን በማስተላለፍ በሚል ፌስቡክ መልእክታቸውን ከገፁ ላይ አጥፍቷል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ክሎሮኪን የወባ ህመምን ለማከም በተለይም ትኩሳትን ለመቀነስ ለአመታት ያገለገለ ሲሆን የኮሮና ቫይረስም በሰውነት ውስጥ ገብቶ ጉዳት እንዳያስከትል ማገድ ይችላልም የሚል ከፍተኛ ተስፋ ተጥሏል።

"በላብራቶሪ ውስጥ በምናይበት ወቅት ክሎሮኪንኮሮና ቫይረስን ማገድ ይችላል። እናም ከአንዳንድ የጤና ባለሙያዎችም እንደተገኘው መረጃ መድኃኒቱ የኮሮናቫይረስን ህሙማን ማከም እንደሚያስችል ነው" በማለት የቢቢሲ ጤና ዘጋቢ ጄምስ ጋላግሄር ተናግሯል።

ምንም እንኳን አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ይህንን ይበሉ እንጂ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ለማከም በተደረገ ሙከራ ሙሉ በሙሉ አመርቂ ውጤት ማምጣት ያልተቻለ ሲሆን አንድ የፈረንሳይ ጥናት ደግሞ ምንም ውጤት እንደሌለው አመላክቷል።

ከዚህም በተጨማሪ መድሃኒቱ ለተጓዳኝ ችግሮች ማለትም ለጉበትና ለኩላሊት ጉዳት ይዳርጋል ተብሏል።

"የመድሃኒቱን ውጤታማነት ለመረዳት በከፍተኛ መጠንና ጥራት ሙከራዎች ልናደርግ ይገባል" በማለት የኦክስፎርዱ ተመራማሪ ኮሜ ጊቢንጄ ይናገራሉ።

እስካሁን ባለው በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ ስፔንና ቻይና ሃያ የሚሆኑ ሙከራዎች ተሞክረዋል።

እንግሊዝ በቫይረሱ ለተጠቁ ህሙማን የወባ መድሃኒት እፎይታ ሊሆን ከቻለ በሚል ምርመራዋን አጠናክራ የቀጠለች ሲሆን አሜሪካ በበኩሏ ክሎሮኪን፣ ሃይድሮክሲክሎሮኪንና የህመም ማስታገሻ የሆነውን ዛይትሮማክከስ በማጣመር ምርምሮችን እያካሄደች ነው።

የትኞቹ አገራት ፈቃድ ሰጡ?

የአሜሪካው የምግብና የመድሃኒት ቁጥጥር አስተዳደር መድሃኒቶቹ የኮሮናቫይረስ ህመሙማን ለማከም እንዲውሉ ለተወሰኑ ሆስፒታሎች ፈቃድ ሰጥቷል።

ምንም እንኳን አስተዳደሩ ሙሉ በሙሉ መድኃኒቱ ይፈውሳል ብሎ ባያረጋግጥም ሆስፒታሎች የኮቪድ 19 ህሙማንን ለማከም በሚጠይቁበት ጊዜ ካላው የክምችት ክፍል በመስጠት ላይ ነው።

ሳይንቲስት በኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ላብራቶሪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ መንግሥት ሰላሳ ሚሊዮን የሃይድሮክሲክሎሮኪን እንክብሎችን ከጀርመን የመድኃኒት ማምረቻ በእርዳታ እንዳገኘ ገልጿል።

ሌሎች ሃገራት በየደረጃው መድሃኒቱን በመጠቀም ላይ ናቸው።

ፈረንሳይ የኮሮና ህሙማንን እንዲያክሙ ፈቃድ ብትሰጥም የመድኃኒት ተቆጣጣሪዎች የጎንዮሽ ጉዳቱ ላይ ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ነው።

የህንድ ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ሃይድሮክሲክሮኪን ለጤና ባለሙያዎች መከላከያ እንዲሆናቸው እንዲሁም በህመሙ ከተጠቁ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች እንዲወስዱት ፈቅዷል።

የተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ አገራትም ሙከራዎችን እያደረጉ ናቸው። ሃይድሮክሲክሎሮኪንን በመጀመሪያ ደረጃ መጠቀም ጀምሬያለሁ የምትለውን ባህሬንን ጨምሮ፣ ሞሮኮ፣ አልጀሪያና ቱኒዝያም መድሃኒቱ በተግባር ላይ እንዲውል ፈቅደዋል።

በቂ ክሎሮኪን አለ?

መድኃኒቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈለገ በመምጣቱም አገራት እጥረት እያጋጠማቸው ነው ተብሏል።

ክሎሮኪንም ሆነ ሌሎች የወባ መድሃኒቶች በታዳጊ አገራት ውስጥ በብዛት ይገኙ ነበር።

አሁን ካለው ፍላጎትም ጋር ተያይዞ እጥረት በማጋጠሙ አገራት የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ ተገደዋል።

ዮርዳኖስ መድሃኒቱ እንዳይሸጥ የከለከለች ሲሆን ኩዌት በበኩሏ መድሃኒቶቹ በመንግሥት ሆስፒታሎችና የጤና ማእከላት ብቻ እንዲገኙ ውሳኔ አስተላልፋለች።

ኬንያ በበኩሏ ያለ ፈቃድ መድሃኒቶቹ እንዳይሸጡ ስትከለክል ህንድ ደግሞ ወደ ውጭ የመላክ እገዳን ጥላለች።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ መድሃኒቶቹ እንዲላኩላቸው የጠየቁዋቸው ሲሆን ህንድም ልትልክ ተችላለች ተብሏል።

መድሃኒቱ የወባ በሽታ አዳኝነቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ አገልግሎት ላይ እንዳይውል ከአመታት በፊት በናይጄሪያ የታገደ ቢሆንም አሁንም ወባን ብዙዎች ይጠቀሙበታል ተብሏል።

በተለይም ቻይና ክሎሮኪን ለኮሮና ቫይረስ ህሙማን እየሰጠች ነው የሚለውን ዜና ተከትሎ ብዙዎች ማከማቸት ጀምረዋል።

ነገር ግን የናይጀሪያ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማእከል የአለም ጤና ድርጅት ፈቃድ እስካልሰጠ ድረስ መድሃኒቱን መጠቀም አይቻልም እያሉ ነው።

ባለስልጣናቱ እንዳሳወቁት ክሎሮኪንን በከፍተኛ መጠን ወስደው የተመረዙ ሰዎች መኖራቸውን ነው።

ኮሮና