ኮሮና ቫይረስ፡ በዓለም ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም ላይ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ መሆኑን ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ወረርሽኙን ለመግታት ለሚደረገው ትንቅንቅም ጨለም ያለ ዜና ነው ተብሏል።
እስካሁን ባለው መረጃ 53ሺ ሰዎች በቫይረሱ ህይወታቸውን አጥተዋል፤ 210 ሺ ሰዎች ደግሞ እንዳገገሙ የዩኒቨርስቲው መረጃ ጠቁሟል።
በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ቀዳሚ በሆነችው አሜሪካ በትናንትናው እለት መጋቢት 24፣ 2012 ዓ.ም አንድ ሺ 169 ሰዎች ሞተዋል።
ለሰው ልጅ ጠንቅ የሆነው ኮቪድ- 19 የተከሰተው ከሶስት ወራት በፊት በቻይና፣ ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ ነው።
የ34 አመቱ ዶክተር፣ ዶ/ር ሊ ዌንሊያንግ ቫይረሱን አስመልክቶ ለሌሎች የህክምና ባለሙያዎች ቢያስጠነቅቅም በምላሹ ግን የፖሊስ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲደርሰው ሆኗል።
ዶክተሩም በውሃን ከተማ በቫይረሱ የታመሙ ሰዎችን ሲንከባከብ ህይወቱን ተነጥቋል።
ምንም እንኳን ከዩኒቨርስቲው የተገኘው መረጃ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ጥር ከአንድ ሚሊዮን ትንሽ ከፍ ያለ ቢሆንም ቁጥሩ ግን ከዚያ በላይ ነው ተብሏል።
ምክንያቱም ከአመዘጋገብ ስርዓት ጋር ተያይዞ ክፍተቶች በመታየታቸው ነው፤ በባለፈው ወር በበሽታው የተያዙ መቶ ሺ ሰዎችን ለመመዝገብ ከአንድ ወር በላይ ጊዜን ወስዷል።
ከዚህ ቁጥር ውስጥ ሩብ የሚሆነው በአሜሪካ የተከሰተ ሲሆን ግማሽ የሚሆነው ደግሞ በአውሮፓ ያለውን ቁጥር ያሳያል።
በትናንትናው ዕለት በስፔን ባለፉት ሃያ አራት ሰዓታት ብቻ 950 ሰዎች ሞተዋል።
ከጣልያን በመቀጠል ብዙ ሰዎችን በኮሮናቫይረስ ባጣችው ስፔን፤ የምጣኔ ሃብት መዳሸቅ እያጋጠማት ሲሆን 900 ሺ የሚሆኑ ሰዎችም ስራቸውን አጥተዋል ተብሏል።
በአሜሪካም በትናንትናው ዕለት 6.6 ሚሊዮን ሰዎች ስራቸውን በማጣታቸው የጥቅማጥቅሞች ይገባኛል ጥያቄዎች ቀርበዋል።













