ከኮሮናቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ አስገራሚ ሕግ ያወጡ አምስት አገራት

ውሻን በምሽት ማንሸራሸር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ውሻን በምሽት ማንሸራሸር

ኮቪድ-19 ብዙ እያሳየን ነው። ሀብታም አገራት ጭምር ቀውስን የመሸከም አቅማቸው እስከምን ድረስ እንደሆነ ፍንጭ ሰጥቷል።

የተለያዩ አገራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቀልበስ ከልል እስከ ጥብቅ መመሪያ አውጥተዋል። የሚከተሉት አምስት አገራት ግን መመሪያቸው ለይት ያለ ሆኖ አግኝተነዋል።ት

1. ሰርቢያ

ሰርቢያ አንድ ሰሞን ለውሾች የሽርሽር ሰዓት ወስና ነበር። ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት ብቻ። የውሻ ባለቤቶች ግን ይህንን ተቃውመው አቤት በማለታቸው መመሪያው ተሸሯል። አንድ የእንሰሳት ሐኪም እንዳለው የምሽቱን የሽርሽር ሰዓት ማሳለፍ ለውሾች ፊኛ ጤና መልካም አይደለም።

2. ኮሎምቢያ

በአንዳንድ የኮሎምቢያ ከተሞች ወደ ውጭ የሚወጣው በመታወቂያ ቁጥር መሰረት ነው። ለምሳሌ መታወቂያ ቁጥራቸው በዜሮ፣ በ4 እና በ7 የሚጨርሱ ሰኞ ሰኞ ደጅ ወጥተው ሽር ማለት ይችላሉ።

በ1 በ8 እና በ5 የሚጨርሱ ደግሞ ማክሰኞ የግላቸው ናት። ጎረቤት ቦሊቪያም ተመሳሳይ ዘዴን ተከትላለች።

በእግር የሚንሸራሸሩ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

3. ፓናማ

የመካከለኛው አሜሪካ አገር ናት።

አንድ ሺህ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘውባታል። ወረርሽኙን ለመቀልበስ ከቤት አትውጡ ብላለች። ሆኖም ግን ለተወሰነ ሰዓት ወጣ ብሎ መናፈስ ይቻላል። ታዲያ ይህ ፈቃድ ግን በጾታ ተለይቶ ነው።

ከረቡዕ ጀምሮ ዜጎች ለ2 ሰዓት ብቻ ከቤት ወጥተው መመለስ ይችላሉ። ወንዶች የሚናፈሱበት ቀንና ሴቶች የሚናፈሱበት ቀን ግን የተለያየ ነው። ነገር ግን ፓናማ ለምን ይህን እንዳደረገች ይፋ አላደረገችም።

ሆኖም እሑድ እሑድ ወንድም ሆነ ሴት ከቤት አይወጣም። ይሄን መመሪያ ያወጣነው የራሳችሁን ሕይወት ለመታደግ እንጂ ለእኛ ብለን አይደለም ብለዋል የአገሪቱ የደኅንነት ሚኒስትር ሁዋን ፒኖ።

4. ቤላሩስ

እንደ ቤላሩስ ፕሬዝዳንት በኮሮናቫይረስ ላይ የተሳለቀ መሪ የለም። አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ይባላሉ። በቲቪ ቀርበው "የምን ኮሮና ነው የምታወሩት? እኔ ቫይረሱ አይታየኝም" ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት የበረዶ የገና ጨዋታ ከሕዝብ ጋር እየተመለከቱ ነው ታዲያ። ጨምረውም "የሚባለው ቫይረስ ካለም ይሄ በረዶ ድራሹን ያጠፋዋል" ሲሉ ቀልደዋል።

አገር ቤት በአንዳንድ ግለሰቦች አረቄ ፍቱን መድኃኒት ነው እየተባለ እንደሚቀለደው ሁሉ አሌክሳንደር ሉካሼንኮም "ለኮሮናቫይረስ መድኃኒቱ ቮድካ ነው፤ ቮድካ ጠጡበት›› ብለዋል።

ከአውሮፓ አገሮች በተለየ ቤላሩስ የስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንዳልዘጋች መዘገባችን ይታወሳል።

5. ቱርከሚስታን

ቱርከሚስታን በበኩሏ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት ከሁሉ የተለየ መንገድን መርጣለች። ይህም "ኮሮናቫይረስ" የሚለው ቃል ላይ ክልከላን መጣል ነው።

በቱርኬሚስታን "ኮሮናቫይረስ" ማለት አይፈቀድም።

መንግሥት የጤና መረጃ ከያዙ በራሪ ወረቀቶች ላይ "ኮሮናቫይረስ" የሚለውን ቃል አስወግዷል። ባለቤትነቱ የመንግሥት የሆነ ሬዲዮ ጣቢያ የፊት ማስክ የሚያደርጉ እና "ኮሮናቫይረስ" የሚለውን ቃል የሚጠቀሙ ዜጎች እስር ሊጠብቃቸው ይችላል ሲል ዘግቧል።

በቫይረሱ ክፉኛ የተመታችው ኢራን ጎረቤት የሆነው የቱርከሚስታን መንግሥት እስካሁን ኮሮና የሚሉት በሽታ በአገራችን አልተገኘም እያለ ነው።

ኮሮና
Banner