በአፍሪካ ከ63 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ቢያዙም የተጣለው ገደብ እየላላ ነው

ምርመራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል አዲስ ያወጣው አሃዝ እንደሚያመለክተው እስካሁን 63 ሺህ 325 በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች በአህጉሪቱ ውስጥ ተመዝግበዋል።

በተጨማሪም 2290 ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ የሞቱ ሲሆን 21 ሺህ 821 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ማገገማቸው ተነግሯል።

የወረርሽኙ መስፋፋት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርስበት ጊዜ ገና እንደሆነ ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ቢሆንም በርካታ የአፍሪካ አገራት ለሳምንታት ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ ዕገዳ በዚህ ሳምንት ማላላት ጀምረዋል።

በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኮሮናቫይረስ ምርመራ በማድረግ ተጠቃሿ ደቡብ አፍሪካ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን አግኝታለች።

የእንቅስቃሴ ገደቡ በአገራቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ያስከተለው ጫና ጎልቶ መታየት በመጀመሩ አገራት የጣሉትን ገደብ ለማላላት እየወሰኑ ነው።

በዚህም መሰረት ጂቡቲ፣ ማሊ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጋቦን፣ ኒጀር እና ኡጋንዳ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር በሚል ለሳምንታት ጥለውት የነበረውን የእንቅስቃሴ እገዳ ለማላላት ያወጡትን ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የምዕራብ አፍሪካ አገራቱ ላይቤሪያና ጋና የእንቅስቃሴ ገደቡን ለተጨማሪ ሳምንታት አራዝመውታል። በዚህ መሰረትም ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ ዕገዳውን ለሁለት ሳምንት ሲያራዝሙት የጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ደግሞ ለሦስት ሳምንት አራዝመውታል።

ማዳጋስካር ከአሪቲ የተዘጋጀ ነው የተባለውን መድኃኒት በስፋት እያስተዋወቀች ቢሆንም ተገቢው ሳይንሳዊ ሙከራ ስላልተደረገበት ጥያቄ እየተነሳበት ነው።

ቢሆንም ታንዛኒያ፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳዎና ዲሞክራቲክ ኮንጎን የመሳሰሉ አገራት "መድኃኒቱን" አዘው ወደ አገራቸው እያስገቡ ሲሆን ማዳጋስካርም በግዛቷ ውስጥ እንዲሸጥ ፈቃድ ሰጥታለች።

የዓለም ጤና ድርጅት 'የመድኃኒቱን' አስተማማኝነት በተመለከተ ምንም የተረጋገጠ ነገር ስለሌለ ሰዎች እንዳይጠቀሙ አስጠንቅቋል።

የደቡብ አፍሪካው ጤና ሚኒስትር ለማዳጋስካር ባላስልጣናት እንደተናገሩት አገራቸው ከስራስር የተሰራውን መድኃኒት በሳይንሳዊ መንገድ ምርመራ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻለች።

ኮሮና
Banner