“በአፍሪካ በኤችአይቪ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በግማሽ ሚሊዮን ሊጨምር ይችላል”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰሀራ በታች ባሉ አገራት በኤችአይቪ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሊጨምር እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳለ ሆኖ በኤችአይቪ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምር የድርጅቱ ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ገልጸዋል።
መንግሥታት ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ድርጅቱ ከተባበሩት መንግሥታት የኤችአይቪ ክንፍ (ዩኤንኤድስ) ጋር በመጣመር የሠራው የዳሰሳ ጥናት፤ ለስድስት ወራት የኤችአይቪ መድኃኒት ቢቋረጥ የሟቾች ቁጥር እንደሚጨምር ያሳያል። ቁጥሩ፤ በበሽታው ሳቢያ ከ12 ዓመት በፊት ይሞቱ ከነበሩ ሰዎች ጋር ሊስተካከል እንደሚችልም ተጠቁሟል።
ያኔ በመላው አህጉሪቱ 950,000 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሞተው ነበር።
“አፍሪካ ውስጥ ከኤድስ ጋር በተያያዘ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ቢሞቱ እጅግ አሳዛኝ ነው። ወዳለፍነው ዘመን ተንሸራተትን ማለትም ነው” ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ አስረድተዋል።
የዩኤንኤድስ ዋና ዳይሬክተር ዊኒ ቢንያማ እንዳሉት፤ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ የኤችአይቪ ሕክምና እንቅፋት ሊገጥመው ይችላል። ሕክምና መስጫዎች ሊዘጉ ወይም አገልግሎት ለመስጠት ሊቸገሩም ይችላሉ ብለዋል።
“በኮቪድ-19 ምክንያት ሕክምና መስጫዎች ከመጠን በላይ ሊጨናነቁም ይችላሉ” ሲሉም አስረድተዋል።
ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት የሚደረገው ጥረት ኤችአይቪን ለማስወገድ የተደረገው ውጊያ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ገልጸው፤ “አንዱ በሽታ ለሌላው በሽታ የሚሰጠው ሕክምና ላይ ማጥላት የለበትም” ብለዋል።
ዶ/ር ቴድሮስ በበኩላቸው አገራት ኤችአይቪ ያለባቸው ሰዎች ሕክምናቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉና አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ማድረግም እንዳለባቸው ተናግረዋል።
አንዳንድ አገራች ዜጎች በብዛት መድኃኒት የሚያገኙበት መንገድ እየቀየሱ ነው። ራስ መመርመሪያ መሣሪያ የሚገኝባቸው ቦታዎች በመመደብ የሕክምና ባለሙያዎችን ጫና ለማቅለልም እየተሞከረ ነው።
“ሕክምና ላይ ያሉ ሰዎች ሕክምናቸውን እንዲቀጥሉ መደረግ አለበት” ብለዋል ዶ/ር ቴድሮስ።














