ኮሮናቫይረስ፡ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች 419 ሚሊየን ዶላር ካሳ ሊከፍሉ ይችላሉ

ፕሪምየር ሊግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ሊጉ በቅርቡ ጀምሮ በዝግ ስታዲየም ቢጫወቱም እንኳን ለአገር ውስጥና ለዓለማቀፍ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች እስከ 419 ሚሊየን ዶላር ካሳ ሊከፍሉ እንደሚችሉ ተነግሯቸዋል።

ቢቢሲ ስፖርት ባገኘው መረጃ መሰረት ሊጉ ከነጭራሹ የሚቋረጥ ከሆነ አልያም ከሊጉ የሚወርዱ ቡድኖች የሚኖሩ ካልሆነ ክለቦቹ ከተገለጸው ገንዘብ ተጨማሪ ሊከፍሉም ይችላሉ።

የፕሪምረየር ሊግ ክለቦች ደግሞ ሊጉን ማስቀጠል በሚቻለበት ሁኔታ ላይ የሚያደርጉትን ውይይት ትናንት አስቀጥለዋል። የ2019/20 ወድድር ዘመን 92 ጨዋታዎች ይቀሩታል። እነዚህን ጨዋታዎች እንዴት እናጠናቅ በሚለው ዙሪያ የሊጉ ክለቦች ላለፉት ሳምንታት የቪድዮ ስብሰባ ሲያደርጉ ነበር።

የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ደግሞ ሊጉን ለማጠናቀቅ ቆርጠው ተነስተዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ቢያንስ 10 ገለልተኛ ሜዳዎች ያስፈለጋሉ ነው የሚሉት። ገለልተኛ ሜዳዎችን መጠቀም ያስፈለገው ደጋፊዎች ከሜዳ ውጪም ቢሆን እንዳይሰበሰቡ በማሰብ ነው ተብሏል።

አልፎም የሚመረጡት ሜዳዎች ከፖሊስና የስፖርት ሜዳዎችን ደህንነት ከሚመረምር አካል ይሁንታ ያገኙ መሆን አለባቸው ተብሏል። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መጋቢት ወር መግቢያ ላይ ነበር በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንዲቆም የተደረገው።

ሁሉም የሊጉ ክለቦች የቀሩትን 92 ጨዋታዎች ለመጫወት ተስማምተዋል። የዚህ ዓመት ወድድር ይቋረጥ የሚል ሐሳብ ከየትኛውም ክለብ አልመጣም ተብሏል።

የገንዘብ ክፍያው የተጠየቀው የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች በታሰበላቸው ጊዜ ባለመካሄዳቸው ነው። በተጨማሪም ሊጉ የሚቀጥል ቢሆን እንኳን ጨዋታዎቹ ያለ ተመልካች መካሄዳቸውና ከቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር ስምምነት ከተደረሰበት ጊዜ ውጪ ስለሚካሄዱ ነው።

የፕሪምየር ሊግ ዋና ስራ አስፈጻሚው ሪቻርድ ማስተርስ በቅርቡ እንደገለጹት ደግሞ የዘንድሮው ሊግ የሚቋረት ከሆነ ክለቦች በአጠቃላይ እስከ 1 ቢሊየን ፓውንድ ኪሳራ ሊያጋጥማቸው ይችላል።

ገለልተኛ ሜዳዎች ላይ ጨዋታዎቹን መቀጠል በሚለው ሀሳብ አንዳንድ ክለቦች አልተስማሙም። የሊጉ ኃላፊዎችም ቡድኖቹን ለማሳመንና በተቻለ መጠን ጨዋታዎቹን በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ለማስጀመር እየሞከሩ ነው።

እስካሁን ዋትፎርድ፣ አስቶን ቪላ እና ብራይተን ጨዋታዎቹን በገለልተኛ ሜዳ ማካሄድ የሚለውን ሀሳብ በይፋ የተቃወሙ ሲሆን በሜዳቸው ደህንነቱ የተጨበቀ ጨዋታ ማካሄድ እንደሚችሉ መንግስትን ማሳመን ይጠበቅባቸዋል።

የሊቨርፑል ከተማ ከንቲባ ደግሞ ጨዋታዎቹ በገለልተኛ ሜዳ ተካሂደውም ሊቨርፑል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ የሚያነሳ ከሆነ ደጋፊዎች በአንፊል ስታዲየም ዙሪያ ተሰባስበው ደስታቸውን ሊገልጹ እንደሚችሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ኮሮና
Banner