የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በገለልተኛ ሜዳ ሊጠናቀቅ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ሊጉን ለማጠናቀቅ ቆርጠው ተነስተዋል። የሊጉ ክለቦች ይህን ለማድረግ ደግሞ ቢያንስ 10 ገለልተኛ ሜዳዎች ያስፈለጋሉ ነው የሚሉት።
አልፎም ተጫዋቾችና ወደ ሜዳ የሚገቡ ሌሎች ባለሙያዎችን ለመመርመር 40 ሺህ መመርመሪያ መሣሪያዎች ያስፈልጋሉ።
የ2019/20 ወድድር ዘመን 92 ጨዋታዎች ይቀሩታል። እነዚህን ጨዋታዎች እንዴት እናጠናቅ በሚለው ዙሪያ የሊጉ ክለቦች የቪድዮ ስብሰባ አድርገው ነበር። በስብሰባው ላይ እንደ ሕክምና ባለሙያዎች ያሉ ያገባቸዋል የተባሉ ሰዎችም ተገኝተው ነበር።
ክለቦች ሊጉ በቀላሉ ወደ ውድድር እንደማይመለስ መግባባት ላይ ደርሰዋል። የፕሪሚዬር ሊጉ አስተዳዳሪ አካል መንግሥት ይሁንታ ሲሰጥ ብቻ ነው ወደ ሜዳ የምንመለሰው ብሏል።
ገለልተኛ ሜዳዎችን መጠቀም ያስፈለገው ደጋፊዎች ከሜዳ ውጪም ቢሆን እንዳይሰበሰቡ በማሰብ ነው ተብሏል። አልፎም የሚመረጡት ሜዳዎች ከፖሊስና የስፖርት ሜዳዎችን ደህንነት ከሚመረምር አካል ይሁንታ ያገኙ መሆን አለባቸው ተብሏል።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ መጋቢት ወር መግቢያ ላይ ነበር በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እንዲቆም የተደረገው። ሁሉም የሊጉ ክለቦች የቀሩትን 92 ጨዋታዎች ለመጫወት ተስማምተዋል።
የዚህ ዓመት ወድድር ይቋረጥ የሚል ሐሳብ ከየትኛውም ክለብ አልመጣም ተብሏል።
የእንግሊዝ መንግሥት እንቅስቃሴዎች ቀስ በቀስ ወደነበሩበት እንዲመለሱ ካደረገ በኋላ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በዝግ ሜዳ ወደ ውድድር እንደሚመለስ ይጠበቃል።
ተጨዋቾች በሳምንት ሁለት ጊዜ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ይደርግላቸዋል። በየቀኑ ደግሞ የበሽታው ምልክት ታየባቸው አልታየባቸው የሚለው ይለካል። አልፎም ሜዳዎች በየጊዜው ንፅህናቸው ይጣራል ተብሏል።
ተጫዎቾች ከጨዋታ ውጪ ባሉት ጊዜያት ሁሉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ አለባቸው። በውድድር ስፍራዎች ውስጥም ምግብ መብላትም ሆነ ገላን መታጠብ አይችሉም።














