ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ ታንዛኒያ በጸሎት ከኮሮናቫይረስ ነጻ መውጣቷን አወጁ

ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ አገራቸው ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነጻ መሆኗን አወጁ።

አነጋጋሪው ፕሬዝዳንት እንዳሉት ታንዛኒያ ከወረርሽኙ ነጻ የወጣችው በሕዝቧ ጸሎት መሆኑን ነው እንደ ምክንያት የጠቀሱት።

"እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን የኮሮናቫይረስ በሽታ ተጣራርጎ ተወግዷል" ሲሉ ዶዶማ በተባለችው ከተማ ውስጥ በአንድ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው ለነበሩ ምዕመናን ተናግረዋል።

ነገር ግን ዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት የታንዛኒያ መንግሥት በኮሮናቫይረስ ዙሪያ እየተከተለው ያለው መንገድ እያሳሰበው እንደሆነ ገልጿል።

የታንዛኒያ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ እየተገኙ ስላሉት የኮሮናቫይረስ ህሙማን መረጃን ይፋ ማድረጉንም አቁሟል።

ለመጨረሻ ጊዜ በታንዛኒያ ስላለው የወረርሽኙ ሁኔታ በይፋ ከተገለጸ ከአንድ ወር በላይ የሆነ ሲሆን፤ በመጨረሻው ሪፖርት ላይ 509 በበሽታው የተያዙ ሰዎችና 21 ሰዎች በአገሪቱ ውስጥ በበሽታው መሞታቸው ተገልጾ ነበር።

ነገር ግን ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ እራሳቸው ዳሬሰላም ውስጥ አራት ህሙማን ህክምና እያገኙ እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ግንቦት ወር ላይ የአሜሪካ ኤምባሲ ዳሬሰላም ከተማ ውስጥ ያሉ ሆስፒታሎች በህሙማን በመጥለቅለቃቸው በኮሮናቫይረስ የመያዝ እድልን ከፍተኛ ያደርገዋል በሚል ያወጣውን መግለጫ መንግሥት ውድቅ አድርጎታል።

ፕሬዝዳንቱ በተደጋጋሚ እንደሚሉት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቀውስ ተጋኗል በማለት ሕዝባቸው ወደ አብያተ ክርስቲያናትና መስጂዶች በመሄድ ጸሎት ካደረገ "ቫይረሱን ማሸነፍ ይቻላል" ብለው ተናግረዋል።