ተማሪዎች መገረፍ አለባቸው የሚሉት የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት

ጆን ማጉፉሊ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ የማደሪያ ክፍላቸውን በእሳት የለኮሱ ተማሪዎችን በልምጭ የገረፉ ከፍተኛ ባለስልጣንን አንቆለጳጰሱ።

አልበርት ቻላሚላ የተባሉት እኚህ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን፤ በሃገሪቱ ውስጥ ያለ የአንድ ግዛት ባለስልጣን ናቸው። ባለስልጣኑ ቆመው፣ ተማሪዎቹ በደረታቸው ተኝተው በልምጭ ጀርባቸው እስኪላጥ ሲገረፉ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ በስፋት ተሰራጭቷል።

ከዚህ ቀደም ቻላሚላን ሌላ የታንዛኒያ ሚኒስትር ቅጣቶችን የትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን ብቻ እንዲፈፅሙ ያደርጋሉ ሲሉ ተችተዋቸው ነበር።

ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ ተማሪዎች መቆንጠጥ ሲከፋም መገረፍ አለባቸው በሚለው አቋማቸው የሚታወቁ ሲሆን ባስ ሲልም በዚህ ረገድ ያለው ሕግ ተለውጦ እያንዳንዱ መምህር የሚያጠፋ ተማሪን 'ልቡ እስኪጠፋ' እንዲገርፈው እንዲፈቀድ ሀሳብ አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንቱ አንድ ተማሪ መቼ መቀጣት አለበት የሚለው መመሪያ ለቀቅ ያለ እንዲሆን ይፈልጋሉ።

በአሁኑ ወቅት የትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን እንኳ ቢሆኑ ተማሪዎችን መቅጣት አይፈቀድላቸውም። ተማሪዎችን የሚቀጡ እንኳ ከሆነ ጠንካራ ምክንያት ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን አራት ጊዜ ብቻ 'ሾጥ ሾጥ' ማድረግ ነው የተፈቀደው።

ፕሬዝዳንት ማጉፉሊ ተማሪ መቅጣት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ያሉትን ከሥራ ገበታቸው አባርረዋል።

"ኮሚሽነር ቻላሚላን አነጋግሬዋለሁ፤ እናም ደግ አደረግህ በማለት ላደረገው ነገር ያለኝን አድናቆት ገልጨለታለሁ" ብለዋል።

"እንደውም ልባቸው እስኪጠፋ ቢገርፋቸው ጥሩ ነበር። ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው የሚሉ ለተቃጠለው የተማሪዎች ማደሪያ መክፈል አለባቸው። እነዚህ ሕንፃዎች የተገነቡት በደሃ ወላጆች መዋጮ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።