ታንዛኒያ የዓለም ቅርስ የተባለ ቦታ ላይ ግድብ ልትገነባ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ በአፍሪካ ድንቅ ከሚባሉት ጥብቅ የእንስሳት ማቆያ አንዱ በሆነ አካባቢ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸው ብዙ ትችት እያስነሳ ነው።
ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀው ሃይል ማመንጫው ግድብ የሚገነባው ሴለስ በተባለው ጥብቅ ማቆያ ውስጥ በሚገኘው ሩፊጂ ወንዝ ላይ ሲሆን፤ አካባቢው ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ሳይንስና ባህል ድርጅት 'ዩኔስኮ' ዓለም ቅርስ ተብሎ ተመዝግቧል።
ታንዛኒያ ግድቡ የሃገሪቱን የኤሌክትሪክ አቅርቦት በእጥፍ ይጨምርልኛል ብትልም፤ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ደግሞ ድንቅ የሆኑትን የዱር አራዊትና መኖሪያቸውን ያጠፋዋል የሚል ስጋት አላቸው።
ፕሬዝዳንቱ ስምምነቱን የተፈራረሙት ከግብጽ ከመጡ ሁለት የግንባታ ድርጅቶች ጋር እንደሆነ ተገልጿል።
የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የሚኖረው የውሃ ማጠራቀሚያ በአፍሪካ ትልቁ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ 1200 ስኩዌር ኪሎሜትር ቦታ ይሸፍናል ተብሏል።
ታንዛኒያ ውስጥ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ዜጋ ብቻ ሲሆን የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኘው፤ የግድቡ ግንባታ ደግሞ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሁነኛ መፍትሄ ተደርጎ ተወስዷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለማቀፉ የአካባቢ ተቆርቋሪ ድርጅት እንደሚለው የግድቡ ስራ ከእንስሳቱ ባለፈ እስከ 200 ሺ የሚደርሱ የአካባቢው ገበሬዎችና አሳ አጥማጆች ህይወትንም አደጋ ላይ ይጥላል።
ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ባወጣው ሪፖርት መሰረት ግድቡ የታችኛው ተፋሰስ አካባቢዎችን አፈር ስለሚሸረሽር፤ ሃይቆች ሊደርቁ ይችላሉ።
ይህ ደግሞ በውሃው ላይ ህይወታቸው መሰረት ያደረጉ አእዋፍና እንስሳት ከአካባቢው እንዲሰደዱ ያስገድዳቸዋል።
የሴለስ ጥብቅ እስሳት ማቆያ ብዙ ብርቅዬ እስሳት የሚገኙት ሲሆን፤ ቁጥራቸው እጅግ እየተመናመነ የመጡት አውራሪና ዝሆንም ይገኙበታል።












