የተገደሉና የታሰሩ ጋዜጠኞች የዓመቱ የታይም መፅሔት ምርጥ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተቱ

ታይም መፅሔት ጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂን በፊት ገጹ ይዞት ወጥቷል

የፎቶው ባለመብት, Time

የምስሉ መግለጫ, ታይም መፅሔት ጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂን በፊት ገጹ ይዞት ወጥቷል

ታዋቂው የአሜሪካ 'ታይም' መጽሄት የተገደሉና የታሰሩ ጋዜጠኞችን የ2018 ምርጥ ሰዎች ብሎ መርጧል።

ጋዜጠኞቹን "ጠባቂዎቻችን " የሚል ስም የሰጣቸው ሲሆን፤ ሁሉም እውነትን ፍለጋ ባከናወኗቸው ስራዎች ምክንያት ጥቃት የደረሰባቸው ናቸው።

ቱርክ በሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ ውስጥ የተገደለው ጋዜጠኛ ጃማል ኻሾግጂ ደግሞ በመጽሄቱ የዓመቱ ምርጥ ሰው ዝርዝር ውስጥ ከገቡት ጋዜጠኞች መካከል ነው።

የአሜሪካው 'ካፒታል' መጽሄት መስሪያ ቤት ላይ በተፈጸመው ጥቃት የሞቱት ጋዜጠኞችም ተካተውበታል።

መጽሄቱ እንዳስታወቀው እነዚህ ሰዎች እውነትን ፍለጋ ህይወታቸውን፣ ስራቸውንና ቤተሰባቸውን አደጋ ላይ እስከመጣል የደረሱ ናቸው።

ዝርዝሩ ውስጥ እነማን ተካተቱ?

ጃማል ሾግጂ

የሳዑዲ ዜግነት ያለው ዝነኛው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጂ ቱርክ ኢስታንቡል ወደ ሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ገብቶ ሳይመለስ ቀረ።

በወቅቱ የቱርክ ባለስልጣናት በሳዑዲ ሰዎች ስለመገደሉ የድምጽ ማስረጃ አለን ብለው ነበር።

ሳዑዲ ግን በተደጋጋሚ ጀማል ወደ ቆንስላው ከገባ ከደቂቃዎች በኋላ ቆንስላውን ለቅቆ ወጥቷል ብትልም በመጨረሻ ግን መገደሉን አምናለች።

ጀማል በሳዑዲ ዝነኛ ጋዜጠኛ ነበር፤ የሶቪየት ሕብረት የአፍጋኒስታን ወረራን በዝርዝር ዘግቧል። እንደ ኦሳማ ቢንላደን ከመሳሰሉ ግለሰቦች ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጓል።

ለበርካታ አስርት ዓመታት ለሳዑዲ ንጉሳውያን ቤተሰብ የቅርብ ሰው ነበር፤ የሳዑዲ መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን አማካሪ ሆኖም ሰርቷል።

ባለፈው ዓመት ግን ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሃገር ጥሎ ወደ አሜሪካ ተሰደደ።

አሜሪካም ሆኖ የዋሽንግተን ፖስት አምደኛ ሆነ። በጽሑፎቹ የሳዑዲ አረቢያውን ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማንን ይተች ነበር።

የካፒታል ጋዜጣ ራተኞች

ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ የታጠቁ ሰዎች ወደ ጋዜጣው መስሪያ ቤት በመግባት አምስት ጋዜጠኞችን ተኩሰው ገድለው ነበር።

ተጠርጣሪዎቹ በአውሮፓውያኑ 2012 ጋዜጣው የስም ጥፋት ዘመቻ ከፍቶብናል ብለው ፍርድ ቤት ቢከሱትም ተሸንፈው የነበረ ሲሆን፤ ጥቃቱን በመፈጸም የቂም በቀል ስራ ማከናወናቸውን መርማሪዎች ተናግረዋል።

በወቅቱ ህይወታቸው የተረፈው ጋዜጠኞች በመኪና ማቆሚያና መኪኖቻቸው ውስጥ በመሆን በነጋታው የሚወጣውን ዕትም ሲያዘጋጁ ውለው ነበር።

የካፒታል ጋዜጣ ሰራተኞች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የቀድሞዋ የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ማሪያ ሪሳ ፊሊፒንስ ውስጥ የራሷን የዜና ተቋም በመመስረት የተለያዩ በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ የተመሰረቱ ጉዳዮችን ትዘግብ ነበር።

በእሷ የሚመራው 'ራፕለር' የተባለው የዜና አውታር የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴ የጸረ አደንዛዥ ዕጽ ዘመቻቸውን ለማጠናከር ያለአግባብ ሃይል መጠቀማቸውን የሚገልጽ ዝርዝር ይዞ ወጣ።

በዚህም ምክንያት በእሷና ሰራተኞቿ ላይ ከፍተኛ እንግልትና ማስፈራራት ደርሶባቸው ነበር።

በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ሌሎቹ ጋዜጠኞች ደግሞ ዋ ሎን እና ክያው ሶ ሲሆኑ ሁለቱም ከሚያንማር ነው የተገኙት።

የሃገሪቱን ሚስጥር አባክናችኋል የሚል ክስ ቀርቦባቸውም የሰባት ዓመታት እስር ተፈርዶባቸዋል።

ጋዜጠኞቹ እያደረጉት በነበረው የምረመራ ጋዜጠኝነት ስራ ወቅት 10 የሮሂንጂያ ሰዎች በመንግስት ወታደሮች መገደላቸውን የሚያሳይ መረጃ አግኝተው ነበር።

በፈረንጆቹ 2017 በቁጥጥር ስር የዋሉት ጋዘጠኞች እስከመጨረሻው ድረስ ጥፋተኛ እንዳልሆኑ ተከራክረዋል።