በሳተላይቶች ዙርያ ማወቅ የሚገባዎ ሰባት አስደናቂ እውነታዎች

ሮኬት ሳተላይት በማምጠቅ ላይ

የፎቶው ባለመብት, BRUCE WEAVER

በመሬት ዙርያ የሚሾሩ ሳተላይቶች ቁጥራቸው ስንት ይደርስ ይሆን? ደግሞስ እርስ በርስ እንዴት አይጋጩም? ደግሞስ እንዴት ወደ መሬት አይፈጠፈጡም?

ከሰሞኑ በአንድ ጊዜ 64 ሳተላይቶችን የማምጠቅ ሐሳብ ተወጥኗል።

ይህ የተወጠነው በደቡብ አፍሪካዊው ባለጸጋ ኢለን ማስከ አማካኝነት ሲሆን «ስፔስ ኤክስ ኤሮስፔስ» ደግሞ ኩባንያው ነው።

በቅርቡ የሚመጥቀው ፋልከን 9 ሮኬት ታሪካዊ የሆነውም ለዚሁ ነው። ከአሜሪካ ምድር የሚነሳው ይህ ሮኬት በአንድ ጉዞ ብቻ 64 ሳተላይቶችን ያመጥቃል።

እነዚህ በኅብረት እንዲመጥቁ የሚደረጉት 64 ሳተላይቶች ከ34 ድርጅቶችና ከ17 አገራት የተሰበሰቡ ናቸው።

ሳተላይቶቹ የተለያየ መጠንና አገልግሎት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል። ለስልክ ግንኙነቶች፣ ለኢንተርኔትና በመርከቦች ላይ የሚፈጸሙ የባሕር ላይ ወንጀሎችን ለመከታተል እንዲያገለግሉ የታሰቡም ይገኙበታል።

ለመሆኑ ስንት ሳተላይቶች ሕዋ ላይ እንዳሉ ይታወቃል? ደግሞስ ማንም ተነስቶ ወደ ሕዋ ሊያመጥቃቸው ይችላል? ወይስ ፍቃድ ያሻል? ፍቃድ ካስፈለገ ፍቃድ ሰጪው ማን ነው? ሳተላይቶች እርስበርስ ሊላተሙ የሚችሉበት አጋጣሚስ ይኖር ይሆን?

ለመኾኑ በመሬት ምህዋር የሚዘዋወሩ ሰው ሰራሽ ሳተላይቶች ስንት ይሆናሉ ብለው ይገምታሉ? መቶ? ሺህ? 10ሺህ?

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአውተር ስፔስ ጉዳዮች ቢሮ UNOOSA እንደተገለጸው ዛሬ ላይ ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ ሳተላይቶች ይገኛሉ። ቁጥሩን በትክክል ለማስቀመጥ ያህል 4921 ሳተላይቶች ምድርን እየተሽከረከሩ ነው።

ነገር ግን ሁሉም በሥራ ላይ ናቸው ማለት አይደለም።

ከሥራ ውጭ የሆኑት 2600 ሲሆኑ በሕዋ ላይ እነዚህን ሳተላይቶች ጨምሮ 17ሺህ የሚጠጉ የተለያዩ ሳተላይት ያልሆኑ መሣሪያዎች ይገኛሉ ይላል በደቡብ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሕዋ ተመራማሪው ዴቪድ ባርን ሀት። እነዚህ ቁሳቁሶች በድምሩ 7600 ቶን ይመዝናሉ።

ሁሉም የሚገኙት ታዲያ ከመሬት እስከ 35 ሺህ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ነው።

በሳተላይቶች ዙርያ 7 አስደናቂ እውነታዎች

የፎቶው ባለመብት, Handout

1. የሳተላይቶቹ መጠን ምን ያህል ነው?

ሳተላይትን ስናስብ መጀመርያ ወደ አእምሯችን የሚመጣው እጅግ ግዙፍና እጅግ ከባድ ከሆኑ ቁሳቁሶች የተሠራ በጣም ትልቅ ቁስ ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን ሁሉም ሳተላይቶች እንደዚያ አይደሉም።

መጠናቸውም ቢሆን ይለያያል። ትንሽ የዳቦ ቅርጫት ከሚያክሉት አንስቶ የከተማ አውቶቡስ እስከሚያህሉት ድረስ አሉ። አንድ መለስተኛ የእግር ኳስ ሜዳ የሚያክሉ ሳተላይቶችም ይገኛሉ።

2. ሳተላይት አገልግሎቱ ምንድነው?

ሁሉም ሳተላይቶች ወደ ምድር አጎንብሰው የመሬት አካልን ፎቶ የሚያነሱ አይደሉም። ዘርፈ ብዙ አገልግሎትን ይሰጣሉ።

የኮሚኒኬሽን ሥራ አንዱ ነው። የስልክ ግንኙነትን፣ የዳታ ስርጭትን የምናገኘው በሳተላይቶች አማካኝነት ነው።

የመሬት ቅኝትና ምልከታን (የጂፒኤስ ሥርዓትን ይጨምራል) የምናውቀው ሳተላይቶች ስላሉ ነው።

የሕዋ ጥናትን እንዲሁም የፕላኔት ጥናትን የሚያካሄዱ መልከ ብዙ ሳተላይቶችም ይገኛሉ።

ነገ አዲስ አበባ ይዘንብ ይሆን ወይስ ደመናማ ይሆናል ለማለት የሳተላይት ምስሎች ያስፈልጉናል። የባህር ወጀብን ሳይቀር ምስል አንስቶ የሚልከው ሳተላይት ነው።

የዓለማችን ሳንባ የሚባለው አማዞን ጫካ ውስጥ ምን ያህል ምንጣሮ እየተካሄደ እንደሆነ፣ ቻይና በረሃ ውስጥ አፈናና ግድያ የሚፈጸምበት ማጎርያ እየተገነባ ይሁን አይሁን ሳተላይቶች ፍንጭ ያቀብሉናል።

በቤታችን ቁጭ ብለን የምንኮመኩማቸው የቴሌቪዥን ስርጭቶችና የራዲዮ ሞገዶች የሳተላይት እገዛን የሚሹ ሊሆኑ ይችላሉ።

3. እንዴት ነው ሳተላይት በምህዋሩ መቆየት የሚችለው?

ሳተላይቶች በምድር ዙርያ ሊሾሩ የሚችሉት የመሬት ስበትን ለመቋቋም በሚያስችል ፍጥነት ላይ እንዲሆኑ ስለተደረጉ ነው። አለበለዚያ ወደ መሬት ይወድቁ ነበር።

ይህን ለመረዳት ትንሽ ውስብስብ ቢሆንም በቀላሉ አንድ መድፍ በከፍተኛ ጉልበት በ180 ዲግሪ ቢተኮስ መሬት ላይ ከመውደቁ በፊት በሆነ አቅጣጫ የተወሰኑ ርቀቶችን ይጓዛል። ወደ መሬት የመውደቅ ርቀቱ የሚወሰነው በሚኖረው የፍጥነት ጉልበት ነው።

ሳተላይቶችም ለመሬት ስበት እጅ የማይሰጡበት ምክንያት ፍጥነታቸው ነው።

ሳተላይት

የፎቶው ባለመብት, NASA

4. የሳተላይቶችን ዕድሜ ምን ያህል ነው?

ሮኬቶች ሳተላይትን ጭነው ወደ ሕዋ ያመጥቁና ለሳተላይቱ ከተሰናዳለት ቦታ ያኖሩታል። የተስተካከለ ርቀቱን እስኪያገኝ ወራትን ሊወስድ ይችላል። በመጨረሻም ሳተላይቱን በምህዋሩ ላይ ይቀመጣል።

ሳተላይቱ ተሸክሞት ከሄደው ሮኬት ቀስ በቀስ በሚለያይበት ወቅት የሚኖረው ፍጥነት በመሬት ዙርያ ለመቶ ዓመት መሽከርከር ያስችለዋል ይላሉ ባለሞያዎች።

ዋናው ሳተላይት በሕዋ ላይ እንዲቆይ የሚያደርገው ምስጢር የመሳሳብ ፊዚክስ ሲሆን በመሬት ስበት እንዳይወድቅ የሚያግደው ብቸኛው ጉዳይ የእሽክርክሪት ፍጥነቱ ነው።

ለዚያም ነው ከመሬት በቅርብ ርቀት የሚገኙት ሳተላይቶች የሚሾሩበት ፍጥነት ከመሬት ራቅ ብለው ከሚገኙት ይልቅ ፈጣን የሆነው።

ሳተላይቶች የእሽክርክሪት ምህዋራቸውን መለወጥ ቢያስፈልግ እና እርስበርስም እንዳይጋጩ እንዲረዳ የየራሳቸውን ነዳጅ ተጭኖላቸዋል።

ሳተላይቶች ከ5 እስከ 15 ዓመታት አገልግሎት ላይ ሊቆዩ ይችላሉ። ዕድሜያቸው ግን በሚሰጡት አገልግሎትና በሚታጠቁት የነዳጅ መጠን ይለያያል።

5. ሳተላይቶች ሊጋጩ ይችላሉ?

ሊጋጩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ የሚሆን ነገር አይደለም። ምክንያቱም የሚሾሩበት መስመር ከመለያየቱም ባሻገር ሕዋ እጅግ ሰፊ አካል መሆኑ ግጭት እንዳይኖር ያደርጋል።

ይህ ማለት ግን ግጭት በፍጹም አይከሰትም ማለት አይደለም። በአሁኑ ጊዜ እጅግ በርካታ ሳተላይቶችን የማምጠቅ ዕቅድ መኖሩ ሲታይ ግጭት የመከሰቱ ዕድል ዜሮ ነው ማለት አይቻልም።

በየካቲት፣ 2009 አንድ የአሜሪካና አንድ የራሺያ ሳተላይቶች ተላትመው ያውቃሉ። ይህ በታሪክ የተመዘገበ የመጀመርያው የሳተላይቶች ግጭት ነው።

ሳተላይት ጣቢያ

የፎቶው ባለመብት, Yuri Smityuk

6. ሳተላይቶችን ማን ነው የሚቆጣጠራቸው?

ሳተላይቶች በድርጅቶች ወይም በኩባንያዎች ወይም በመንግሥት አንዳንድ ጊዜም በግለሰቦች ባለቤትነት ሊያዙ ይችላሉ።

በ1967 በተደረገው የአውተር ስፔስ ስምምነት መሠረት እያንዳንዱ ሳተላይት ያመጠቀ አገር የተወሰነ የመቆጣጠር ሥልጣን እንዲኖረው የተደረገው የሬዲዮ ልውውጥ መጠላለፍን ለማስቀረት ጭምር ነው።

በአሜሪካ ለምሳሌ የግል ኩባንያዎች በስፔስ አገልግሎት ላይ ለመሰማራት መጀመርያ ከፌዴራል መንግሥት ፍቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

ለኮሚኒኬሽንና ቴሌኮም ሳተላይት ግንኙነት ለማድረግ ከፌዴራል ኮሚኒኬሽን ኮሚሽን ፍቃድ መውሰድ ግድ ነው። ሳተላይትን ወደ ሕዋ ለማምጠቅ ደግሞ የፌዴራል አቪየሽን አስተዳደርን ፍቃድ ማግኘት ያሻል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ የተባበሩት መነግሥታት ድርጅት የአውተር ስፔስ ጉዳዮች በእንግሊዝኛ ምህጻሩ UNOOSA የሚባለው ኃላፊ መሥሪያ ቤት ነው። በሕዋ ጉዳዮች ዙርያ ሕግ ያረቃል ይቆጣጠራል።

7. ማንም ሳተላይት ወደ ሕዋ ማምጠቅ ይችላል?

አዎ! ዛሬ ማንኛውም ሰው ሳተላይትን ወደ ሕዋ ማምጠቅ የሚችለበት ደረጃ ተደርሷል። የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሳይቀሩ ሳተላይት ገንብተው በማምጠቅ ፕሮግራማቸውን ከሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ጋር ይጋራሉ።

ከመቼውም ጊዜ በላይ የንግድ ኩባንያዎች ሳተላይት የሚያመጥቁበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ኾኖም ከፍ ያለ በጀት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ይህ የሳተላይት ኢንዱስትሪም በቢሊዮን ዶላር ይገመታል።