የሃምዛ ሃሚድ ፈጠራ የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነቱ ሊጠበቅለት ነው

ሃምዛ ሃሚድ በውድድሩ ጊዜ አሸናፊ በሆነበት ጊዜ የተነሳው ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Girma Worku

ገና የ3ኛ እና የ4ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ጊዜ በፈጠራ ሥራዎች ቀልቡ መሳብ እንደጀመረና ከኤሌክትሪክ የተገናኙ ነገሮችን መስራት ያስደስተው እንደነበር ያስታውሳል - የ18 ዓመት ወጣቱ ሃምዛ ሃሚድ።

ሃምዛ በፈጠራ ሥራው ብቻ ሳይሆን በቀለም ትምህርቱም ጥሩ ውጤት ከሚያስመዘግቡ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነው፤ ፊዚክስና ሒሳብም አብዝቶ የሚወዳቸው የትምህርት ዓይነቶች ናቸው።

የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ አስተማሪያቸው 'የፈጠራ ሥራ የሠራ ይበረታታል' ሲሉ ማስታወቂያ ያስተላልፋሉ።

ሥራውን ለማሳየት ዕድሉን ለመጠቀም የፈለገው ሃምዛ የትራፊክ መቆጣጠሪያ መብራት ሠራ፤ ነገር ግን ሥራው የመጀመሪያው በመሆኑ በራስ መተማመን አልሰጠውም። እየፈራ እየተባ ፈጠራውን የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በተገኙበት አቀረበ።

ያኔ ታዲያ ፊቱን በደስታ ብርሃን ያፈካ ያልጠበቀውን ምላሽ አገኘ። በሥራው ከመደነቃቸው የተነሳም ተማሪዎች በተሰበሰቡበት የአንድ 'ቢክ' እስክርቢቶ ሽልማት ተበረከተለት። ደስታው ወደር አልነበረውም፤ የልጅነት ልቡ ዳንኪራ ረገጠች።

የትራፊክ መብራቱ (ፈጠራው) ሰዎች የተሽከርካሪ አደጋ እንዳይገጥማቸው የሚያስተምር ቅርፅ (ሞዴል) ነበር። እርሱ እንደሚለው ከዚያ በኋላ ድፍረትንም ድልንም ደጋግሞ መቀዳጀት ጀመረ።

የ4ኛ ክፍል ተማሪ እያለ በአስተማሪው ድጋፍ ራዲዮ ላይ የሚገጠም ድምጽ ማጉያ (ስፒከር) ሰርቶ በመወዳደር የሁለተኛነት ደረጃን አግኝቷል።

ሃምዛ 20 የሚሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን በተለያየ ጊዜ አቅርቧል። የሻይ ማሽን፣ ጤፍን በመስመር ለመዝራት የሚያስችል መሣሪያ እንዲሁም ሻማ ከቀለጠ በኋላ እንደገና ተመልሶ አገልግሎት የሚያስገኝ መሣሪያ ሰርቶ ለዕይታ አቅርቧል።

የሚማርበትን ትምህርት ቤት ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችልና አርፋጅ ተማሪን በዘመናዊ አሠራር የሚቆጣጠር ማሽን እና ዘመናዊ የአስተያየት መስጫ ሳጥን እንደሰራም ይናገራል።

ኔት ወርክና ገንዘብ የማያስፈልገው ስልክ የፈጠረ ሲሆን የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር ካሉበት ሆነው ስብሰባ ማካሄድ የሚያስችል ነው። እነዚህ የፈጠራ ሥራዎቹ ከብዙው በጥቂቱ ያውም በጥቅሉ የተገለጹ መሆናቸውን ግን አስምሮበታል - ሃምዛ።

ሃምዛ ሃሚድ በውድድሩ ጊዜ አሸናፊ በሆነበት ጊዜ የተነሳው ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, University of Gonder

ገመድ አልባው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ (Wi-power)

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካልና ኮምፒዩተር ምህንድስና የአንደኛ ዓመት ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኘው ሃምዛ የአልበርት አንስታይንና የቶማስ ኤድሰንን የሕይወት ታሪኮችና ሥራዎች ማንበብ ያዘወትራል።

በኢትዮጵያ የሚታዩ ችግሮችን በፈጠራ ሥራዎቹ የመፍታት ህልም አንግቧል። እርሱ እንደሚለው ለዚህ የፈጠራ ሥራው ተወልዶ ባደገበት ጃን አሞራ ያለው የኃይል መቆራረጥ እንዳነሳሳው ይገልፃል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት አቶ ሰለሞን መስፍን፤ ሃምዛ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ሳለ ሥራዎቹን ይከታተሉ እንደነበር ይናገራሉ። አመርቂ ውጤት በማስመዝገብም ዩኒቨርሲቲውን ሊቀላቀል ችሏል።

አቶ ሰለሞን የእርሱ ፈጠራዎች አካል የሆኑት ገመድ አልባ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያና ገመድ አልባ የኢንተርኔት አገልግሎት በዩኒቨርሲቲው እንደተሞከሩ ይገልጻሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የሳይንስ ቀን አስመልክቶ ለሦስተኛ ጊዜ በተከበረው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አገር አቀፍ ውድድር ላይ ገመድ አልባው የኢንተርኔት አገልግሎት (Signal Wi Fi) ፈጠራው ሁለተኛ ደረጃን አግኝቶ ሽልማት ተበርክቶለታል።

ይሁን እንጂ ገመድ አልባው የኤሌክትሪክ ኃይል (Wi power) ከሥራዎቹ ሁሉ አዲስና ተሰምቶ የማይታወቅ በመሆኑ የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ስለ ሥራው በዝርዝር መግለፅ እንደማይፈልጉ አቶ ሰለሞን ጨምረው ተናግረዋል።

"የኤሌክትሪክን ኃይል ያለ ገመድ ማስተላለፍ የማይታመን ነገር ነው" የሚሉት አቶ ሰለሞን በዩኒቨርሲቲው 60 ሜትር ርቀት ላይ እንደተሞከረና ያለምንም የገመድ ማስተላለፊያ አምፖል ማብራት እንደተቻለ በዐይናቸው መታዘባቸውን ግን አልሸሸጉንም።

ከዚህ ቀደም በግሉ ባደረገው ሙከራ ኃይሉ በሚተላለፍበት አቅጣጫ ሰዎች ሲሻገሩ ንዝረት ይፈጥር እንደነበርና ያ ችግር ግን አሁን መስተካከሉን ከራሱ ከሃምዛ መስማታቸውን ገልፀውልናል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መለያ

የፎቶው ባለመብት, University of Gonder FB

"የፈጠራ ራውን በአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት ለማስመዝገብ እየተራ ነው"

ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ከዚህ ቀደም ዣንጥላዎችን እንዲሁም በኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን በመጠገን ከሚያገኘው ገንዘብ ለፈጠራ ሥራው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ያሟላ ነበር።

አንዳንዴም በኤሌክትሮኒክስ ንግድ የተሰማሩ የአካባቢው ነጋዴዎች የሚያስወግዷቸውን ቁርጥራጮችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ይለግሱታል። አንዳንዴም በርካሽ ይሸጡለታል።

ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ ግን ይህ የቀረለት ይመስላል። በዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ሥራ ማዕከልና ቤተ ሙከራዎች እንዲጠቀም፣ መምህራንም በቅርብ እንዲያግዙትና የሚያስፈልገው ነገር እንዲሟላለት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አቶ ሰለሞን ነግረውናል።

ዩኒቨርሲቲውም ተጓዳኝ የሆኑ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት፣ እያንዳንዱን የፈጠራ ሥራዎች እንደ አንድ ፕሮጀክት በመውሰድ በጥናት እንዲሠሩ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸውልናል።

ዩኒቨርሲቲው ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እንደ ሃምዛ ያሉ በፈጠራ ሥራ የተሠማሩ ወጣቶችን በማገዝ እየሠራ ይገኛል።

ተማሪው የጊዜም ሆነ የሌላ ጫና እንዳይገጥመው የፈጠራ ሥራ ውጤቶቹን ቀስ በቀስ ተግባራዊ እንዲደረጉና በጥናት ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ እየሠሩ ነው። በዚህም መሰረት ዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ሥራው በአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት እንዲመዘገብ ማድረግ ቅድሚያ የሰጠው ጉዳይ ሆኗል።

ፈጠራውን ለማስመዝገብም በሂደት ላይ እንደሚገኙ አቶ ሰለሞን ለቢቢሲ ገልጸዋል።