የአልበርት አንስታይን ደብዳቤ በ84 ሚሊዮን ብር ተሽጧል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አልበርት አንስታይን የከተበው ደብዳቤ ከግምቶች ሁሉ ልቆ በ2.9 ሚሊዮን ዶላር (84 ሚሊዮን ብር ገደማ) ሊሸጥ ችሏል።
በፈረንጆቹ 1954 ላይ የተጻፈው እና ''ጎድ ሌተር'' ተብሎ የሚታወቀው አንስታይን የጻፈው ደብዳቤ ኒውዮርክ ላይ በተካሄደው ጨረታ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል ተብሎ ተገምቶ ነበረ።
በወቅቱ የ74 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ የነበረው የኖቤል ሽልማት አሸናፊው አንስታይን ይህን ባለ አንድ ገጽ ከግማሽ ደብዳቤ የጻፈው ለጀርመናዊው ፈላስፋ ኤሪክ ጉትኪንድ ስራ ምላሽ በማለት ነበር።
ጽሑፉ በሃይማኖት እና ሳይንስ መካከል ስላለው ክርክር መሰረት ጥሎ ያለፈ ሃሳብ ነው ይባልለታል።
ይህ ግልጽ እና ግላዊ ደብዳቤ የተጻፈው አንስታይን ከመሞቱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ የነበረው ሲሆን አንስታይን በሳይንስ እና ሃይማኖት ዙሪያ ያለውን አመለካከት በግልጽ ያሰፈረበት ተደርጎ ይወሰዳል።
ደብዳቤው የተሸጠበት ዋጋ ከተጠበቀው በእጥፍ በልጦ ተገኝቷል።
የአፍ መፍቻ ቋንቋው በሆነው በጀርመንኛ የተጻፈው ይህ ደብዳቤ በፈጣሪ ስለማመን ጉዳይ ያብራራል።
''ፈጣሪ ለእኔ ምንም ነው፤ የሰው ልጆች ድክመት መገለጫ እንጂ'' ሲል ጽፏል፤ ''መጽሐፍ ቅዱስ ማለት የቅዱሳን ስብስበ ነው፤ እኚህ ቅዱሳን ግን ጥንታዊያን ናቸው'' ሲልም ያክላል።
''ምንም አይነት ትርጓሜ ቢሰጠው፤ ምንም ያክል አሳማኝ ቢሆን፤ [ለእኔ] ስለ ጉዳዩ የሚለውጠው ነገር የለም'' በማለት ይቀጥላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በራሱ አይሁዳዊ ማንነትም ላይም ''እንደ ሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ ጥንታዊ እና ፍርሃት ላይ የተመሠረተ እምነት ነው'' ሲል ጽፏል።
የአንስታይን የእጅ ፅሁፍ ለጨረታ ሲቀርብ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ባለፈው ዓመት አንስታይን ሊያገኘው ፍቃደኛ ላልሆነ ለአንድ ጣሊያናዊ የኬሚስትሪ ተማሪ የጻፈው ደብዳቤ 6100 ዶላር ተሽጧል።
2017 ላይ አንስታይን ደስተኛ ህይወት እንዴት መምራት እንደሚቻል ምክር የሰጠበት ጽሑፍ 1.56 ሚሊዮን ዶላር መሸጡም የሚዘነጋ አይደለም።
በዚህ ደብዳቤ ላይ ''የተረጋጋ ህይወት መምራት ብዙ ደስታ ይሰጣል፤ ስኬትን ማሰስ ግን እረፍት ማጣት ነው" የሚል ምክር ጣል ያደርጋል።













