የሁዋዌ ባለቤት ልጅ ካናዳ ውስጥ ታሠረች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የቻይናው ቴሌኮም ኩባንያ ሁዋዌ ባለቤት ሴት ልጅ ካናዳ ውስጥ ለእሥር ተዳርጋለች፤ ወደ አሜሪካ ልትላክ እንደምትችልም እየተነገረ ነው።
ከጥቂት ቀናት በፊት ነበረ ሜንግ ዋንዦ፤ የሁዋዌ ባለቤት ሴት ልጅ እና የሁዋዌ ምክትል ኃላፊ በካናዳዋ ቫንኮቨር ከተማ በቁጥጥር ሥር የዋለችው።
ሜንግ የታሠረችበት ምክንያት ግልፅ ባይሆንም አሜሪካ ሁዋዌ የተሰኘውን ኩባንያ ከኢራን ጋር በተያያዘ ጉዳይ እየመረመረች እንደሆነ ተነግሯል።
በካናዳ የቻይና ኤምባሲ እሥሩ ህጋዊ አይደለም በሚል ሜንግ ዋንዦ በፍጥነት እንድትፈታ ጠይቋል።
ኩባንያው ስለጉዳዩ ብዙም የሚያውቀው መረጃ እንደሌለ በመጠቆም ምክትል ኃላፊዋ ግን ምንም ዓይነት እኩይ ተግባር እንደሌለባቸው ጠቁሟል።
ጉዳዩ አሜሪካ እና ቻይና ንግድ በተመለከተ ከገበቡት እሰጥ-አገባ አንፃር ውጥረት እንዲነግስ አድርጓል እየተባለ ነው።
ምክትል ኃላፊዋ ለአሜሪካ ተላልፈው ሊሰጡ እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጠው የካናዳ ፍትህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በዋስትና ጉዳይ ብይን ለመስጠት ለዕለተ አርብ የፍርድ ቤት ቀጠሮ እንደተሰጠ አሳውቋል።
አሜሪካ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ሁዋዌ አሜሪካ ኢራን ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ሳይጥስ አልቀረምና ለዚህ ነው ምክትል ኃላፊዋ ለእሥር የተዳረጉት በማለት እየዘገቡ ይገኛሉ።
ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ኩባንያው አሜሪካ ኢራን ብቻ ላይ ሳይሆን ሰሜን ኮሪያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ሳይተላለፍ አልቀረም ሲል ዘግቧል።
የአሜሪካ ሕግ አርቃቂዎችም ኩባንያው ለሃገራችን ደህንነት ስጋት ነው በማለት በተደጋጋሚ ሲከራከሩ ይደመጣሉ።
የሁዋዌ ፈጣሪ ሬን ዤንገፌይ ሴት ልጅ ሜንግ ዋንዦ ካናዳ እንደመሸጋገሪያ ተጠቅማ ወደሶስተኛ ሃገር ለመብረር እየተዘጋጀች ሳለ ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለችው።
አሜሪካ፤ ኢራን የኑክሊዬር ጦር መሣሪያ እያብላለቸው ነው በማለት ማዕቀብ መጣሏ የሚዘነጋ አይደለም፤ ከማዕቀቦቹ አንዱ ደግሞ ምጣኔ ሃብታዊ ነው። ሁዋዌ የተሰኘው ግዙፍ የቻይና ኩባንያ ይህንን በመተላለፍ በምስጢር ከኢራን ጋር ሳይሰራ አልቀረም።













