አይፎን አዲስ ስልኮችን እና ሰዓት ይዞ ብቅ ብሏል

የፎቶው ባለመብት, Apple
አፕል የተሰኘው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አይፎን ኤክስ ኤስ (iPhone XS) ብሎ የሰመየመውን ዘመናይ ስልክ እና የእጅ ሰዓት ለገበያ ይፋ አድርጓል።
አይፎን ኤክስኤስ ማክስ (iPhone XS Max) 6.5 ኢንች ወይም 16.5 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው ስክሪን ሲኖረው አይፎን ኤክስ ኤስ (iPhone XS) ደግሞ በ6.1 ኢንች ርዝማኔ ነው ወደ ገበያ የዘለቀው።
ከስልኩ ጋር ግንኙነት ያለው እጅ ሰዓትም ይፋ የሆነው በትላንትናው ዕለት ነው።
ከሌሎች የአይፎን ምርቶች ላቅ ባለ ሁኔታ አይፎን ኤክስ ኤስ (iPhone XS) ዋጋው ወደድ ይላል የተባለለት ይህ ስልክ ከ749 ዩሮ (26 ሺህ ብር ገደማ) ጀምሮ እስከ 1449 ዩሮ (52 ሺህ ብር) ለገበያ ቀርቧል።
ቢሆንም ምርቱ እንደጉድ ከመቸብቸብ ወደኋላ እንደማይል በዘርፉ ጥርስ የነቀሉ ባለሙያዎች እየተነበዩ ነው።
ስልኩ ባለገመድ የጆሮ ማዳመጫ የለውም። ተጠቃሚዎች ገመድ አልባ የጆሮ ማዳመጫ ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ ተጨማሪ 9 ዩሮ የምታስወጣ ቻርጅ ማድረጊያ ቦታ ላይ የምትሰካ ገመድ በመግዛት የጆሮ ማዳመጫ ገመዷ ላይ በመሰካት መጠቀም ይችላሉ።
የአይፎን ስልኮች አምራቹ አፕል ኩባንያ 1 ትሪሊየን ዶላር የገበያ ድርሻ በመያዝ ዓለም የመጀመሪያው ድርጅት ነው።
በስልኮች ሽያጭ ግን በሳምሰንግ እና በቻይናው ሁዋዌ ተበልጦ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።













