ፈረንሳይ 'አላሁ አክበር' ብሎ ተኩስ የከፈተውን ግለሰብ በማደን ላይ ናት

የገና በዓል ዝግጅት ባለባቸው ቦታዎች ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በምስራቃዊ ፈረንሳይ ከተማ ስትራስበርግ የአውሮፓውያንን ገና በዓል ምክንያት በማድረግ ማክሰኞ ምሽት ላይ እየተዝናኑ የነበሩ ሰዎች ላይ 'አላሁ አክበር ' ብሎ ተኩስ በመክፈት ሁለት ሰዎችን ገድሎ አስራ አንድ የሚሆኑትን ያቆሰለውን ግለሰብ ለመያዝ ፈረንሳይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን አሰማርታለች።

በመገናኛ ብዙሃን ቸሪፍ ቺካት ተብሎ በመጠራት ላይ ያለው ይህ ግለሰብ እስር ቤት በነበረበት ወቅት አክራሪ እንደሆነ ተገልጿል።

የፓሪስ ከተማ አቃቤ ህግ የሆኑት ሪሚ ሄትዝ እንደገለፁት ደግሞ ግለሰቡ የ29 ዓመት ወጣት ሲሆን ጥቃቱን የፈፀመበት ቦታ ላይ መሳሪያና ስለት ይዞ የነበረ ሲሆን ጥቃቱን ከፈፀመ በኋላ በታክሲ ከአካባቢው ተሰውሯል።

የታክሲ ሾፌሩም ግለሰቡ አስር ሰዎችን እንደገደለና ከወታደሮች ጋር ሲታኮስ መቁሰሉንም በኩራት እንደነገረው ለፖሊስ ቃሉን ሰጥቷል።

ጥቃቱ በተፈፀመ ምሽት ከግለሰቡ ጋር ግንኙት እንዳላቸው የተጠረጠሩ አራት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አቃቤ ህጉ አስታውቀዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የፀጥታ ሃይሎችን አሰማርተው ፍለጋውን እያካሄዱ ቢሆንም ምናልባትም ግለሰቡ ከፈረንሳይ ሳይወጣ እንዳልቀረ የፈረንሳይ ምክትል አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ሎረን ኑንዝ ቀደም ሲል ተናግረዋል።

የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ክሪስቶፍ ካስታነር በበኩላቸው ደግሞ የገና በዓል ዝግጅቶች በሚካሄድባቸው ቦታዎች እንዲሁም ድንበሮች ላይ ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገ እንዳለ ገልፀዋል።

የስትራስበርግ ከተማ ከንቲባ ሮናልድ ሪስ ዛሬ በገና በዓል የገበያ ስፍራዎች ዝግ እንደሚሆኑና በከተማዋ የስብሰባ ማዕከሎችም ሰንደቅ አላማ ዝቅ እንደሚል ተናግረው ነበር።