ሕንዳዊቷ ህፃን ሃኒፋ ዛራ በመፀዳጃ ቤት ምክንያት አባቷን ለፖሊስ ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, BBC Tamil
የ7 ዓመቷ ህንዳዊት አባቷ መፀዳጃ ቤት ሊሰራላት የገባላትን ቃል ባለመጠበቁ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በማምራት ክስ አቅርባለች።
ሃኒፋ ዛራ የተባለችው ይህች ሕፃን አባቷ "አታሎኛል፤ ስለዚህ መታሰር ይገባዋል" ስትል ለፖሊስ ደብዳቤ ፅፋለች። ምክንያቷ ደግሞ በመኖሪያ ቤታቸው ምቹ የሆነ መፀዳጃ ቤት ባለመኖሩ ደጅ ሰዎች እያዩኝ መፀዳዳት ያሳፍረኛል ብላለች።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ሪፖርት አብዛኞቹ የህንድ ዜጎች መፀዳጃ ቤት የሌላቸው ሲሆን 500 ሚሊዮን የሚሆኑት በግላጭ ቦታዎች ለመፀዳዳት ይገደዳሉ።
በተቃራኒው በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ መፀዳጃ ቤቶች የተገነቡ ቢሆንም በአግባቡ አይጠቀሙባቸውም።
በህንድ ምዕራባዊ ግዛት በሆነችው አምቡራ ከቤተሰቦቿ ጋር የምትኖረው ሃኒፋ ሳትሸማቀቅ የምትጠቀምበት መፀዳጃ ቤት ኖሯት አያውቅም።
ሃኒፋ ለቢቢሲ እንደተናገረችው፤ ጎረቤቶቿ መፀዳጃ ቤት ስላላቸው እነሱም መፀዳጃ ቤት እንዲኖራቸው ደጋግማ አባቷ እንዲገነባላት ትጠይቀው ነበር። ይህንን ጥያቄ ስታቀርብ የመዋለ ህፃናት ተማሪ ነበረች።
"ደጅ ወጥቼ ስጠቀም በጣም ነው የማፍረው፤ ሰዎች አተኩረው ሲያዩኝም ጥሩ ስሜት አይሰማኝም" የምትለው ሃኒፋ በተለይ ትምህርት ቤት ንፅህናው ባልተጠበቀ ቦታ መፀዳዳት ስለሚያስከትላቸው የጤና ችግሮች ትምህርት ካገኘች በኋላ ጥያቄውን ለማቅረብ እንደተነሳሳች ትናገራለች።
ለፖሊስ በፃፈችው ደብዳቤ ላይ እንደገለፀችው በትምህርቷ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ከቻለች መፀዳጃ ቤት እንደሚገነባላት አባቷ ቃል ገብቶላት ነበር።
አሁን የሁለተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሃኒፋ ከመዋለ ሕፃናት ትምህርት ጀምሮ ከፍተኛ ውጤት ብታስመዘግብም፤ አባቷ የገባላት ቃል ተፈፃሚ ሊሆንላት አልቻለም። " እንሰራላን አታስቢ " የሚል መፅናኛ ብቻ እንደሚነግራት ታስረዳለች።
"በመሆኑም የአባቴ ተግባር ከማጭበርበርና ማታለል ያልተናነሰ በመሆኑ እሰሩት፤ የማታስሩት ከሆነ ግን ፖሊስ መፀዳጃ ቤቱን መቼ ሊሰራ እንደሚችል ገልፆ እንዲፈርም ማድረግ አለበት" ስትል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥታለች።

አባቷ ኢህሳኑላህ መፀዳጃ ቤቱን መገንባት የጀመሩ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ስራ ስለሌላቸው ለመጨረስ በቂ ገንዘብ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።
"ሃኒፋን ጊዜ እንድትሰጠኝ ጠይቄያታለሁ፤ ነገር ግን ቃሌን ልጠብቅ ባለመቻሌ ልታነጋግረኝ ፈቃደኛ አይደለችም" ብለዋል።
እርሷም በበኩሏ "እስከ መቼ መወትወት አለብኝ፤ ገንዘብ ሳይኖረው ፤ሁል ጊዜም ተማሳሳይ ነገር ነው የሚነግረኝ" ስትል ትሞግታለች። በዚህም ምክንያት ወደ ፖሊስ ለመሄድ እንደተገደደች ታስረዳለች።
ከዚያም ባለፈው ሰኞ ከእናቷ ማሃሪን ጋር በመሆን ከትምህርት ቤቷ አቅራቢያ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ አመሩ።
"በቦርሳዋ የያዘቻቸውን ደብዳቤና የትምህርት የምስክር ወረቀቷን ጠረጴዛ ላይ አስተካክላ አስቀመጠች፤ ከዚያም 'መፀዳጃ ቤት ልትሰጠኝ ትችላልህ?'" ስትል ጠየቀችኝ ይላል የፖሊስ ኃላፊው ቫላርማቲ።
ጥያቄዋን ያዳመጡት ፖሊሶች ለአባቷ ጥሪ ያቀርባሉ። "ሲነገረኝ በልጄና በባለቤቴ ላይ አንዳች አደጋ የደረሰባቸው ነበር የመሰልኝ'' ይላል የሃኒፋ አባት።
ምንም እንኳን ጉዳዩ በዚህ መልክ ወደ እርሱ ይመጣል ብሎ ባይገምትም ለመስሪያ ቤቶችና ለህግ አካላት እየከፈላ ሌላ ሰው ደብዳቤ የሚያፅፈው አባት ልጁ ለፖሊስ በፃፈችው ደብዳቤ መደነቁ አልቀረም ታዲያ።
በሃኒፋ ሐቀኛ ጥያቄ ልባቸው የተነካው የፖሊስ አባላትም ችላ ሳይሉ ችግሩን ለመፍታት ጥረት አድርገዋል።
የእርሷ ጥያቄ የአካባቢው ባለስልጣናት ሃኒፋ በምትገኝበት አካባቢ ከ 500 በላይ መፀዳጃ ቤት ለመገንባት ገንዘብ ለማሰባሰብ አቅደዋል።
በመሆኑም በትምህርት ቤት ልጆች ወላጆቻቸው በመኖሪያ ቤት መፀዳጃ ቤት እንዲገነቡላቸው እንዲጠይቁ ትምህርት ለመስጠት እንዳሰቡ ኮሚሽነር ኤስ ፓርታሳራቲይ አስረድተዋል።
መንግስትም በመጭው ዓመት እያንዳንዱ ቤተሰብ መፀዳጃ ቤት እንዲኖራቸው ያቀደ ቢሆንም እቅዱ ግን ችግር አላጣውም።
በቅርብ የተጠና ጥናት እንደሚያሳየው በገጠራማዋ ህንድ 89 በመቶ የሚሆኑት ህንዳውያን መፀዳጃ ቤትን ማፅዳት እንዲሁም በቅርባቸው እንዲገኝ አይፈልጉም።
ሃኒፋ ግን በጥያቄዋ ምክንያት ከአባቷ ጋር ለተከታታይ 10 ቀናት ተኮራርፈው ቢቆዩም ፖሊስ መካከላቸው ገብቶ እርቅ አውርዶላቸው በደስታ መተቃቀፍ ችለዋል።












