ኔታኒያሁ እስራኤል ውስጥ ስላሉ ኤርትራዊያን ከጠ/ሚ ዐብይ ጋር መወያየታቸውን ተናገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና ጠቅላይ ሚኒስርት ቤንያሚን ናታኒያሁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በቅርቡ ከኢትዮጵያው አቻቸው ጋር በተገናኙበት ወቅት ኤርትራዊያን ጥገኝነት ጠያቂዎችን በኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ ከእስራኤል ለማስወጣት "አዲስ ዕቅድ" እንዳላቸው እንደተናገሩ 'ዘ ታይምስ ኦፍ ኢዝራኤል' የተባለ ጋዜጣ ዘገበ።

መስከረም ሰባት ቀን ከተደረገው የእስራኤል ምክር ቤት ምርጫ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ለቅስቀሳ በሚል በሊክዊድ ፓርቲ የፌስቡክ ገጽ በወጣው ቪዲዮ ላይ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር መገናኘታቸውን በማስታወስ የተነጋገሩትን ይጠቅሳሉ።

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሃገራቸው ከኤርትራ ጋር ከአንድ ዓመት በፊት ስለደረሱት የሠላም ስምምነት በማንሳት መልካም አጋጣሚዎች እንደተፈጠሩ እንዳነሱላቸው ይናገራሉ።

ጋዜጣው እንደጠቀሰው "አዲስ በሆነ ፕሮጀክት አማካይነት ሰዎቹ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ ለመርዳት የሚያስችል ጥሩ መንገድ አለኝ" እንዳሏቸው ኔታኒያሁ ተናግረዋል።

ኔታኒያሁ አክለውም "ጠቅላይ ሚኒስትሩ [ዐብይ] ለመርዳት ያላቸው ፍላጎት ከዚህ በፊት ያላገኘነውን አጋጣሚ ይከፍትልናል" ብለዋል።

በአጭር ቪዲዮው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የፓርቲያቸው የምክር ቤት አባል ከሆነችውና ጸረ ስደተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ ከሆነችው ሜይ ጎላን ጋር ሲነጋገሩ ይታያሉ። በዚህ ወቅት ነው ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ስላደረጉት ውይይት ሲናገሩ የተደመጡት።

ቢቢሲ ቪዲዮውን አግኝቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ በእብራይስጥ የሚናገሩትን አስተርጉሞ ነበር። በዚህ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይም "መልካም ዜና አለ። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ በመጡበት ጊዜ እንደነገሩኝ 'ከኤርትራ ጋር ሠላም ማውረዳችንን ታውቃለህ፤ እኔም በጣም ዘመናዊ በሆኑ ፕሮጀክቶች አማካይነት ሰዎቹ በጣም ጥሩ በሆነ ሁኔታ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ ለማድረግ በሚያስችሉ መንገዶች ልረዳህ እችላለሁ' ብለውኛል" ብለው ሲናገሩ ይደመጣል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ አክለውም "በእርግጥም በአፍሪካ ውስጥ ትኩረትን እየሳበ ባለው፣ ይህ ወጣትና ከፍተኛ ፍላጎት ያለው መሪ፣ እኛን ለመርዳት ያለው ዝግጁነት እስካሁን ያላገኘነውን መልካም አጋጣሚን ይከፍትልናል" በማለት ሲናገሩ ይሰማሉ።

ጋዜጣው በዚህ ጉዳይ ላይ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠይቅም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

ቴል አቪቭ የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲም አስተያየት እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።

አንድ በቴል አቪቭ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ያለ ሰራተኛን በፌስቡክ በኩል ለጋዜጣው እንደነገረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በእስራኤል ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ስለኤርትራዊያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ እንዳልተነሳ ገልጸዋል።

"በውይይቱ ላይ ይህን ጉዳይ በተመለከተ የተነሳ ነገር የለም። ውይይቱ የሁለትዮሽ ግንኙነትን በተመለከተ ነበረ" ሲሉ የኤምባሲው ሰራተኛ የጽሁፍ መልስ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ጊዜ ከ23 ሺህ በላይ ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራዊያን እስራኤል ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፤ ከ16 ሺህ በላይ የሚሆኑት ይፋዊ የጥገኝነት ጥያቄን አቅርበዋል።

ከእነዚህም ውስጥ እስካሁን 13ቱ ብቻ ተቀባይነት ሲያገኙ ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጓል። የቀሪዎቹ ማመልከቻዎች እስካሁን ድረስ ምላሽ አላገኘም።