ተማሪውን የገደለው ታንዛንያዊው መምህር በስቅላት ሊቀጣ ነው

ታንዛኒያ ውስጥ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ተማሪውን በከባድ ሁኔታ ደብድቦ ለሞት ያበቃው መምህር በስቅላት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል።
ብይኑን ያስተላለፉት ዳኛ ላሜክ ምላቻ እንደተናገሩት የ51 ዓመቱ መምህር ሬስፒሸስ ምታዛንጊራ በዱላ የ14 ዓመት ታዳጊውን በተደጋጋሚ መትቶት ነበር።
ታዳጊውም ከደረሰበት ከባድ ጉዳት ማገገም ሳይችል ቀርቶ ህይወቱ አልፋለች። መምህሩ ታዳጊውን የደበደበው የአንዲት ሴት መምህርን የእጅ ቦርሳ ሰርቀሃል በሚል ምክንያት እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ተገልጿል።
በታንዛኒያ ህግ መሰረት ትምህርት ቤት ውስጥ አካላዊ ቅጣት የተከለከለ ሲሆን ቅጣቱ የሚፈቀድባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ግን አሉ።
በዚህም ወቅት ተማሪዋ ወይንም ተማሪው አራት ጊዜ እንዲገረፍ የሚፈቀድ ሲሆን የትምህርት ቤቱ ሃላፊ ወይም ሃላፊው ስልጣን የሰጠው መምህር ግን በቦታው መኖር አለበት ይላል።
ባለፈው ዓመት በኪቤታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ይማር የነበረው ታዳጊ ህይወት ማለፉ ሲሰማ ሃገር አቀፍ ተቃውሞና ቁጣ አስነስቶ ነበር። የታዳጊው ቤተሰቦችም ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ የልጃችንን ሬሳ አንቀብርም ብለው ነበር።
ምንም እንኳን መምህሩ የሞት ቅጣት ቢፈረድበትም ታንዛኒያ ከአውሮፓውያኑ 1994 ወዲህ ምንም አይነት የሞት ቅጣት አከናውና አታውቅም።
የእጅ ቦርሳዋ ተሰረቀባት የተባለችው መምህርም ክስ ቀርቦባት የነበረ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ምንም ጥፋት አልሰራችም ብሎ በነጻ አሰናብቷታል።













