የተማሪውን ልጅ አዝሎ ያስተማረው አሜሪካዊው መምህር አድናቆት ተቸረው

ፕሮፌሰር ናታን አሌክሳንደር

የፎቶው ባለመብት, Twitter/@Original_Vaughn

አንድ አሜሪካዊ የሂሳብ ፕሮፌሰር የተማሪውን ልጅ አዝሎ ማስተማሩ የማህበራዊ ሚዲያዎችን ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል።

አሳታ የተባለችው ህጻን አባት ዋይን ሄየር እንደተናገረው ሴት ልጁን የሚጠብቅለት ሰው በማጣቱ ነው ወደ ትምህርት ቤት አዝሎ ያመጣት። ነገር ግን ያልጠበቀው ነገር ተከሰተ።

አስተማሪው ፕሮፌሰር ናታን አሌክሳንደር እኔ ልጅህን አዝዬልህ አንተ ለምን ዘና ብለህ ትምህርትህን አትከታተልም አለው።

መምህሩ ከበድ ያለውን የሂሳብ ትምህርት ለተማሪዎቹ እያስረዳ ለ50 ደቂቃዎች ህጻኗን ሲያዝል አባቷ ደግሞ ጠረጴዛ ላይ አቀርቅሮ ማስታወሻ ይወስድ ነበር ተብሏል።

የ34 ዓመቱ ፕሮፌሰር ናታን 'በዘፊድ' ለተባለው የዜና ምንጭ እንደገለጸው እስካሁን ልጅ አልወለደም። ነገር ግን ህጻኗ ምንም ባለመረበሿ በጣም ጥሩ አባት እንዳስመሰለችው በደስታ ተውጦ ተናግሯል።

''ታለቅሳለች ብዬ ፈርቼ ነበር፤ እሷ ግን እኔ ማስተማሬን ስቀጥል በተረጋጋ መንፈስ ትከታተለኝ ነበር።'' ብሏል

የህጻኗ አባት በበኩሉ ''ሁሌም ቢሆን ልጄን ለመንከባከብ ስል ከክፍል በጊዜ እንደምወጣ ያስተዋለው መምህር ወደ ትምህርት ቤት ይዣት እንድመጣ ያበረታታኝ ነበር'' ብሏል።

ሁለት ስራዎችን ደርቦ የሚሰራው አባት የሙሉ ሰአት ተማሪም ነው። ከሁለቱ ስራዎቹና ከትመህርቱ ጊዜ በማሸጋሸግ ነበር ሴት ልጁን የሚንከባከበው። አሁን ግን ሌላው ቢቀር ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ የልጁ ጉዳይ የሚያሳስበው አይመስልም።

ፕሮፌሰር ናታን አሌክሳንደር ህጻኗን አዝሎ ሲያስተምር የሚያሳየወው ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ተከታታዮች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎለታል።

አንዳንዶች እንደውም በአሜሪካ መንግስት ህጻናት እንክብካቤ የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆኑ ማሳያ ሊሆን ይችላል እያሉ ነው።

ሌሎች ደግሞ የሰው ልጅ ምን ያህል ጥሩ ሆኖ እንደተፈጠረ ለመረዳት ይህንን ፎቶ መመልከት ብቻ በቂ ነው ብለዋል።