በጾታ እኩልነት የሚያምኑ ወንዶች የትኞቹ ናቸው. . .?

ወጣት አባት ሴት ልጁን ወደ ትምህርት ቤት ሲያደርስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተመራማሪዎች ደረስንበት ያሉት ድምዳሜ ሴት ልጅ ያላቸው ወጣት አባቶች በጾታ እኩልነት ያምናሉ፤ ያረጁና ያፈጁ አመለካከቶችንም ይቃወማሉ ብለዋል።

የሎንዶን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ባካሄደው በዚህ ጥናት መሠረት በጾታ እኩልነት ዙርያ የተንሸዋረረ አመለካከት የነበራቸው ወጣት አባቶች ሴት ልጅ ከወለዱ በኋላ የባሕሪ ለውጥ አምጥተዋል።

የባሕሪ ለውጡ ሴት ልጃቸው የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ስትጀምር በ8 በመቶ፣ 2ኛ ደረጃ ስትገባ ደግሞ በአማካይ በ11 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል።

ጥናቱ እንዴት ተሠራ?

በዚህ ጥናት ውስጥ የተካተቱት አባቶች ከ21 ዓመት በታች ሴት ልጅ ያላቸው ብቻ ናቸው። በጥናቱ 5 ሺህ የሚሆኑ አባቶች ተካፍለዋል። ሌሎች 6 ሺህ የሚሆኑ እናቶችም የጥናቱ አካል ነበሩ።

ወላጆቹ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችን የተጠየቁ ሲሆን "የሴትና የወንድ ሚና በቤት ውስጥ ምን መሆን አለበት?" በሚለው አመለካከት ላይ አስተያየታቸውን ተጠይቀዋል።

ለምሳሌ "ባል ሥራ ሠርቶ ገንዘብ ማምጣት፣ ሚስት ደግሞ ልጆችን መንከባከብና ምግብ ማብሰል" አለባቸው በሚለው ላይ ይስማሙ እንደሆን ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

በዚህና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች ዙርያ አባቶች የሰጡት መልስ በጊዜ ሂደት እየተቀየረ እንደመጣ ተነግሯል። "የሚስት ሚና በቤት ውስጥ መታጠር አለበት" የሚለው አመለካከት ሴት ልጆች በወለዱ ወንዶች ዙርያ ቀስ በቀስ እየተቀየረ መጥቷል።

የምርምሩ ውጤት

ተመራማሪዎች በጥናታቸው ማሳረጊያ ላይ ተረዳን እንዳሉት ከሆነ ጾታዊ አመለካከት በጊዜ ሂደት እየተለወጠ የሚመጣ መሆኑና በተለይም ወንዶች ሴት ልጅ ከወለዱ በኋላ በጾታ እኩልነት ዙርያ ያላቸው አመለካከት እየተሻሻለ እንደመጣ ተመላክቷል።

የጥናቱ ተባባሪ ደራሲ ጁሊያ ፍሊፕ "የባሕሪ ለውጥ በጊዜ ሂደት መኖሩ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ነው" ብላለች።