ለልጃቸው "ሂትለር" የሚል ስም የሰጡ እናትና አባት ተፈረደባቸው

አባትና ልጅ የናዚን ባንዲራ ይዘው የተነሱት ምሥል

የፎቶው ባለመብት, WEST MIDS POLICE

ክላውዲያ ፓታታ እና አዳም ቶማስ አፍቃሪ ናዚ የሆነው ሕገ ወጥ ፓርቲ አባላት ናቸው።

ለአዶልፍ ሂትለር ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ የሄዱበት ርቀት እንግሊዛዊያንን አስደንግጧል። የልጃቸውን የመሐል ስም "ሂትለር" ሲሉ ነው የሰየሙት።

አዳም 22 ዓመቱ ሲሆን ክላውዲያ ደግሞ 38 ዓመቷ ነው። የበርሚንግሐም ፍርድ ቤት ትናንት በሰጠው ብይን አባትና እናትን እያንዳንዳቸው በ6 ዓመት ጽኑ እስራት ቀጥቷቸዋል።

መኖርያ ቤታቸው በተበረበረበት ጊዜም የናዚ አርማ የሆነው "ስዋስቲካ" በብዛት ተገኝቷል።

"በድርጊታችሁ፣ ቤታችሁ በተገኙት ቁሳቁሶችም ሆነ ለልጃችሁ በሰጣችሁት ስያሜ ድርጊታችሁና ማንነታችሁ ጎልቶ ወጥቷል" ብለዋቸዋል የመሐል ዳኛው።

ሂትለር የሚል ስም የተሰጠው ብላቴና ወደፊት ምን ሊሰማው እንደሚችል ባይታወቅም ወላጅ እናቱ ልጇን የናዚ ሰላምታ ሳይቀር ታሰለጥነው ነበር ተብሏል።

የናዚ አልባሳትና የሕጻናት መጫወቻዎችም ቤት ውስጥ ተገኝተዋል።

ይኸው ፍርድ ቤት የአፍቃሪ ናዚ አባል ነበሩ ያላቸውን ሌሎች አባላትን በተመሳሳይ በእስራት የቀጣ ሲሆን ሕገ ወጥ ፓርቲያቸውንም አደገኛ ዓላማን ያነገበ ብሎታል።

ኬኬኬ የተሰኘ የናዚ ልብስ የለበሰ አባት

የፎቶው ባለመብት, WEST MIDLANDS POLICE/PA WIRE

ከነዚህ ፍቅረኛሞች ጋር ፍርድ ቤት የቆመው ዳንኤል ቦጉዋንቪክ የአፍቃሪ ናዚ ፓርቲን ስትራቴጂና ፕሮፓጋንዳ በማቀናበሩ ተከሶ በተመሳሳይ ስድስት ዓመት ቅጣት ተበይኖበታል።

ፍሌቸር የተባለው የፓርቲው አባል እጅግ አክራሪ ሲሉ ዳኛው የገሰጹት ሲሆን ቀጥለውም 6 ዓመት አከናንበውታል።

የቡድኑ የደኅንነት ጉዳዮች ኃላፊ የተባለው ራይኬ 5 ዓመት ከ10 ወር ተፈርዶበታል።

"ናሽናል አክሽን" የተባለው ይህ ሕገ ወጥ ቡድን በጀርመን የሚገኙ ማናቸውም ስደተኞች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ይፈልጋል። ቡድኑ በ2013 የተመሠረተ ሲሆን በ2016 በአሸባሪ ቡድንነት ተፈርጇል።

አውሮፓም በናዚ ዘመን ወደነበረው አስተዳደር እንድትመለስ ይፈልጋል።