በማርገዛቸው ከትምህርት ቤት የተባረሩት ተማሪዎች ተመረቁ

ታንዛኒያ ውስጥ ተማሪ እያሉ በማርገዛቸው የተነሳ ከትምህርት ቤት ተባረው የነበሩ ሴቶች ጡረታ በወጡ አንዲት መምህር ድጋፍ አማካይነት ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።
ከሁለት ዓመት በፊት የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ያረገዙ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት መባረር አለባቸው ብለው ከተናገሩ በኋላ በአገሪቱ እየተበራከተ የመጣው የታዳጊዎች እርግዝና ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የውዝግብ ርዕስ ሆኖ ነበር።
ማርቲና ሳይመን ሲያራ የተባሉት የ72 ዓመት ጡረተኛ መምህር በሰሜናዊ ታንዛኒያ በምትገኘው የአሩሳ ከተማ ውስጥ ለእናቶቹ በከፈቱት ትምህርት ቤት ውስጥ ለተባረሩት ተማሪዎች የመማር ዕድልን ፈጥረውላቸዋል።
ፋራጃ በተባለው ማዕከል ውስጥ ሴቶቹ የምግብ ዝግጅትና የልብስ ስፌት ሥልጠናዎችን የሚያገኙ ሲሆን ከሁሉ የበለጠው ደግሞ ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ በትኩረት እንዲከታተሉ ሥራዎቻቸውን የሚያሳዩበትና የሚሸጡበት ቦታም ተዘጋጅቶላቸዋል።
ከተማሪዎቹ መካከል አንዷ የሆነችውና የመንታ ልጆች እናት የሆነችው የ23 ዓመቷ ዴብራ ኢማኑኤል በ17 ዓመቷ በማርገዟ ቤተሰቦቿ ያባረሯት ሲሆን ከትምህርት ቤትም ተባራ ነበር።
"ልጆቼን ለማሳደግና ለማስተማር ገንዘብ የሚያስገኝልኝ የራሴ የሆነ ሥራ እጀምራለሁ" ስትል በምግብ ዝግጅት የተከታተለችውን ሥልጠና ጨርሳ ስትመረቅ ለቢቢሲ ተናግራለች።
የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደ አንድ ሥነ ሥርዓት ላይ "ካረገዛችሁ፤ አለቀላችሁ" በማለት ተማሪ ልጃገረዶችን ካስጠነቀቁ በኋላ ከፍተኛ ወቀሳና ትችት ቀርቦባቸው ነበር።
በወቅቱ ፕሬዝዳንቱ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ያለውን የአገሪቱን ሕግ ጠቅሰው ነበር። እንደ አውሮፓዊያኑ በ2002 የጸደቀው ሕግ ተማሪ ልጃገረዶች አርግዘው ከተገኙ ከትምህርት ቤት ማባረርን ይፈቅዳል።















