ኮሮናቫይረስ፡ ለመሆኑ ምን ያህል ነው መራራቅ ያለብን? 1 ሜትር? ወይስ 2?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ሰዎች ሁለት ሜትር መራራቅ አለባቸው የሚለውን መርህን ይደግፋሉ።
በተቃራኒው የሕዝብ እንደራሴዎቻቸውና የመስተንግዶ ዘርፉ ሠራተኞች ሁለት ሜትር ተራርቆ መሥራት የማይታሰብ ነው ይላሉ።
የአገሪቱ መንግሥት አማካሪዎች በበኩላቸው 1 ሜትር ብቻ መራራቅ ለበሽታው የመጋለጥ እድልን በአስር እጥፍ ይጨምራል ሲሉ ይከራከራሉ።
ታድያ ሰዎች ምን ያህል ነው መራራቅ ያለባቸው? አንድ ሜትር ወይስ ሁለት ሜትር?
ሳይንሱ ምን ይላል?
በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር በተቀራረብን ቁጥር ለበሽታው የመጋለጥ እድላችን እንደሚጨምር ሳይንስ ያስረዳል።
የዓለም ጤና ድርጅት የሚመክረው አንድ ሜትር መራራቅን ነው። አንዳንድ አገራት የሚተገብሩትም ይህንን መርህ ነው። በእርግጥ ዜጎቻቸው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርጉ ያስገድዳሉ።
በሰዎች መካከል ምን ያህል ርቀት መኖር አለበት? የሚለውን በተመለከተ የተለያዩ አገራት ያወጡትን መመሪያ እንመልከት፦
1 ሜትር መራራቅ- ቻይና፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ሆንክ ኮንግ፣ ሉቴኒያ፣ ሲንጋፖር
1.4 ሜትር መራራቅ- ደቡብ ኮርያ
1.5 ሜትር መራራቅ- አውስትራሊያ፣ ቤልጅየም፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ጣልያን፣ ኔዘርላንድስ፣ ፖርቹጋል
1.8 ሜትር መራራቅ- አሜሪካ
2 ሜትር መራራቅ- ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ስፔን
‘ዘ ላንሴት’ በተባለ የሕክምና መጽሔት ላይ የወጣ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ቢያንስ አንድ ሜትር ከሰዎች መራቅ ራስን ከበሽታው ለመከላከል ይረዳል።
አንድ ሜትር ከሰዎች ሲራቅ በቫይረሱ የመያዝ እድልን 13 በመቶ ይሆናል። ከአንድ ሜትር በላይ መራቅ ደግሞ ወደ 3 በመቶ ያወርደዋል።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት እስከ ሦስት ሜትር ድረስ ከሰው ጋር ያለን ርቀት በጨመረ ቁጥር የበሽታው ተጋላጭነት በግማሽ እየቀነሰ ይሄዳል።
አካላዊ ርቀት የመጠበቅ መርህ ከየት መጣ?
አካላዊ ርቀት የመጠበቅ መርህ በ1930ዎቹ የተሠራ ጥናትን የተመረኮዘ ነው።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ ስንስልና ስናስነጥስ የሚወጣው ፈሳሽ አየር ውስጥ ይተናል ወይም መሬት ላይ ይወድቃል።
ፈሳሹ ከአንድ እስከ ሁለት ሜትር ባለው ርቀት ነው የሚወድቀው። ሰዎች ሲስሉ ወይም ሲያስነጥሱ በሽታውን የሚያስተላልፉትም ለዚያ ነው።
በቫይረሱ የተያዘ ሰው የሳለባቸው (ወይም የነካቸው) ቁሳ ቁሶችን መንካትም ለበሽታው በግንባር ቀደምነት ያጋልጣል።

ቫይረሱ በአየር መጓጓዝ ይችላል?
በሽታው ከያዘው ሰው ጋር መቀራረብ ወይም በቫይረሱ የተያዘ ሰው የተጠቀመባቸውን ቁሳ ቁሶች ነክቶ ፊትን መንካት ለበሽታው ያጋልጣል።
አንዳንድ ተመራማሪዎች ኮሮናቫይረስ በጥቃቅን የፈሳሽ ቅንጣቶች (ኤሮሶልስ) አማካይነት በአየር ላይ ይጓጓዛል ብለው ይሰጋሉ።
ይህ እውነት ከሆነ ከአንድ ሰው የሚወጣ ትንፋሽ ቫይረሱን ብዙ ርቀት ይዞት ይጓዛል ማለት ነው።
በማሳቹሴትስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ፕሮፌሰር የሆኑት ሊድያ ቦሩባ፤ በከፍተኛ ፍጥነት ፎቶ የሚያነሳ ካሜራ ተጠቅመው፤ አንድ ሰው ሲስል የሚወጣው የፈሳሽ ቅንጣት እስከ 6 ሜትር እንደሚሄድ አሳይተዋል።
ቻይና በሚገኙ የኮቪድ-19 ህሙማን ማከሚያ ክፍሎች ውስጥ የተሠራ ጥናት፤ 4 ሜትር መራቅ የተሻለ መሆኑን ጠቁሟል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ የበሽታዎች ቁጥጥር ተቋም፤ ጥቃቅን የፈሳሽ ቅንጣቶች (ኤሮሶልስ) ቫይረሱን ስለማሰራጨታቸው ገና አልታወቀም ብሏል።
ከርቀት ውጪ ያሉ ነገሮች
ስለበሽታው ስርጭት ሲነሳ ከግምት የሚገባው ርቀት ብቻ አይደለም። በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ለምን ያህል ጊዜ ቆይተናል? የሚለውም መታየት አለበት።
ቫይረሱ ካለበት/ካለባት ሰው ጋር ዘለግ ላለ ጊዜ መቆየት ለበሽታው የመጋለጥ እድልን ያሰፋል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥትን የሚያማክሩ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ከሆነ፤ ከአንድ ሰው ጋር ለስድስት ሰከንድ በአንድ ሜትር ርቀት መቆየት እና በሁለት ሜትር ርቀት ለአንድ ደቂቃ መቆየት እኩል ናቸው።
ሳል ካለበት ሰው ጋር መቀራረብ ደግሞ የበለጠ አስጊ ነው። ከሚያስል ሰው 2 ሜትር መራቅና 2 ሜትር ርቆ መነጋገር እኩል ለበሽታው ያጋልጣሉ።
በሰዎቹ ያሉበት ቦታ ምን ያህል ነፋሻማ ነው? የሚለውም መታየት አለበት። የተጨናነቀ ቦታ ለቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ያጋልጣል።
አየር በየትኛው አቅጣጫ ይነፍሳል? የሚለውን ስንመለከት ደግሞ፤ ቫይረሱ ካለበት ሰው አቅጣጫ ወደሌለበት ሰው የሚነፍስ ከሆነ (ወይም ቬንትሌተር ትንፋሹን ከገፋው) ግለሰቡ ለበሽታው ይጋለጣል።
ስለዚህም ክፍት ቦታ ላይ ወይም ንጹህ አየር በሚናፈስበት ቦታ መሆን ይመከራል።
ለምሳሌ ቻይና በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ ዘጠኝ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ነበር። በሬስቶራንቱ ግድግዳ ላይ ያለው የቤት ውስጥ አየር ሁኔታ መቆጣጠሪያ (ኤር ኮንዲሽኒንግ) ለበሽታው መዛመት ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል።
በጃፓን በኮቪድ-19 በተያዙ 110 ሰዎች ላይ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ቤት ውስጥ መሆን አደባባይ ከመሆን 19 ጊዜ በበለጠ ለቫይረሱ ያጋልጣል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
መፍትሔው ምንድን ነው?
የዩናይትድ ኪንግደም ሳይንቲስቶች 2 ሜትር መራራቅ ከተቻለ እሰየው፤ ካልተቻለ ግን ከአጭር ደቂቃ በላይ ሰዎች ባይጠጋጉ መልካም ነው ይላሉ።
ሰዎች ፊት ለፊት እንዳይቀመጡ ማድረግና በተመሳሳይ ሰዓት አንድ የሥራ ቦታ ወይም ቢሮ የሚገቡ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ይመክራሉ።
በተለይም በሕዝብ ማመላለሻና የተጨናነቁ ቦታዎች የአፍን አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ያስፈልጋል።
ኮሮናቫይረስ መሰራጨት ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ተመራማሪዎች ስለ ቫይረሱ ብዙ መረዳት ቢችሉም፤ አሁንም መመለስ ያልቻሏቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ።
ገና ምላሽ ካልተገኘላቸው ጉዳዮች አንዱ ደግሞ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ምን ያህል ቫይረስ ይወጣል? የሚለው ነው። ታዲያ ለዚህ ግልጽ መልስ እስኪገኝ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ይመከራል።








![ኮሮናቫይረስን ማደን [ስዕል]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/660/cpsprodpb/2642/production/_112749790_01_investigation_01_hd.jpg.webp)









