ኮሮናቫይረስ፡ ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች ያሉበት አዲሱ መድኃኒት ዴክሳሜታዞን በበኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ዓይን

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto
በአሁኑ ጊዜ ዴክሳሜታሶን የሁሉን ቀልብ የገዛ መድኃት ሆኗል። ምክንያቱ ደግሞ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በኮቪድ-19 ተይዘው በጽኑ የታመሙ ሰዎችን ለማከም ሊውል ይችላል ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅትም ይህ መድኃኒት በኮቪድ-19 በጸና የታመሙ ሰዎችን ለማከም መዋሉን እደግፋለሁ ብሏል።
ድርጅቱ በዩናትድ ኪንግደም ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው የክሊኒካል ሙከራ በኮቪድ-19 በጽኑ የታመሙ እና በቬንትሌተር ድጋፍ የሚተነፍሱ ሰዎችን የሞት መጠን በአንድ ሦስተኛ ይቀንሳል፤ ኦክስጅን ብቻ የሚፈልጉ ታማሚዎች የሞት መጠንን ደግሞ በአንድ አምስተኛ ይቀንሳል ብሏል።
በተጨማሪም እንደተባለው የጥናቱ ውጤት ያሳየው ዴክሳሜታሶን በጠና በታመሙ ሰዎች ላይ እንጂ መካከለኛ ምልክት በሚያሳዩት ላይ አመርቂ ውጤት አላመጣም።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም "ይህ ኦክስጅንና የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ ለሚያስፈልጋቸው የኮሮናቫይረስ ህሙማን ላይ የሚያጋጥምን ሞት የሚቀንስ የመጀመሪያው መድኃኒት ነው" ሲሉ ገልጸውታል።
ዋና ዳይሬክተሩ ይህም ታላቅ ዜና መሆኑን ጠቅሰው የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥትንና በዚህን ህይወትን በሚታደግ የመጀመሪያ ግኝት ላይ በመሳተፍ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ለኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ፣ ለሆስፒታሎችና ለህሙማን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
'ዴክሳሜታሶን' እንዴት ያለ መድኃኒት ነው?
ዴክሳሜታሶን ከ1960ዎቹ (እአአ) ጀምሮ በተለያዩ ህመሞች ምክንያት የሚያጋጥሙ እብጠቶችን ለመቀነስና የተወሰኑ አይነት የካንስር ህመሞችን ለማከም ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።
ከ1977 ጀምሮ በተለያየ መልኩ ተዘጋጅቶ አስፈላጊ ከተባሉ የዓለም ጤና ድርጅት የመድኃኒቶች ዝርዝር ውስጥ የገባ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከባለቤትነት መብት ነጻ ከመሆኑ በተጨማሪ በብዙ አገራት ውስጥ በቀላሉ ይገኛል።
የፋርማሲ ባለሙያ እና በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ መምህር የሆኑት አቶ ሸዋነህ አየለ፤ ይህ መድኃኒት 'ግሉኮኮሪኮይድ' ተብሎ በሚጠራ መድኃኒት ዘርፍ ሥር የሚመደብ መሆኑን ይናገራሉ።
አቶ ሸዋነህ ይህ መድኃኒት በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ለበርካታ ዓመታት ከመቆየቱ ባሻገር በስፋት እንደሚገኝ እና የጤና ባለሙያዎችም ታማሚዎችን ለማከም ሲጠቀሙ የቆየ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ባለሙያው እንደሚሉት ይህ መድኃኒት የሚሰጠውን አገልግሎትን የሚተኩ ሌሎች መድኃኒቶች በስፋት ስለማይገኙ ዴክሳሜታሶን በኢትዮጵያ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።
ይህን መድኃኒት ከአፍንጫ ጀምሮ አስከ ሳምባ ድረስ የሚያጋጥሙ አለርጂዎችን ለማከም ጥቅም ላይ ሲውል መቆየቱን ገልጸው፤ በአሁኑ ሰዓት የጎንዮሽ ጉዳታቸው (ሳይድ ኢፌክት) አነስተኛ የሆኑ መድኃኒቶች በመፈብረካቸው እንጂ ይህ መድኃኒት የአስም ታማሚዎችን ለማከም በስፋት ይውል እንደነበረ የፋርማሲ ባለሙያው ይናገራሉ።
በአሜሪካ አገር የድንገተኛ ክፍል እና የኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት እና የጤና ጥበቃ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ጽዮን ፍሬውም በተመሳሳይ፤ መድኃኒቱ አስም ላለባቸው ሰዎች ሊታዘዝ አንደሚችል እንዲሁም ህጻናት እንደተወለዱ መተንፈስ ሲያቅታቸው እንደሚሰጣቸው እና ሰውነታቸውን ለመገንባት ለሚፈልጉ ሰዎች ጡንቻቸውን ለማፈርጠም እንደሚጠቀሙት ይናገራሉ።
'ዴክሳሜታሶን' ለኮሮናቫይረስ ታማሚዎች?
የፋርማሲ ባለሙያ አቶ ሸዋነህ ዴክሳሜታሶን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ለማከም መዋል ይችላል የሚለው ዜና "ለእኔ በጣም አስገራሚ ነው" ይላሉ።
ባለሙያው መድኃኒቱ ኮቪድ-19 በሽታ የሚያስከትለውን ቫይረስ እንደማይገደል ይናገራሉ።
ይህ መድኃኒት ቀድሞውንም ቢሆን በመተንፈሻ አካላት ላይ የሚከሰቱ አለርጂዎችን ለማከም ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል። ኮሮናቫይረስም የመተንፈሻ አካላትን ነው የሚያጠቃው። ይህ ቫይረስ ሰውነታችን ውስጥ ሲገባ፤ የሰውነታችን ተፈጥሯዊ ሥርዓት ቫይረሱን ከሰውነት ለማስወጣት በተደጋጋሚ እናስላለን፤ እናስነጥሳለን። ይህ ተፈጥሯዊ ነው።
ይሁን እንጂ በቫይረሱ የተያዘ ሰው በተደጋጋሚ ሲያስል የመተንፈሻ ቱቦዎች ጡንቻ ይሰበሰባሉ መልሰው ይላቀቀሉ፤ ይህ ሲደጋገም አለርጂ ይከሰታል። ይህ መድኃኒት ግን ተደጋጋሚ ማስነጠስ እና ማሳልን በመቀነስ በመተንፈሻ ቱቦዎች ላይ አለርጂ እንዲቀንስ ያደርጋል። ከዚያም ታማሚው በተሻለ መልኩ መተንፈስ እንዲችል ያስችለዋል በማለት ያስዳሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ መድኃኒት ሰውነታችን የበሽታ መከላከል አቅሙን ከፍ የሚያደርጉ ሴሎች ማምረትን ዝቅ እንዲል ያደርጋል። በርካቶች በኮሮናቫይረስ የሚሞቱት ሰውነታቸው ቫይረሱን ለመከላከል በሚያወጣው ከፍተኛ አቅም ምክንያት ነው ይላሉ ባለሙያው።
የበሽታ መከላከል አቅምን ከፍ የሚያደርጉት ሴሎች የሚመረቱበት መጠን ዝቅ አለ ማለት ሰውነታችን ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያወጣው ኃይል ቀነሰ ማለት ነው። በዚህም ሳል እና ማስነጠስ ስለሚቀንስ ታማሚው በቀላሉ መተንፈስ ይችላል።
ዴክሳሜታሶን ለጽኑ ሕሙማን በደም ስር የሚሰጥ ሲሆን፣ ሕመማቸው ላልፀናባቸው ደግሞ በክኒን መልክ እንዲወስዱት ይደረጋል።
መድኃኒቱ የጎንዮሽ ችግር ያስከትላል?
መድኃኒቱ በስፋት እና በአነስተኛ ዋጋ ማግኘት መቻሉ መልካም አጋጣሚ መሆኑን የሚጠቅሱት ዶ/ር ጽዮን፤ በመድኃኒቱ አጠቃቀም ላይ ግን ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ።
"የጉሉኮስ ቁጥሮችን በመጨመር የስኳር በሽታን ያብሳል፣ ጭንቀት ወይም ድብርት ሊያስከትል ይችላል፣ የአጥንት መሳሳትን ሊያስከትል ይችላል" ሲሉ መድኃኒቱ ሊኖረው የሚችለውን የጎንዮሽ ችግር ይተቅሳሉ።
ዶ/ር ጽዮን እንደሚሉት ይህ የምርመር ውጤተ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ገና ቁንጽል የጥናት ውጤት በመሆኑ ሕብረተሰቡ በዚህ ሊዘናጋ አይገባም በማለት ይመክራሉ።
ስለዚህም ከበሽታው ሊጠብቁን የሚችሉት "በቤት መሆን፣ የአፍና የአፍንጫ መሰፈኛ ጭምብል ማድረግ፣ የእጅ ንጽህናን መጠበቅ . . . እነዚህ ነገሮች እንደሚሰሩ እናውቅለን። ለአሁኑ የሚሰሩት ነገሮች ላይ ብናተኩር ጥሩ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ዴክሳሜታሶን በኢትዮጵያ መቼ ጥቅም ላይ ይውላል?
በጤና ሚኒስቴር የህክምና ግልጋሎት ዋና ኃላፊ የሆኑት አቶ ያዕቆብ ሰማን ለቢቢሲ እንደገለጹት በመድኃኒቱ ላይ ምርመራውን እንዲያደርግ የባለሙያዎች ቡድን ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
በዚህ መሰረትም ቡድኑ ይፋ የተደረገውን ሙሉውን ጥናት ከመረመረም በኋላ የደረሰበትን እንዲሁም ይሆናል ያለውን ምክረ ሐሳብ አቅርቧል። ስለመድኃኒቱ አጠቃቅም ይጥናት ቡድኑ ያቀረበው ምክረ ሃሳብ ዝርዝር ይዘት ገና ይፋ አልተደረገም።
በቀጣይ ምን እንጠበቅ?
ተመራማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራ ውጤታቸውን ለዓለም ጤና ድርጅት አሳውቀው በቀጣይ ቀናትን ደግሞ ስለዴክሳሜታሶን ያለው ሙሉ መረጃ ተተንትኖ እንደሚቀርቡ እየተጠበቀ ነው።
በቀጣይም ድርጅቱ ስለመድኃኒቱ ተጨማሪ መረጃዎችን እንደሚያቀርብና ስለመድኃኒቱ አጠቃቀም ያለው መመሪያ ላይ መሻሻል ያደርጋል ተብሏል።














