የኮሮናቫይረስ፡ ሬምዴሲቬር ሐኪሞች እያዳነቁት ያለው የኮሮናቫይረስ መድኃኒት

ተስፋ የተጣለበት ሬምዴሲቬር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በጥር 20 አሜሪካ የመጀመርያውን የኮቪድ-19 ተጠቂ አገኘች። በዋሺንግተን፤ ኤቨሬት።

ሰውየው በቻይና ሁቤይ ግዛት ዉሃን ከተማ ዘመዶቹን ጠይቆ መመለሱ ነበር። 35 ዓመቱ ነው። ምንም የከፋ ሕመም አይታይበትም። ያስላል፣ ትኩሳት አለው፤ በቃ ይኸው ነው።

ሐኪሞቹ ግን በዚያ ወቅት በቻይና እየሆነ ስላለው ነገር በንቃት እየተከታተሉ ስለነበር ታማሚውን "አይዞህ በቃ ትድናለህ ሂድ" አላሉትም። በዚያ ላይ ሰውየው ደግሞ ከቻይና ነው የተመለሰው።

ትንሽ እንየው ብለው በሽተኛውን ያቆዩታል። እንደፈሩትም ሰውየው ትኩሳቱም ሳሉም እየበረታበት መጣ። ትንፋሽም ያጥረው ጀመር። ብሎ ብሎ ኦክሲጂን አስፈለገው። ሳምባውም ምች መቶት ነበር፤ ኒሞኒያ። እነዚህ ሲደማመሩ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነበር።

ሰውየው በኮቪድ-19 መያዙ እርግጥ ሆነ።

ዶ/ር ዳያዝ ወዲያውኑ ለአሜሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ሁኔታውን አሳወቁ። ሰውየው ላይ ክትትሉ በረታ።

ለዚህ አዲስ በሽታና ለዚህ በሽተኛ ምን ብናደርግ ይሻላል ሲሉ መከሩ። ምክንያቱም በሽታው መድኃኒት አልነበረውም፤ አሁንም የለውም።

ለጊዜው ጥቅል የጸረ-ቫይረስ መድኃኒት የሆነውን ሬምዴሲቬርን ብንሰጠውስ ተባለ። የመድኃኒቱን አምራች ጊሌድ ኩባንያን አማከሩት። ጊሌድ መድኃኒቱን ወደ ሆስፒታሉ ይዞት መጣ።

ከዚህ በኋላ የሚቀረው ከመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ፍቃድ ማግኘት ነበር። ያልታወቀ በሽታ ሲከሰት በሐኪሞች ምክክር አንድ መድኃኒት ተግባራዊ እንዲሆን የሚፈቅደውን ሕግን [ኮምፓሺኔት ዩዝ ኦፍ ድራግስ] በመጠቀም ለ35 ዓመቱ ጎልማሳ ሬምዴሲቬርን በ7ኛው ቀን ሰጡት።

ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት አላስከተለበትም። እንዲያውም እያገገመ መጣ። በተለይ መድኃኒቱን በወሰደ በነገታው የተነቃቃ መሰለ።

ዶ/ር ዳያዝ ያንን ምሽት ሲያስታውሱ "ያ በሽተኛ ያንን መድኃኒት ሲወስድ በወረርሽኙ ታሪክ የመጀመርያው ፍጡር ስለሆነ መድኃኒቱ ምን ሊያስከትልበት እንደሚችል በጉጉት ነበር የምንከታተለው" ይላሉ።

ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው እንግዲህ ሬምዴሲቬር የተሰኘው ይህ መድኃኒት ላይ በምርምር የተዘመተበት።

ሬምዴሲቬር፡ ምን ያህል ፈውስ ይመጣል?

ሬምዴሲቬር ጸረ-ቫይረስ መድኃኒቶች መሀል የሚመደብ ነው። ለኮሮናቫይረስ ታማሚዎች እስካሁን የተሻለው መድኃኒት እሱ እንደሆነ በስፋት እየተነገረ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ሚኒስትር ማት ሃንኮክ "ምናልባት እስካሁን ከሞከርናቸው እጅግ ተስፋ ሰጪው" ብለውታል።መድኃኒቱ ቀደም ሲል ለኢቦላ ታማሚዎች የሚሰጥ ነበር።

ሬምዴሲቬር አሁን በዩናይትድ ኪንግደም የብሔራዊ ጤና አገልግሎት ለኮቪድ-19 ታማሚዎች እንዲሰጥ በሚል አቅርቦት እንዳይጓደል እየተሰራ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሞያዎች ይህን መድኃኒት በተወሰኑ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ በፈዋሽነቱ ዙርያ በቂ መረጃ ተገኝቷል።

ለጊዜው መድኃኒቱ እንደልብ ስለማይገኝ ሕመም ለጠናባቸው ብቻ እየተሰጠ ነው።

የኮሮናቫይረስ ህሙማንን ለማከም እንዲውል የተፈቀደው ሬምዴሲቬር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኮሮናቫይረስ ህሙማንን ለማከም እንዲውል የተፈቀደው ሬምዴሲቬር

በዚህ መድኃኒት ዙርያ ብዙ እየሰራች ያለችው ዩናይትድ ኪንግደም ትሁን እንጂ አሜሪካና ጃፓንም መድኃኒቱን በስፋት ለማምረት ሂደት ላይ ናቸው።

አሁንም ቢሆን መድኃኒቱ ላይ የሚደረጉ ምርምሮችና ሙከራዎች በመላው ዓለም ተጠናክረው ቀጥለዋል።

የዚህ መድኃኒት ተመራጭ መሆን በሁለት ምክንያት ነው። አንደኛው ከዚህ በፊት ለተለያዩ ጸረ-ቫይረስ ደዌዎች የሚሰጥ መድኃኒት ስለሆነ የሰው ልጅ ላይ የከፋ ጉዳይ እንደማያመጣ ቀድሞም መታወቁ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ለኢቦላ ይሰራል ወይስ አይሰራም በሚል ብዙ ክሊኒካል ሙከራዎች የተደረገቡት መሆኑ ነው።

እስካሁን በእርግጠኝነት ስለዚህ መድኃኒት የተደረሰበት ነገር ቢኖር ከኮሮናቫይረስ የማገገምያ ጊዜን እንደሚያፋጥን ወይም እንደሚያሳጥር ነው።

መድኃኒቱን ከኮሮናቫይረስ እያገገሙ ያሉ ታማሚዎች ሲወስዱት በትንሹ በአራት ቀናት የማገገሚያ ጊዜያቸውን ያሳጥራል። ነገር ግን መድኃኒቱ ስለ ፈዋሽነቱ እስካሁን አልተረጋገጠም።

በሽተኞች በሁለት ቡድን ተከፍለው አንደኛው ቡድን መድኃኒቱን እንዲወስድ ሌላኛው እንዳይወስድ በማድረግ ልዩነቱን ማየት ተችሏል። የወሰዱት በተሻለ ፍጥነት አገግመዋል።

ተስፋን ያጫረው ሬምዴሲቬር

የሊድስ የሕክምና ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ዶ/ር ስቴፈን ግሪፊን "እስካሁን ከተሞከሩ መድኃኒቶች እጅግ ተስፋ ሰጪው" ብለውታል ሬምዴሲቬር።

"ለጊዜው እየተሰጠ ያለው በሽታው ለጠናባቸው ብቻ ቢሆንም" ይላሉ ዶ/ር ስቲፈን፣ በቀጣይነት ተደራሽነቱ ሲሰፋ ለብዙ ዜጎች ተስፋን ይሰጣል።

ከዚህ መድኃኒት ሌላ ለኮሮናቫይረስ ፈውስ በሚል አሁን በምርምር ላይ የሚገኙት ለኤችአይቪ እና ለወባ ይሰጡ የነበሩ መድኃኒቶች ናቸው።

የዶናልድ ትራምፕና የቦልሶኖሮ ተመራጭ መድኃኒት ሃይድሮክሲክሎሮኪን ግን ቢያንስ በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዘንድ አልተመረጡም። በርሱ ላይ የሚደረገው ምርምር እንዲቆም ተደርጓል።

ድርጅቱ ሃይድሮክሲክሎሮኪን በተመለከተ ጊዜያዊ ውሳኔ ያሳለፈው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሃይድሮክሲክሎሮኪን መድኃኒትን የወሰዱ ሰዎች ሞታቸው መፋጠኑን ከተመለከተ በኋላ ነው።

ስለዚህ ለጊዜው ሜዳው ላይ ያለው ሬምዴሲቬር ነው።

የጸረ-ቫይረስ መድኃት የሆነውን ሬምዴሲቬርን ያመረተው ጊሌድ የመድኃኒት አምራች መጀመርያ መድኃኒቱን ሲፈበርከው ለጠቅላላ አንቲቫይራል [ጸረ ቫይረስ] እንዲሆን የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ለኢቦላ የተሻለው ሆኖ ቆይቷል።

የተሻለ ይባል እንጂ መድኃኒቱ በኢቦላ ላይ ያሳየው ውጤት ግን ያን ያህል የሚያስመካ አልነበረም።

ሬምዴሲቬር በአሁኑ ጊዜ ቢያንስ በአምስት ዓለም አቀፍ ቤተ ሙከራዎች ውስጥ ምርምር እየተደረገበት ይገኛል። የመድኃኒት ቅመማ ባለሞያዎችም ሆኑ ሐኪሞች ይህ መድኃኒት በምንም መልኩ "ጨርሶዉኑ ፈዋሽ" ተደርጎ መታሰብ እንደሌለበት ያሳስባሉ።

ለአንድ በሽታ መድኃኒት ማግኘት እጅግ አዝጋሚ፣ እጅግ አታካችና እጅግ ትዕግስትን የሚፈታተን ሂደት እንደሆነ የጊሌድ ምክትል ፕሬዝዳንት ቶማስ ሲሀላር ያሰምሩበታል።

ያም ሆኖ ለጊዜው ዓለም ሬምዴሲቬር ላይ ዐይኑን ጥሏል።

ኮሮና
Banner