ኮሮናቫይረስን፡ የወባ በሽታ መድኃኒት ለኮቪድ-19 ማከሚያነት ሊሞከር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የወባ በሽታ መድኃኒቶች ኮሮናቫይረስን ይከላከላሉ እንደሆን ለማረጋገጥ በዩናይትድ ኪንግደም ብራይተን እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ሙከራ ሊደረግ ነው።
ክሎሮኪን፣ ሃይድሮክሲክሎሮኪን እንዲሁን በሕክምናው ፕላሴቦ ተብሎ የሚጠራ ምንም ዓይነት ጥቅምም ሆነ ጉዳት የሌለው ውህድ ከአውሮፓ፣ ከአፍሪካ፣ ከእስያና ከደቡብ አሜሪካ ለተውታጡ 40 ሺህ የጤና ባለሙያዎች ይሰጣል።
ሁሉም ተሳታፊዎች የኮሮናቫይረስ ያለባቸው ወይም የነበረባቸው ናቸው ተብሏል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ሳምንት "ሃይድሮክሲክሎሮኪን እየወሰድኩ ነው" ማለታቸውን ተከትሎ ወቀሳ ሲዘንብባቸው ነበር።
መድኃኒቱን ሳይታመሙ መውሰድ ጉዳት ሊኖረው ይችላል ይላሉ የጤና ባለሙያዎች።
ዩናይትድ ኪንግደም ወስጥ የመጀመሪያዎቹ የጥናቱ ተሳታፊዎቹ ሐሙስ ዕለት በብራይተን እና ሰሴክስ ዩነቪርሲቲ ውስጥ የሙከራ መድኃኒት ይሰጣቸዋል ተብሏል።
ለተሳታፊዎቹ የሚሰጠው መድኃኒት ክሎሮኪን፣ ሃይድሮክሲክሎሮኪን ወይም ፕላሴቦ ነው። መድኃኒቱ የሚሰጣቸው ደግሞ ለሦስት ወራት ነው።
የዩናይትድ ኪንግደም ጥናት ውጤት በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መገባደጃ ላይ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
መድኃኒቶቹ በጤና ባለሙያዎች ላይ እንዲሞከሩ የተፈለገው ሙያተኞቹን ከኮሮናቫይረስ ይከላከላሉ ወይስ አይከላከሉም የሚለውን ለማረጋገጥ ነው።
ጥናቱን ከሚያካሂዱት መካከል አንዱ የሆኑት የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ኖኮላስ ዋይት ናቸው። ፕሮፌሰሩ ' ክሎሮኪን ወይም ሃይድሮክሲክሎሮኪን ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ጠቃሚ ይሆኑ ጎጂ የምናውቀው ነገር የለም ይላሉ።
ነገር ግን እንዲህ ያሉ ጥናቶች ጠቃሚ ናቸው ይላሉ ፕሮፌሰሩ። "ተሳታፊዎቹም ሆኑ አጥኚዎቹ የትኛው መደኃኒት ለማን እንደተሰጠ አያውቁም፤ ይህ ደግሞ ጥናቱን ውጤታማ ያደርገዋል።"
"በጣም ውጤታማ የሆነ መድኃኒት ማግኘት ጊዜ ይፈልጋል" የሚሉት ደግሞ የብራይተን ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ማርቲን ናቸው።
"ክሎሮኪንና ሃይድሮክሲክሎሮኪን ከኮቪድ-19 የመያዝ ዕድልን የሚቀንሱ ከሆነ ይህ መልካም ነው።"
ሁለቱም የወባ መድኃኒቶችን ትኩሳትና ስቃይን በመቀነስ የሚታወቁ ናቸው። ሃይድሮክሲክሎሮኪን የሰውነት መከላከል አቅምን የሚያዳብር መድኃኒት ነው።
መድኃኒቱ ሉፐስ የተሰኘውን በሽታ በመከላከልም ይታወቃል። መድኃኒቱ አሁን ገበያ ላይ መጥፋቱ ለሉፐስ በሽተኞች አደጋ ነው እየተባለ ነው።
የወባ መድኃኒት ታዋቂነቱ የጨመረው የዩናትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ኮቪድ-19ኝን ለማከም ይጠቅማል ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ኮሮናቫይረስ እንዳይዛቸው በማሰብ ሃይድሮክሲክሎሮኪን የተሰኘውን መድኃኒት እየወሰዱ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአሜሪካው ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ቢሮ መድኃኒቱን ከሆስፒታል ወይ ከተፈቀደላቸው ሥፋራዎች ውጭ ጥቅም ላይ ማዋል ክልክል ነው ብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅትም ሰዎች መድኃኒቱን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ እየተጠቀሙ ራሳቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ነው ሲል አስጥቅቋል።
መድኃኒቱ ለለኮቪድ-19 ፈዋሽ መሆኑ አልተረጋገጠም፤ አልፎም ለልብ በሽታ ሊያጋልጥ ይችላል እየተባለ ነው።
ይህ በመድኃኒቶቹ ላይ የሚደረገው ሙከራ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከታይላንድ፣ ከቬትናም፣ ከላኦስ፣ ከካምቦዲያና ከጣሊያን የተወጣጡ ተመራማሪዎች የሚሳተፉበት ነው።














