ኮሮናቫይረስ፡ ወንጀለኛን ከማደን ጋር የሚመሳሰለው ወረርሽኝን የመቆጣጠሪያ መንገድ
![ኮሮናቫይረስን ማደን [ስዕል]](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/2642/production/_112749790_01_investigation_01_hd.jpg.webp)
አንድ ቫይረስ ከየት ተነሳ የሚለው ነገር ነፍሰ ገዳይን ለማደን ከሚደረገው ሂደት አይለይም። ፖሊስ ወንጀል የተፈጸመበት ሄዶ አካባቢውን ማጠር አለበት። የኅብረተሰብ ጤና ሰዎችም እንደዚያው ነው የሚያደርጉት።
ፖሊስ ምስክሮችን ቶሎ ይዞ መመርመር አለበት። የጤና ባለሞያዎችን ቶሎ ታማሚዎችን ወይም የታማሚ ቤተሰቦችን መመርመር አለባቸው።
ገዳዩን ለማግኘት ዱካውን ፍለጋ ሩጫ ያሻል። ቫይረስም እንደዚያ ነው።
ምንም እንኳ የቫይረሱን ጭራ ለመያዝ ዓለም አቀፍ ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም ነፍሰ ገዳዩ ቫይረስ አሁንም ሺህዎችን እየገደለ ነው።
አሁን ቫይረሱ የመጀመርያውን ጥቃት ካደረሰ መንፈቅ ሆኖታል። ሳይንቲስቶች እስካሁን ምን ላይ ደርሰው ይሆን? መዳኛውን ባያገኙም መነሻውን ደርሰውበት ይሆን?
ቫይረሱን ወደ ሰው ያጋባው የትኛው እንሰሳ ነው?
ቁልፉ ነገር መነሻውን ማወቅ ነው። መድረሻው ግን ይደረስበታል።
ከየት ተነሳ? የሚለው ሲመለስ የት ድረስ ይሄዳል? ለሚለው ከፊል ምላሽ ይገኛል።
ከምን ተነሳ? የሚለው ሲታወቅ በምን ፍጥነት እንደሚጓዝም ፍንጭ ይኖረናል። ነገር ግን ይህ ኮሮናቫይረስ ገና ከመነሻው ነው ጥቃቱን ያፋፋመብን። ከየት ተነሳ? የሚለውን ለማጥናትም ጊዜ አልሰጠም። ለቁጥጥርም ጊዜ አልሰጠም።

ቻይናዊያን ለአዲስ ዓመት በሚሰናዱበት ወቅት ዶክተር ሊ ዌንሊያንግ በዉሃን ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍል ውስጥ እየሰሩ ነበር። ሰባት ታማሚዎቻቸው ላይ የሳንብ ምች የሚመስል ምልክት ያሳያሉ።
ዊቻት በሚባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ወሬ ማድመቂያ ላይ ዶ/ር ሊ ለጓደኞቻቸው ፍርሃታቸውን አጋሯቸው።
እርሳቸው ለጓደኞቻቸው ኮቪድ-19 ተከሰተ አላሉም። መቼ አወቁትና።
የጠረጠሩትን ነገሯቸው። የሳርስ ወረርሽኝ በድጋሚ ሳይከሰት አይቅርም ሲሉ ለባልደረቦቻቸው አረዳቸው።
ያን ጊዜ ዶ/ር ሊ ያልተረዱት ግን እነዚህ 7ቱ ህሙማን ላይ ይታይ የነበረው ነገር ሳርስ አገርሽቶ ሳይሆን አዲሱ የኮቪድ-19 የመጀመሪያ ወረርሽኝ ነበር።
ይሄ ሳርስም ያኔ በ2003 ከቻይና ነበር የተነሳው። ከዚያ በኋላ በ26 አገራት ተሰራጭቶ 8 ሺህ ሰዎችን አጥቅቷል።
ዶ/ር ሊ በዊቻት በኩል ለጓደኞቻቸው ስጋታቸውን በመግለጻቸው ብቻ በሦስተኛው ቀን ካሉበት ፖሊስ ከቸች አለ።
ሌሎች 8 ሰዎች ጋር አብሮ አሰራቸው። ክሱ የነበረው ታዲያ የሐሰት ወሬ አሰራጭተዋል የሚል ነበር። ይህ በቻይና መገናኛ ብዙሃን ጭምር የተዘገበ ጉዳይ ነው።
ኋላ ላይ ከእስር ሲፈቱ፤ ዶ/ር ሊ ራሳቸው በኮሮናቫይረስ ተህዋስ ተይዘው ነበር። ከዚያ ወዲያ በሕይወት ለመቆየትም ዕድለኛ አልነበሩም። በጥቅምት 7፣ በተወለዱ በ34 ዓመታቸው በአጭር ተቀጩ።
ዶ/ር ሊ የአንድ ልጅ አባት ነበሩ፤ ሚስታቸውም እርጉዝ ነበረች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወንጀሉ የተፈጸመበት ቦታ
ታኅሳስ ወር መጨረሻውን ሙሉ እንደ ዶ/ር ሊ ሁሉ ሌሎች ነርሶችም የሆነ ወረርሽን የሚመስል ነገር እንደተከሰተ ሲያስጠነቅቁ ነበር።
መጀመሪያ የነቁት ግን የጤና ሠራተኞች ነበሩ። የጤና ሠራተኞቹ ታማሚዎች ከአንድ ቦታ የሚመጡ እንደሆነ አስተዋሉ። ሁሉም ሁዋናን ከሚባው የዓሣና የባሕር ውስጥ እንሰሳት ገበያ የመጡ ሰዎች ነበሩ።
ይሄ የዓሣ ገበያ ታዲያ በዉሃን አዲስ ሰፈር የሚገኝ ሲሆን ዶሮ፣ ዓሣና ሌሎች ተሳቢና ተራማጅ እንሰሳት ሳይቀሩ ከነነፍሳቸው የሚሸጡበት ቅልጥ ያለ ሥጋ ተራ ነው።
በታኅሳስ ወር መጨረሻ የዉሃን ከተማ የጤና ኮሚሽን የሆነ ወረርሽኝ መከሰቱን አምኖ ለቤይጂንግ ሪፖርት አደረገ። በቀጣዩ ቀን ያ የዓሣ ገበያ ተዘጋ።
በዚህ ሁኔታ ወንጀለኛው ብዙ ጉዳት አድርሶ ከሄደ በኋላ ነው ፖሊስ የወንጀሉን ሥፍራ የከበበው እንደማለት ነው።
ዛሬ ሳይንቲስቶች በጋራ ያመኑት ነገር ቢኖር ከፍተኛ ወረርሽኝ በዚያ የዓሣ ገበያ መከሰቱን ነው፡፡ ቫይረሱ የመነጨው ከዚያ ገበያ ነው ወይ የሚለው ግን አከራካሪ ሆኗል።
እርግጥ ነው በዚያ ገበያ ከሰዎችም ሆነ ከእንሰሳት ናሙና ተወስዶ ሁሉም ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ምናልባት የመጀመርያው ሰው የተያዘው ቫይረሱ ይፋ ከመደረጉ አራት ሳምንታት ቀደም ብሎ እንደሆነ ተገምቷል። ይህም በታኅሣሥ 1/ 2019 መሆኑ ነው። ያን ጊዜ የተከሰተው መጀመሪያ በዚያ የዓሣ ገበያ ስለመሆኑ ግን መረጃ የለም።
በመስከረም ወር በዉሃን ከተማ በርካታ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ እንደሆነ ቢታወቅም፤ ማንም በዚያ ፍጥነት ዓለም ላይ ይሰራጫል ያለ አልነበረም። አይደለም በመላው ዓለም፣ ቫይረሱ ቻይናን ያዳርሳል ያለም አልነበረም።
በመስከረም 11/2019 የመጀመሪያው ሞት በቻይና በተመዘገበ በ9 ቀናት ውስጥ ቫይረሱ ድንበር ተሸገረና ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ታይላንድ መድረሱ ተሰማ።
ቫይረሱን ለመያዝ መርማሪዎች እግር በእግር ቢከተሉትም ሁልጊዜም ቀድሞ ሌላ ስፍራ ይገኛል። ባለፉት 6 ወራት 188 አገራትን ያዳረሰውም በዚሁ መንገድ ነው። አሁን 7 ሚሊዮን ሕዝብን በክሏል።

የፎቶው ባለመብት, WEIBO
የገዳዩን ቫይረስ ማንነት ማወቅ
የአንደርሰን ቤተ ሙከራ ኃላፊ ፕሮፌሰር ክርስቲያን እንደሚሉት የመጀመሪያው ሥራ ገዳዩ ቫይረስ ማን ነው ብሎ ማግኘት ነው።
ቫይረሱ ከእንሰሳት ወደ ሰው እንዴት ሄደ? ከሰው ወደ ሰው እንዴት ነው የሚተላለፈው? የሚለው የሚታወቀው ከዚያ በኋላ ነው።
በመስከረም መጨረሻ በዉሃን ኢንስቲትዩት ኦፍ ቪሮሎጂ [በቫይረስ ላይ ምርምር በሚደረግበት ተቋም] ውስጥ የተደረገውም ይኸው ነው።
ከሰው አፍንጫ ፈሳሽ በተወሰደ ናሙና የቫይረሱ ዘረመል ቅርጹ ተደረሰበት።
የቫይረሱ የዘረመል ቅጥልጥል ኮዱ ሲገኝ የቫይረሱ አፈጣጠር ተገኘ ማለት ነው። እንዴት እንደሚሰራጭም የሚታወቀው የዘረመል ቅጥልጥል ኮዱ ሲታወቅ ነው።
የዘረመል ኮድ የፊደሎች ቅጥልጥል ነው። ለምሳሌ የአንድ ሰው የዘረመል ኮድ በ3 ቢሊዮን ጄኔቲክ ፊደሎች ነው የሚወከለው።
አንድ ተራ የጉንፋን ቫይረስ ለምሳሌ 15 ሺህ ፊደሎች ይወክሉታል። ይህ የፊደል ውክልና ቫይረሱ ባሕሪውን፣ እንዴት እንደሚዋለድ፣ በምን ፍጥነት እንደሚዋለድ ይነግረናል።
አንድን የቫይረስ ዘረመል ኮድ ፈልፍሎ ለማግኘት ወራት ሊወስድ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ዓመታትንም ይወስዳል።
በዚህ ረገድ ግን እድለኞች ነን።
የኮቪድ-19 ቫይረስ ዘረመል ኮድ የተገኘው በመስከረም 10 ሲሆን የወሰደው ጊዜም በጣም አጭር ነበር።
ይህን የዘረመል ቅጥልጥል ኮድ የፈቱት ደግሞ በዉሃን ቪሮሎጂ ኢንስቲትዩት ፕሮፌሰር ዮንግ ዣንግና የመሩት ቡድን ነው።
ልክ የዘረመል ቅጥልጥሉ ሲገኝ ቫይረሱ ከኮሮናቫይረስ ቤተሰብ የሚመደብ ዓይነት ቫይረስ መሆኑ ተደረሰበት፤ 80 ከመቶ ደግሞ ከሳርስ ጋር ተፈጥሮው እንደሚመሳሰል ታወቀ።
በተለምዶ ኮሮናቫይረስ የሚባለው በዘርፉ ባለሙያዎች ለብዙ ቫይረሶች የተሰጠ የወል ስም እንጂ የአንድ ልዩ ቫይረስ ስም አይደለም።
ባለብዙ ዝርያው ኮሮናቫይረስ
የዚህ ቫይረስ ዝርያዎች በአሳማ፣ በግመል፣ በሌሊት ወፍ እንዲሁም በድመት ላይ ጭምር በስፋት ይገኛል።
ኮቪድ-19 የኮሮናቫይረስ ቤተሰብ አንድ አባል ብቻ ነው።
ከእንሰሳት ወደ ሰው በመተላለፍ ደግሞ ከኮሮናቫይረሶች 7ኛ ነው።
የዘረመል ቅጥልጥል ኮዱ ከተገኘ በኋላ ሁለተኛው እንቆቅልሽ አንዴት እንደርስበታለን የሚል ነው። ይህም ስለመመርመሪያ ሂደቶች እንድናውቅ ያደርገናል።
በወንጀል ምርመራ ሂደት ሦስተኛው ወንጀለኛን የማደን ሂደት ወንጀለኛውን በቁጥጥር ማዋል ነው። በተመሳሳይ ቫይረሱን ለመያዝ በመላው ዓለም ፖሊሶች እየተራወጡ ነው። ወንጀለኛው ተያዘ የምንለው ደግሞ ክትባቱ ሲገኝ ነው።
ፕሮፌሰር አንደርሰን እንደሚሉት በርካታ ጥናቶች ይህ ቫይረስ ከሌሊት ወፍ እንደመጣ ይጠቁማሉ። ምክንያቱም በሌሊት ወፍ ውስጥ በርካታ ተመሳሳይ ቫይረሶች ይገኛሉና ነው።
መላምቱ እውነት ከሆነ አሁን ማወቅ ያቃተን፤ እንዴት ከሌሊት ወፍ ወደ ሰው እንደተሸጋገረ ነው ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
የፕሮፌሰር አንደርሰን የጥናት ቡድን ከሌሊት ወፍ የመጣ ሌላ የኮሮናቫይረስ አባል የሆነ ቫይረስ አግኝቷል። የዚህ ቫይረስ የዘረመል ቅጥልጥል ኮዱ ከኮቪድ-19 የሚለየው በትንሹ ነው። "96 ከመቶ አንድ ናቸው ማለት ይቻላል" ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
ሌላው ደግሞ ፓንጎሊን በሚባሉ አጥቢ እንሰሳትም ላይ ተመሳሳይ ቫይረስ ተገኝቷል።
አንዱ መላምት የሚሆነው ታዲያ ቫይረሱ ከሌሊት ወፍ ተነስቶ ወደ ፓንጎሊኖች ተሻግሮ ከዚየ የተወሰነ ፕሮቲን አግኝቶና ዳብሮ ይሆን ወደ ሰው የመጣው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ምርምሩ ቀጥሏል።
የሚገርመው በቻይና ይህን የዘረመል ቅጥልጥሉን ያገኙት ፕሮፌሰር ዣንግ ከዚህ ስኬታማ ሥራ በኋላ ቤተ ሙከራቸው ታሽጎባቸዋል፤ ባልደረቻቸውም ኮዱን ለዓለም ባሳወቁ በ2ኛው ቀን ፖሊስ ወስዷቸዋል። ፍቃዳችውንም ሰርዞታል።
የቻይና መገናኛ ብዙሃን እንደዘቡት ይህ ለምን እንደተደረገ የተሰጠ ምንም ምክንያት የለም።
የፕሮፌሰር ዣንግ የዘረመል ቅጥልጥል ባይኖር ኖሮ አሁን የተሰሩት ነገሮች አንዳቸውም ሊሳኩ አይችም ነበር ይላሉ ፕሮፌሰር አንደርሰን።
የቫይረስ ዘረምል ቅጥልጥል ኮድ ሳይገኝ አንዳችም ሥራ መስራት አይቻም ነበር።

ወንጀለኛውን ማሳደድ
ደቡብ ኮሪያ 51 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት አገር ናት። ቫይረሱን አሳዶ በመያዝ ተሳክቶላታል የምትባለው እርሷ ናት።
ይህን ያሳካችው ወንጀለኛን አድኖ የመያዝ ችሎታ ያላቸውን ትንንሽ የቫይረስ ወታደሮችን በማሰልጠኗ ነው።
እነዚህ ወንጀል አዳኞች ሥራቸው ሌላ አይደለም። አንድ ሰው ቫይረሱ ተገኘበት ሲባል የዚያን ሰው ንክኪና የእንቅስቃሴ ታሪክ ቶሎ አግኝቶ እርምጃ መውሰድ ነው።
እነዚህ አዳኞች ማን ራሱን ማግለል እንዳለበት፣ ማን መንቀሳቀስ እንደሚችል፣ የትኛው ሕንጻ ሙሉ በሙሉ መታሸግ እንዳለበት፣ የትኛው ገበያ መዘጋት እንዳለበት ቶሎ ውሳኔ ይሰጣሉ።
በዚህ ሁኔታ ቫይረሱን መፈናፈኛ አሳጡት። እግር በእግር አሳደዱት። ደቡብ ኮሪያ ተጨበጨበላት።
ይህ ስኬት እያለ ነው ታዲያ በጥቅምት መጨረሻ አንዲት የኮሪያ ከተማ ድንገት በቫይረሱ የተወረረችው።
በጥቂት ቀናት ውስጥ ሺህ ሰዎች ተያዙ ተባለ። ይህቺ ከተማ ዴጉ ትባላለች። አንዲት ሴት ናት ይቺን ከተማ የበከለቻት። ብቻዋን!
ለዚህች ሴትዮ "ታማሚ 31" የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷታል።
ይህች ሴት በጥቅምት 17 ቫይረሱ እንዳለባት ታወቀ።
እነዚህ ቫይረስ አዳኞች ያዳረሰቻቸውን ቦታዎች በሙሉ ሲመረምሩ በ10 ቀናት ውስጥ አንድ ሺ ሰዎችን ነካክታለች።
ምስጋና ለአዳኞች እንጂ ሴትዮዋ ታደርስ የነበረው ጉዳት ከዚህም በላይ በሆነ ነበር ተብሏል።
እነዚህ አዳኞኝ የስልክ መተግበሪያን፣ ጂፒኤስን [የቦታ አመልካች መሳሪያ]፣ የክፍያ ካርዶችን እነ ክሬዲት ካርድን ጭምር ይጠቀማሉ።
ይቺ ሴትዮ መጀመሪያ የሺንቼኖጂ ቤተክርስቲያን አባል መሆኗን አልተናገረችም ነበር። እነዚህ አዳኞች ናቸው የደረሱበት። ያደረሰቸው ጉዳትም ከፍተኛ የሆነው ለዚያ ነው።
ይህ ቤተክርስቲያን 300 ሺህ አባላት አሉት። የቤተክርስቲያኑ መሪ ሊ ማን ሂ ይባላሉ። ዳግማዊ ክርስቶስ ናቸው ተብሎ ይታመናል። መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎም ሥልጣን ያላቸውም እሳቸው ብቻ ናቸው ብለው ያምናሉ ተከታዮቹ። ይህ ቤተክርስቲያንና የሚያራምደው እምነት ደቡብ ኮሪያ ከሚገኙ በአብዛኞቹ ክርስቲያኖች ዘንድ ያፈነገጠ የሚባል ነው።
ይህቺ "ታማሚ 31" በሚል ቅጽል የምትታወቅ ሴትዮ የዚህ ቤተክርስቲያን አባል መሆኗ ብቻ አልነበረም ችግር የፈጠረው። የህመሙን ምልክት እያሳየች በ10 ቀናት ብቻ አንድ ሺህ ሰዎችን ጋር በተለያየ መንገድ ተገናኝታለች።
ጥቅምት 7 ላይ የመኪና አደጋ ደረሰባትና ሆስፒታል ገባች። ሆስፒታል ውስጥ ደግሞ ከ128 ሰዎች ጋር ንክኪ ነበራት። እቃ ላምጣ እያለች ከሆስፒታል ወጥታ ብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝታለች። በኋላም ምሳ በልቼ መጣሁ እያለች ጓደኞቿን ታገኝ ነበር። በመጨረሻም ተደብቃ ወጥታ እዚህ ቤተክርስቲያን ተገኘችና ከሺህ ሰዎች ጋር ታደመች።
ትልቁ ችግር የተከሰተው ደግሞ የዚህ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ራሳቸውን መደበቃቸው ነው። ዴጉ ከተማ ከፍተኛ ተጠቂ የሆነችውም በዚሁ ምክንያት ነበር።
ዋናው የአደኑ ሂደት የተያዘውን ሰው የጉዞ ታሪክ ለማግኘት በፍጥነት ምርመራ በማድረግ በሚያዚያ ወር በዴጉ ከተማ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ዜሮ ሆነ።
ሌሎች አገሮች ግን ይህን የዴጉን ስኬት ማሳካት አልተቻላቸውም።
አንዲት የጉዞ ታሪኳን የደበቀች ሴት ይህን ሁሉ ጉዳት የምታደርስ ከሆነ የሰዎችን የእንቅስቃሴ ታሪክ በቴክኖሎጂ ለማደን የማይችሉ አገራት ቫይረሱ እንዴት ሊዛመት እንደሚችል መገመት ከባድ ይሆንባቸዋል።














