የኮሮናቫይረስን መከሰት ያጋለጠው ዶክተር በበሽታው ህይወቱ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, LI WENLIANG
ገዳዩ ኮሮናባይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ለማሳወቅ ጥረት ያደረገው ቻይናዊው ዶክተር በቫይረሱ ህይወቱ በማለፉ ቻይና ውስጥ ከፍተኛ ቁጣና ሃዘንን ቀሰቀሰ።
የዶክተሩ ሞት ከተሰማ በኋላ የቻይና የማህበራዊ ትስስር መድረክ በሆነው ዌቦ ላይ ዜጎች ከፍተኛ ሐዘናቸውን ሲገልጹ ቆይተው ሁኔታው ወደ ቁጣ ለመቀየር ጊዜ አልፈጀበትም።
በዚህም ምክንያት መንግሥት መጀመሪያ ላይ በሽታውን ለመደበቅ በመሞከርና የወረርሽኙን አስከፊነት በማቃለል ክስ እየተሰነዘረበት ነው።
በዶክትር ሊ ሞት የተፈጠረው ቁጣ እየተባባሰ በቻይና ውስጥ የመናገር ነጻነት ስላለበት ሁኔታ ውይይት እንዲጀመር አድርጓል።
የአገሪቱ ጸረ ሙስና ተቋምም "ከዶክተሩ ጉዳይ ጋር በተያያዘ" ምርመራ ማድረግ እንደሚጀምር አሳውቋል።
አንድ የቻይና ድረ ገጽ እንዳለው የሟቹ ዶክተር ባለቤት እርጉዝ ስትሆን ሰኔ ላእ እንደምትወልድ ይጠበቃል።
ኮሮናቫይረስ እስካሁን 636 ሰዎችን የገደለ ሲሆን ከ31 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በቻይና ብቻ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
ዶክተር ሊ ዌንሊያንግ ወረርሽኙ በተከሰተበት ዉሃን ከተማ ዉሃን ሴንትራል ሆስፒታል ውስጥ ይሰራ ነበር።
ዶክተር ሊ በሆስፒታሉ ውስጥ ይሰራ በነበረበት ወቅት በአንድ እንግዳ ቫይረስ ተጠቅተው የመጡ ሰባት ሰዎችን ያገኛል። ከዚያም በሽታው ከ15 ዓመታት በፊት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሆኖ የነበረው 'ሳርስ' ሳይሆን እንደማይቀር ገምቶ ነበር።
የበሽታውን መከሰት በተመለከተ ለሰዎች በመንገር እንዲጠነቀቁ ምክር የለገሰ ሲሆን ፖሊሶች ቤቱ ድረስ መጥተው ከድርጊቱ እንዲቆጠብ አስጠንቅቀውታል።
ፖሊሶቹ በወቅቱ 'ሃሰተኛ መረጃን እያሰራጨህ ህብረተሰቡን እያሸበርክ ነው' ሲሉ ነበር ማስጠንቀቂያውን የሰጡት።
ዶክተር ሊ ይህን ማስጠንቀቂያ ከደረሰው ከአንድ ወር በኋላ ግን በሽታው በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ዓለምን ማስጨነቅ ሲጀምር፤ ዶክተር ሊም የበሽታው ሰለባ ሆኖ የሆስፒታል አልጋ ላይ ሆኖ ነበር።
ሊ ከሃኪም ቤት ተኝቶ ታሪኩን ይፋ ሲያደርግ ጀግና ተብሎ ተወድሷል።
"ጤና ይስጥልኝ፤ ሊ ዌንሊያንግ እባላለሁ፣ በዉሃን ማዕከላዊ ሆስፒታል የዓይን ሃኪም ነኝ" በማላት ይጀምራል የዶክተሩ መልዕክት።
ዶክተሩ ይፋ ያደረገው መልዕክት የኮሮናቫይረስ በተከሰተባቸው የመጀመሪያ ሳምንታት ዉሃን ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት በሽታውን ለመሸፋፈን ያደረጉትን ጥረት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው ተብሏል።
ታህሳስ ወር ላይ ወረርሽኙ በተከሰተበት ማዕከል ውስጥ ይሰራ የነበረው ዶክተር ሊ በአንድ እንግዳ ቫይረስ ተጠቅተው የመጡ ሰባት ሰዎችን አግኝቶ ነበር ተናግሯል።
እንደ አውሮፓዊያኑ ታህሳስ 30 ላይ ዶክተሩ በአንድ የቡድን መልዕክት መለዋወጫ መድረክ ላይ ለሙያ አጋሮቹ ዶክተሮች ስለወረርሽኙ መከሰትና እራሳቸውን ለመጠበቅ የመከላከያ አልባሳትን እንዲጠቀሙ የሚመክር መልዕክት አስተላልፎ ነበር።
ከአራት ቀናት በኋላ ከሕዝብ ደህንንት ቢሮ ባለስልጣናት መጥተው አንድ ደብዳቤ ላይ እንዲፈርም ነገሩት። ወረቀቱም ዶክተሩን "ሐሰተኛ አስተያየቶችን በመስጠት" ይህም "በከፍተኛ ሁኔታ ማኅበራዊ ሥርዓትን የሚያናጋ" መሆኑን በመግለጽ ጥፋተኛ አድርጎ የሚከስ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, LI WENLIANG
"በጥብቅ የምናሳስብህ ነገር ቢኖር፡ በዚህ ድርጊትህ በግትርነት የምትገፋ ከሆነና ሕግን ባለማክበር በሕገወጥ ተግባርህ የምትቀጥል ከሆነ ለፍርድ ትቀርባለህ። ገብቶሃል?" ይላል የቀረበለት ወረቀት። ከስርም ዶክተር ሊ በእጅ ጽሑፉ "አዎ፤ ተረድቻለሁ" የሚል ጽሑፍ ሰፍሯል።
"ሐሰተኛ አሉቧልታዎችን በማሰራጨት" በሚል ተጠርጥረው ምርመራ ከተደረገባቸው ስምንት ሰዎች ዶክተሩ አንዱ ነው።
በጥር ወር ማብቂያ ላይም ዶክተር ሊ ከባለስልጣናት የተሰጠውን የዚህን ደብዳቤ ቅጂ 'ዌቦ' በተባለው የቻይናዊያን ማህበራዊ የትስስር መድረክ ላይ በማውጣት ምን አጋጥሞት እንደነበረ ይፋ አደረገ።
ይህንን ተከትሎም የአካባቢው ባለስልጣናት የበሽታው ወረርሽኝ ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ በኋላ ዶክተሩን ይቅርታ ቢጠይቁትም፤ ይቀርታው የዘገየ ነበር።
በጥር ወር መጀመሪያ ሳምንታት ላይ ዉሃን ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት በቫይረሱ የሚያዙት ሰዎች በሽታው ካለባቸው እንስሳት ጋር የቀረበ ንክኪ ያላቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑ በመግለጻቸው፤ ሐኪሞችን ለመከላከል ምንም መመሪያ አልተሰጠም ነበር።
ፖሊሶች ዶክትር ሊን ካናገሩት ከሳምንት በኋላ አንዲት የግላኮማ ችግር ያለባትን ሴት እያከመ ነበር። ታካሚዋም አዲሱ የኮሮናቫይረስ እንዳለባት አላወቀም።
ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈረው ጽሑፉ ዶክትር ሊ በጥር ወር ሁለተኛ ሳምንት ላይ ሳል እንደጀመረው፣ በቀጣዩ ቀን ደግሞ ትኩሳት እንዳጋጠመውና ከሁለት ቀናት በኋላም ብሶበት ሆስፒታል እንደገባ ገልጿል። ቤተሰቦቹም መታመማቸውንና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውንም አመልክቷል።
ዶክትር ሊ ላይ የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት ከታየ ከ10 ቀናት በኋላ ቻይና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን አወጀች።
ዶክትር ሊ እንዳለው የኮሮናቫይረስ ምርመራ በተደጋጋሚ ቢደረግለትም የተገኘው ውጤት ግን ነጻ እንደሆነ ነበር። ነገር ግን በጥር ወር መጨረሻ ላይ የተደረገለት ምርመራ በበሽታው መያዙን አመለከተ።
ይህንንም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ይፋ በማድረጉ አድናቆትና ድጋፍን ከበርካታ ሰዎች አግኝቷል።
















