የኮሮናቫይረስ እስካሁን ትክክለኛ ስም እንደሌለው ያውቃሉ?

የፎቶው ባለመብት, SMITH COLLECTION/GADO
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አጥቅቶ፣ መቶዎችን ደግሞ በገደለው የወቅቱ የዓለማችን የጤና ስጋት የሆነው ቫይረስ አስካሁን ድረስ ትክክለኛ ስም እንዳልተሰጠው ያውቃሉ?
ወረርሽኙ እስካሁንም የሚታወቀው ኮሮናቫይረስ በሚል ስያሜ ነው። ነገር ግን ይህ ስም ቫይረሱ የሚገኝበት ዝርያ አጠቃላይ ስም ነው።
ስለዚህም ተገቢውን ስያሜ ለበሽታው ለማግኘት ሳይንቲስቶች የቤተሙከራቸውን በር ዘግተው ጥረት ሲያደረጉ ቆይተዋል። አሁን ግን ተገቢውን ስያሜ ይፋ ለማድረግ እየተቃረቡ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለዚህ ቫይረስ ስም መስጠት ለምን ይህን ያህል አስቸጋሪ ሆነ?
"ለአዳዲስ ቫይረሶች ስም ማውጣት በአብዛኛው ቀስ ብሎ የሚመጣ ጉዳይ ነው፤ ሁሉም እንደሚረዳው እስካሁን ዋነኛው ትኩረት የተደረገው የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ነው" ሲሉ በጆንስ ሆፕኪንስ ውስጥ በሚገኘው የጤና ደህንነት ማዕከል ውስጥ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ክሪስታል ዋትሰን ይናገራሉ። ።
አክለውም "ነገር ግን ስም መስጠቱ ቀዳሚ ጉዳይ የሚሆንባቸው ወቅቶችም አሉ" ይላሉ።
ይህንን ቫይረስ ለመለየት ሳይንቲስቶች ኖቬላ ወይም "አዲስ" እያሉ ሲጠሩት ቆይተዋል። ቫይረሱ ኮሮናቫይረስ የሚል ስም ያገኘው በማጉሊያ መነጽር በሚታይበት ጊዜ ባለው ከዘውድ ጋር የሚመሳሰል ቅርጽ እንደሆነ ይነገራል።
የዓለም የጤና ድርጅትም ቫይረሱ በጊዜያዊነት 2019-ኤንኮቪ (2019-nCoV) ተብሎ እንዲጠራ አድርጓል።
ይህም 2019 ቫይረሱ የተገኘበት ዓመትን የፈረንጆቹን አመት ሲወክል "ኤን" ደግሞ ኖቬላ ወይም "አዲስ" የሚለውን አመልክቶ "ኮቪ" የሚለው ደግሞ ኮሮናቫይረስን ይወክላል።
"በሽታው አሁን ያለውን ስም ለመጠቀም ቀላል አይደለም፤ ስለዚህም የመገናኛ ብዙሃንና ሕዝቡ ቫይረሱን ለማመልከት ሌሎች ስሞችን እየተጠቀሙ ነው" ይላሉ ዶክተር ዋትሰን።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
"ለቫይረሱ ትክክለኛውን ስያሜ የማንጠቀም ከሆነ የእራሱ ችግር ያስከትላል። ለምሳሌም የቻይና ቫይረስ በማለት ከተጠራ በአገሩ ዜጎች ላይ ችግርን ያስከትላል።"
ማህበራዊ ሚዲያ በተስፋፋበት በዚህ ዘመን ይፋዊ ያልሆኑ ስሞች በፍጥነት ተሰራጭተው ስለሚለመዱ በተገቢ ስያሜ ለመተካት እጅግ አስቸጋሪ እንደሚሆን ይጠቅሳሉ።
አዲስ ለሚከሰቱ የቫይረስ አይነቶች በአስቸኳይ ስያሜን የመስጠቱ ኃላፊነት ያለው የቫይረሶችን አፈጣጠርና ዝርያ የሚለይ ኢንተርናሽናል ኮሚቴ ኦን ታክሶኖሚ ኦፍ ቫይረስስ የተባለው ኮሚቴ ነው።
ከአስር ዓመት በፊት አጋጥሞ የነበረው ኤች1ኤን1 (H1N1) የተባለው ወረርሽኝ "የወፍ ጉንፋን" የሚል ስያሜን አግኝቶ ነበር። ይህም ምንም እንኳን በሽታው በሰዎች አማካይነት የሚዛመት ቢሆንም ግብጽ ያሏትን አሳማዎች በሙሉ አርዳ አስወግዳለች።
ይፋዊ ስያሜዎችም እራሳቸው ችግርን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ለዚህም ምሳሌ ከ4 ዓመታት በፊት ተከስቶ ለነበረው ሜርስ ቫይረስ የተሰጠውን ስያሜ የዓለም የጤና ድርጅት ተችቶት ነበር። ምክንያቱም ለበሽታው የተሰጠው ስያሜ አህጽሮተ ቃል ሲተነተን የመካከለኛው ምሥራቅ የመተንፈሻ አካል በሽታ የሚል በመሆኑ ነው።
ድርጅቱ እንዳለው ለአንዳንድ የበሽታ አይነቶች የሚሰጠው ስያሜ በተወሰኑ የኃይማኖትና የጎሳ አባላት ላይ ተገቢ ያልሆነ የጉዞና የንግድ ግንኙነት እቀባንና ሌሎችንም ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል።
በዚህም ምክንያት ለኮሮናቫይረስ ትክክለኛ ስያሜ ሲወጣ በስሙ ውስጥ መካተት የለባቸውም ያላቸውን ነገሮች በመመሪያ መልክ ድርጅቱ እንደሚከተለው አስቀምጧል።
- መልክዓ ምድራዊ ስፍራዎችን
- የሰዎችን ስም
- የእንስሳት ስም ወይም የምግብ አይነት
- የተለየ ባህልን ወይም ኢንዱስትሪ
በተጨማሪም ስያሜው ሲሰጥ ስሙ አጭርና ገላጭ መሆን እንዳለበትም አመልክቷል።
አስራ አንድ ሰዎች ያሉበትና ለአዲሱ ወረርሽኝ ቀላልና ገላጭ ስያሜ ለማግኘት የተሰባሰበው ኮሚቴ ሁለት ሳምንታትን የፈጀበት ሲሆን አንድ ስያሜ ላይ ለመስማማትም ሁለት ቀናት አስፈልጎት እንደነበር የቡድኑ አባል የሆኑት ፕሮፌሰር ቤንጃሚን ኑማን ተናግረዋል።
ኮሚቴው ለአዲሱ ወረርሽኝ ያገኘው ስያሜ አሁን በሳይንሳዊ ጆርናል ላይ እንዲታተም ያቀረበ ሲሆን በቀናት ውስጥም ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ኮሚቴው ስራውን ማጠናቀቁ ሕዝቡ ቫይረሱን እንዲረዳው ከማገዙ በተጨማሪ ግራመጋባትን በማስወገድ ጊዜን የሚቆጥብ ሲሆን ተመራማሪዎችም በሽታውን በመዋጋት ላይ እንዲያተኩሩ ያግዛል ተብሏል።












