የኮሮናቫይረስ ዘመኗ እመጫት ኢትዮጵያዊት የአራስ ቤት ማስታወሻ

እርጉዝ ሴት

የፎቶው ባለመብት, BBC

የኮሮናቫይረስ የዓለም ጤና ስጋት በሆነባቸው ባለፉት ወራት ወረርሽኙን በመፍራት በርካቶች በጣም አስፈላጊ ለሆኑ የጤና አገልግሎቶች ወደ ህክምና ተቋማት ከመሄድ እተቆጠቡ መሆናቸው የጤና ባለሙያዎችን እያሳሰበ ነው።

ከእነዚህም መካከል የእርግዝና ክትትል ለማግኘትና ለወሊድ ወደ ሐኪም ቤቶች መሄድ ያለባቸው እናቶች ስጋት ይጠቀሳል። ከእነዚህ ውስጥም ወ/ሮ መሠረት* ተመሳሳይ ስጋት ነበራት፤ ነገር ግን የሚጠበቅባትን ጥንቃቄ አድርጋ ከሳምንታት በፊት ሐኪም ቤት ውስጥ ወልዳለች።

ነገር ግን ቀደም ሲል የምታውቃቸው ነገሮች በወረርሽኙ ምክንያት ተቀይሯል ስትል የገጠማትን ነገሮች ያሰፈረችበትን የግል ማስታወሻ ለቢቢሲ አጋርታለች።

መስመር

በእርግዝናዬ ማገባደጃ ሰለሳ ሰባተኛ ሳምንት ላይ ክትትል የማደርግበት ሆስፒታል ስደርስ ግራ የመጋባት ስሜት ውስጥ ነበርኩ።

ገና ከሆስፒታሉ መግቢያ ጀምሮ አንዲት ሴት እያንዳንዱን የሚገባውን ሰው የሙቀት መጠን ትለካለች። እኔም ተለክቼ ወደ ውስጥ ስዘልቅ ደግሞ ሆሰፒታሉ ውስጥ ያለው ሰው ሁሉ ጭምብል (ማስክ) አድርጓል።

ሳያደርጉ ለሚመጡትም በሆስፒታሉ ከጨርቅ የተዘጋጀ ማስክ እየታደለ ስለነበረ ያላደረገ ሰው አልነበረም፤ የታካሚ ተቀባዮቹም ሆነ የነርሶቹ ቢሮ ፊት ለፊት ወለሎቹ ላይ መስመሮች ተሰምረው ከዚህ ማለፍ አይቻልም የሚል ጽሁፍ ሰፍሮባቸዋል።

የእጅ ማጽጃ (ሳኒታይዘርም) ግድግዳ ላይ ተንጠልጥሏል፤ ከሰዓታት ጥበቃ በኋላ ተራዬ ደርሶ ወደ ሐኪሜ ስገባ የታካሚ መቀመጫ ወንበሩ ከሌላው ጊዜ በተለየ ራቅ ብሎ ግድግዳ ተጠግቶ ነበር የተቀመጠው።

በአንድ በኩል ጥንቃቄያቸው የደኅንነት ስሜት ቢያሳድርብኝም በዚያው ልክ ጭንቀት ለቀቀብኝ። የኮሮናቫይረስ ሁሉም ቦታ በሰዉ ልክ የሚርመሰመስ ሲመስለኝ ምነው ዝም ብዬ ቤቴ ሆኜ ምጤን ብጠባበቅስ የሚል ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። ግን አላደረግኩትም።

በተለይም በመጨረሻዎቼ የእርግዝናዬ ሳምንታት የሐኪም የቅርብ ክትትል እንደሚያስፈልግ ያለፉት ሁለት እርግዝናዎች ስላስተማሩኝ ከባለቤቴ ጋር የራሳችንን ጥንቃቄ እያደረግን ለመቀጠል ተስማማን።

ከቤት ለመውጣት በማደርገው ዝግጅት አፌን ስለመሸፈንማ የእጅ ማጽጃ ስለመጠቀም ማሰብ የሚፈጅብኝ ጊዜ ቀላል አይደለም።

ጭንቀቴን የሚያባባሰው ደግሞ በጤና ባለሙያዎች ነፍሰጡሮች ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው የሚለው ሀሳብ ነው። "እንደው የልጆቼ አምላክ አደራህን" እያልኩ እስከመጨረሻው የቻልኩትን ያህል እየተጠነቀቅኩኝ ለክትትሌ ተመላለስኩኝ።

መስመር
የህጻን እግር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተደብቆ መውለድ

ከባለቤቴ ጋር ለመውለድ ሆሰፒታል ከገባሁ በኋላ በሠላም እስክገላገል ድረስ ለማንም ሰው እንዳይናገር ተስማማን፤ ምክንያታቻን ደግሞ ከዚህ በፊት ሁለቱ ልጆቻችን ሲወለዱ የነበረው የቤተሰባችን ልምድ ነው።

ገና ሆሰፒታል መግባቴን ሲሰሙ ብዙዎቹ የቤተሰባችን አባላት ወደ ሆሰፒታል መጥተው ከውጪ ተሰብስበው በጭንቀት ይጠባበቁ ነበር። እናም በዚህ ጊዜ ይህን ላለማድረግ ወሰንን።

በእርግጥ እኛ ባናስበውም በሆስፒታሉ ግድግዳ ላይ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለጊዜው ለእንድ ታካሚ የሚፈቀደው አንድ አስታማሚ ብቻ ነው የሚል መልዕክት በየቦታው ተለጥፎ ነበር። ይህ እንደማያቆማቸው ግን እርግጠኛ ነበርኩኝ።

እንዳይደርስ የለም የመውለጃዬ ቀን ደረሰ። አሁንም ከምጥ የሚስተካከል ሌላ ጭንቀት። ከዚህ በፊት በነበረኝ ልምድ በሆሰፒታሉ የምጥ ክፍል እንደእኔ በምጥ የተያዙ ሴቶች እና የሚንከባከቧቸው አዋላጅ ነርሶች ይበዙ ነበር።

ታዲያ አሁንስ እንዲህ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ ስሄድ ቫይረሱ ቢይዘኝስ? ቫይረሱ የያዛት ሴት በቅርብ እዚህ ወልዳ ቢሆንስ? በምጥ ላይ ሆኜ ራሴን አንዴት መጠበቅ እችላለሁ?. . . ብቻ ብዙ ጥያቄዎች ቢመላላሱብኝም መልስ ሳጣላቸው ፈጣሪዬን ብቻ ለመንኩ።

"እባክህን ጌታዬ ከልጆቼ እንዳትነጥለኝ፤ አዲስ ልጅ ትሰጠኛለህ ብዬ ያሉት እንዳይበተኑብኝ፣ ቤተሰቤን አደራህን በምህረትህ ጎብኘን" እላለሁ።

ነገር ግን ወደ ሆስፒታሉ ስገባ በአጋጣሚ ያለሁት ወላድ እኔ ብቻ መሆኔንን ሳውቅ ትንሽ ቀለል አለኝ። አልጋዎቹም ቢሆኑ ከወትሮው ዘርዘር ብለዋል።

የማይቀረው የጭንቁ ጊዜ ሲደርስና ምጡ እየተፋፋመ፣ ጭንቀቴም እያየለ ሲመጣ አጠገቤ ያለውን የአልጋ መደገፊያ ብረት ብርታት እንዲሰጡኝ ቁንጥጥ አድርጌ እይዝና ፋታ ሳገኝ የኮሮናቫይረስ እስከ አራት ቀን ይቆይበታል ሲባል የሰማሁትን ብረት መጨበጤ ታውሶኝ ሌላ ጭንቀት ሰውነቴን ይወረዋል።

አዋላጅ ነርሷ ደግሞ አጠገቤ ቁጭ ብላ በስልኳ ደቂቃ እየያዘች የቁርጠቴን ጥንካሬና የደም ግፊቴን እየለካች ትንፋሽ በረጅሙ እየሳብኩኝ እንድተነፍስ ስትነግረኝ በጣም እሳቀቅ ነበር።

ምክንያቱም ትንፋሼ በቀጥታ ወደእርሷ እንደሆነ ሳስተውል ለእርሷም መጠንቀቅ እንዳለብኝ እያሰብኩ ትንፋሼን ዋጥ አደርግና ሲከብደኝ ደግሞ ፊቴን ዞር አድርጌ በብርድ ልብሱ እየሸፈንኩ እተነፍሳሁ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ምጤ ሲታገስልኝ አልጋዬ ጎን ያስቀመጥኩትን ማጽጃ (ሳኒታይዘር) ከህመሜ ፋታ ባጋኘሁበት ቅጽበት ሁሉ እጄን ለማጽዳት መጠቀሜን አላቆምኩም።

የመጨረሻው የጭንቅ ጊዜ ሲደርስ ግን የሆንኩትም የጨበጥኩትም ምን እንደሆን አላስታውስም፤ ብቻ ያ ሁሉ ጭንቀት አልፎ ሁለቱን ልጆቼን ስወለድ ከነበረኝ ከምጥ ጊዜ እጅግ ባነሰ ሰዓት ሆስፒታል በገባሁ በሦስት ሰዓታት ውስጥ በሰላም ተገላገልኩኝ።

የአራስነት ጊዜ ለብቻ

ያን ጊዜ ምንም የማያውቁት ቤተሰቦቼም የምሥራቹን በስልክ ሰሙ፤ ከዚህ በፊት ወደቤት ስንመለስ እናቴ ነበረች ጨቅላውን አቅፋ እልልልልል እያለች የምትገባው፤ ጎረቤትም ተከትሎ እልልታውን ያቀልጠዋል፤ እቅፍ አድርጎ እየሳመ "እሰይ፣ እሰይ እንኳን ደስ ያለሽ! ያሳድግልሽ! ለቁም ነገር ያብቃልሽ!" እያለ መልካም ምኞቱን ያጎርፈዋል።

አሁን ግን የእናቴና የጎረቤቶቼ እልልታም ሆነ አነርሱም አልነበሩም። እኔ እና ባለቤቴ ብቻ ልጃችንን ይዘን ሹልክ ብለን እንደወጣን አዲሷን ልጃችንን ይዘን ቤታችን ገባን።

በአራስነቴ የመጀመሪያዎቹ ቀናት ልክ እንደ መጀመሪያ ጊዜ እንዴት እንደማደርግ ራሱ ግራ ተጋብቼ ነበር። እናቴ የአራስ ወግ ነው ጭንቅላትሽ ይደርቃል እያለች በግድ የምትቀባኝ ቅቤ ናፈቀኝ፤ ስዎች ተሰብስበው ገንፎ በትልቅ ድስት ተገንፎቶ ሲበላ ቤቱም በምርቃትና በጨዋታ ሲደምቅ ማየት ተመኘሁ።

የእኛ ቤተሰብ ደግሞ ብዙ ስለሆነ እኛ ብቻችንን እንኳን ስንሰባሰብ ቤቱ ይሞላ ነበር። በተለይ ደግሞ በወለድኩ በሰባተኛ ቀኔ ጎረቤትና ዘመድ አዝማድ ተስብስቦ የሚደረገው የገንፎ ዝግጅት በጣም ደስ ይለኝ ነበር፤ ሥነ ሥርዓቱን የወዳጆቼ መሰባሰቢያ እና የልጄ የምርቃት መቀበያ መሆኑን እንደጥሩ ዕድል እቆጥረዋለሁ።

አሁን ግን ይሄ ሁሉ ነገር በምናብ ብቻ ነው፤ ሁሉም ነገር በስልክ ብቻ ሆኗል። ያውም ደስታቸውን ገልጸው ሳይጨርሱ ወሬው ወደኮሮናቫይረስ ጉዳይ ይለወጣል። 'ይሄ መጥፎ ወረርሽኝ' የሚለው 'ከእንኳን ማሪያም ማረችሽ' ቀድሞ ዋነኛ ጉዳይ ሆኗል።

እናቴ እንጀቷ አልችል ቢላት "ግድ የለሽም ለአምስት ደቂቃ ልይሽና አመለሳለሁ" ትላለች፤ አንዳንዴ እንደማልቀስ ሲዳዳኝ ቶሎ ብዬ ስልኩን እዘጋባታለሁ።

መቼስ በእናት መታረስ ዓለም ነው ብዙ ሸክም ያቀላል፤ ግን ደግሞ በሽታ የመቋቋም አቅሟ የተዳከመው አረጋዊቷ እናቴ ወይም ጨቅላዋ ልጄ ቢታመሙብኝስ ብዬ ፈራሁ።

በተለይ ደግሞ በሽታው እስክ 14 ቀን ምልክት ላያሳይ ይችላል ሲባል ስለነበር እነዚያ ቀናት በጭንቀት ነበር ያለፉት።

ይኽው አሁን አንድም ሰው በአካል መጥቶ የተለመደውን የአራስ ጥየቃና ምርቃት ሳላገኝ አንድ ወር ሆኖኝ፤ መጪዎቹ ቀናትም እንዲሁ አልፈው የተሻለ ቀን እስኪመጣ ለሁላችንም ጤና ስል አራስነቴን በብቸኝነት አየገፋሁ ነው።

[* ስሟ ለዚህ ታሪክ ሲባል ተቀይሯል]

ኮሮና
Banner