ያልተነገረላቸው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀግና ሴቶች

An illustration of Cheng Benhua, a Chinese resistance fighter

የፎቶው ባለመብት, Davies Surya, BBC

እስቲ ለአፍታ የጦርነት ጀግኖችን ያስቡ። በጀግንነት ሲፋለሙ ያሰቧቸው ወንዶች ናቸው ሴቶች? በብዙዎች አእምሮ ጀብድ የፈጸሙ ሴቶች አይታወሱም። አርብ ዕለት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ ያበቃበት 75ኛ ዓመት ዕለት ነበር። እኛም በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጀብድ የፈጸሙ 8 ሴቶችን ልናስተዋውቃችሁ ፈቅደናል።

Presentational grey line 1

ቼንግ ቤንሁ፡ ሞትን በፈገግታ የተቀበለችው

ቼንግ ቤንሁ ቻይናዊ ጀግና ነበረች። ጃፓን እ.አ.አ. 1937 ላይ አገሯን ስትወር ቼንግ ከሌሎች ጋር ሆና ወራሪውን ጠላት ከአገሯ ለማባረር ታግላለች።

ቼንግ በስለት ተወግታ ከመገደሏ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት የተነሳችው ፎቶግራፍ ሰዎች ያለፍርሃት የትጥቅ ትግል እንዲያደርጉ መነሳሳትን የፈጠረ ነበር።

ፎቶግራፉን ያነሳው ጃፓናዊ ፎቶግራፍ አንሺ የቼንግን የመጨረሻ ሰዓታት መዝግቦ አስቀምጧል።

በጃፓን ጦር በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ ድብደባ ተፈጽሞባታል፤ በበርካቶች በተመሳሳይ ጊዜ ተገዳ ተደፍራለች፤ ለጠላቶቿ ግን አልተንበረከከችም።

ምንም እንኳ የቼንግ ሕይወት ቢያልፍም ከመሞቷ በፊት በተነሳችው ፎቶ ላይ በፈገግታ ተሞልታ እና እጆቿን ደረቷ ላይ አጣምራ አይኖቿ ካሜራውን እያዩ ነበር።

ቼንግን ለመዘከረም በጃፓን ወታደሮች ከ300 ሺህ በላይ ቻይናውያን በተገደሉበት ናንጂንግ ከተማ 5 ሜትር የሚረዝም ሃውልት ቆሞላታል።

ቼንግ በ24 ዓመቷ ነበር እ.አ.አ. በ1938 የተገደለችው።

Presentational grey line 1

ኖራ ኢናያት ካን፡ ላይዋ ልዕልት

An illustration of Noor Inayat Khan

የፎቶው ባለመብት, Davies Surya, BBC

ኖራ ኢናያት ካሃን የህንድ ልዕልት እና የብሪታኒያ ሰላይ ነበረች። ኖራ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የሕንዷን ማይሱሩ ከተማ ሲያስተዳድር ከነበረው ቲፑ ሱልታን የዘር ግንድ ትመዘዛለች።

ከሕንዳዊ የእስልምና እምነት አስተማሪ እና ከአሜሪካዊቷ ተዋናይት የተወለደችው ኖራ፤ ትውልድ እና እድገቷ ሩሲያ፣ ሞስኮ እንዲሁም ትምህርቷን የተከታተለችው ደግሞ ፈረንሳይ፣ፓሪስ ነው።

የቋንቋ ችሎታዋ የብሪታኒያ የደህንነት ኃላፊዎችን ቀልብ ገዛ። ኖራ ከብሪታኒያ ተነስታ በናዚ ጀርመን ቁጥጥር ሥር ወደሚገኘው ፈረንሳይ በፓራሹት አማካኝነት ገብታ የናዚ ጀመርን ወታደሮችን እንቅስቃሴ በተመለከተ ለእንግሊዝ መረጃ አቀብላለች፣ አጋር የነበሩትን ፈረንሳይ እና እንግሊዝ መካከል ግንኙነት እንዲፈጠር ረድታለች።

ኖራ አደገኛ የሚባለውን የሬዲዮ ኦፕሬተርነት ኃላፊነትን በብቃት ተወጥታለች። በጠላት ክልል ውስጥ ላለመያዝ በተደጋጋሚ መቀመጫዋን ትቀያይር ነበር።

በመጨረሻ ግን በናዚ ጀርመን ደህንነት ኃይል ተያዘች። ኖራ ለእስር በተዳረገችበት ወቅት በተደጋጋሚ ከእስር ለማምለጥ ሙከራ አድርጋለች።

ለማምለጥ በሞከረች ቁጥር የሚደርስባት ስቃይ እና እስር በከፋ ሁኔታ ይባባስ ነበር።

ናዚ ጀርመኖች የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ኖራ መረጃዎችን እንድታወጣ በርካታ ጥረቶችን ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ጀርመኖች 'ሜድላይን' ከሚባለው የሚስጥር ስሟ ውጪ ሕንዳዊ ስለመሆኗ እንኳ ማወቅ አልቻሉም።

እ.አ.አ. መስከረም 1944 ላይ ኖራን ጨምሮ ሌሎች ሶስት ሴቶች፣ ጀርመን ወደሚገኝ ማሰቃያ ካምፕ ከተወሰዱ ከቀናት በኋላ ተረሽነዋል።

ኖራ ለጀብዱ ስራዎቿ የፈረንሳይ እና ብሪታኒያ መንግሥታት ሽልማት አበርክተውላታል። እርሷን የሚዘክር ሃውልትም በለንደን ከተማ ቆሟል።

Presentational grey line 1

ሊዩድሚል ፓቨሊቼንኮ፡ የሞት ሴት

An illustration of Lyudmila Pavlichenko, a Soviet sniper

የፎቶው ባለመብት, Davies Surya, BBC

ሊዩድሚል ፓቨሊቼንኮ ባሪክ እጅግ ውጤታማ ከነበሩ አልሞ ተኳሾች መካከል አንዷ ነበረች። ናዚ ጀርመን እ.አ.አ. 1941 የተባበሩት ሶቬት ህብረትን በወረረበት ወቅት 306 ጠላቶቿን ከርቀት መትታ ጥላለች። ከእነዚህም መካከል ቀላል የማይባሉት እንደ እርሷ አልሞ ተኳሾች ነበሩ።

ከአልሞ ተኳሾች ጋር የነበራት ግብግብ 'ሌዲ ዴዝ' የሞት ሴት፣ የሚል ስም አሰጥቷታል።

የናዚ አልሞ ተኳሾች ሊያገኟት አልቻሉም፤ ይሁን እንጂ በሞርታር ጥይት ተመትታ በደረሰባት ጉዳት አልሞ ተኳሽ ሆና መቀጠል አልቻለችም። ይህ ግን አገሯ ከጠላት ጋር የምታደርገውን ፍልሚያ ከማገዝ አልገደባትም።

የተለያዩ ተልዕኮችን በመውሰድ በመላው ዓለም የተጓዘችው ሊዩድሚል በሥራዋ አማካኝነት ከወቅቱ ፕሬዝደንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ጋር ተገናኝታለች።

ሊዩድሚል ለጀብድ ሥራዋ የወርቅ ኮከብ ተሸላሚ ብትሆንም ሕይወቷ ካለፈ በኋላ ከሩሲያ የታሪክ መዝገብ ላይ ስሟ እንዲሰረዝ ተደርጓል።

"የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሶቬት ታሪክ ውስጥ ጀግና ተብለው በታሪክ መዝገብ ላይ የሰፈሩት ወንዶች ብቻ ናቸው። ሴቶች የዛኔ የታሪክ አካል አይደሉም" ስትል የጾታ እኩልነት ተሟጋቿ ኢራይና ስላቪስካ ለቢቢሲ ተናግራለች።

Presentational grey line 1

ናንሲ ዌክ፡ ነጯ አይጥ

An illustration of Nancy Wake, an Australian spy during WW2

የፎቶው ባለመብት, Davies Surya, BBC

የተወለደችው ኒው ዚላንድ ያደገችው ደግሞ አውስትራሊያ ነው። ናንሲ አደገኛ ተዋጊ እና አማላይ፣ ጠጪ እና ለጠላቷ ናዚ የራስ ምታት ነበረች።

ናንሲ ገና የ16 ዓመት ታዳጊ ሳለች ከትውልድ አገሯ በመጥፋት ወደ ፈረንሳይ አቀናች። በዚያም የጥንታዊ ግብጽ ቋንቋ እችላለሁ ብላ በመዋሸት በአንድ የፈረንሳይ ጋዜጣ ላይ ጋዜጠኛ ሆና ተቀጠረች።

ከአንድ ፈረንሳይ ዜጋ ጋር በፍቅር የወደቀችው ናንሲ በፍቅር ተጣምራ ትዳር ለመመስረት ብዙ ጊዜ አልወሰደባትም። በማርሴ ከተማ ሳለች ጀርመኖች ፈረንሳይን እ.አ.አ. 1939 ላይ ወረሩ።

ናንሲ የፈረንሳይ አርበኞችን ተቀላቀለች። በተለያየ አጋጣሚ በጀርመን ጦር ተከበው የነበሩ ፈረንሳውያን ታጋዮችን እያስመለጠች ወደ ስፔን አሽሽታለች።

ከብሪታኒያ በመነሳት በፓራሹት ከአውሮፕላን እዘየለለች በፈረንሳይ በርካታ ተልዕኮችን በድል ተወጥታለች። ከአንድ የጀርመን ካምፕ ጠባቂ ጋር በጨበጣ ውጊያ ድል ነስተዋለች። እስከ 500 ኪ.ሜትር ድረስ ወደ ጠላት ድንበር ዘልቃ በመግባት በማይታመኑ አጫጭር ጊዜያት ውስጥ የተለያዩ ተልዕኮችን በስኬት ተወጥታለች።

ድምጽ ሳታሰማ ጠላት መንደር ገብታ በመውጣት ክህሎቷ የተነሳ "ነጯ አይጥ" የሚል ስያሜን በጀርመን ጦር አሰጥቷታል።

በ98 ዓመቷ እ.አ.አ. 2011 ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው ናንሲ፤ ለጀብድ ሥራዋ የተለያዩ ሽልማቶችን ተቀብላለች።

Presentational grey line 1

ጄን ቫያል፡ ዘጋቢ፣ ሰላይ፣ ፖለቲከኛ

ጄን ቫያል ትውልዷ በአፍሪካዊቷ ኮንጎ ሪፐብሊክ ቢሆንም በልጅነቷ ወደ ፈረንሳይ አቅንታለች። ጋዜጠኛ ሆና እየሰራች ሳለች ነበር ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተቀሰቀሰው።

መኖሪያዋ የነበረችው ፓሪስን ጥላ በመሰደድ በደቡባዊ ፈረንሳይ ተደራጅተው የነበሩትን የፈረንሳይ ነጻነት ታጋዮችን ተቀላቀለች።

ጄን የምትልካቸው መልዕክቶች በኮድ የተቆለፉ ስለነበሩ ጠላት እጅ ሲደርሱ ከተራ አህዝ እና የቃላት ድርዳራ ውጪ ትርጉም የሚሰጡ አልነበሩም።

ጄን የናዚ ወታደሮችን እንቅስቃሴ እየሰለለች ለአጋር አገሮች እና ለነጻነት ታጋዮቹ ትልክ ነበር። እ.አ.አ. 1943 ላይ በጠላቶቿ እጅ ወደቀች። ከዚያም የአገር ክህደት የሚል ክስ ተመሰረተባት።

በናዚ ጀመርን ከተያዘች በኋላ ወደ ማርሴ የሴቶች እስር ቤት ተልካ የጉልበት ሥራ ስትሰራ ነበር። ከእስር ቤት አምልጣ ይሆን በምህረት ተለቃ ግልፅ ባይሆንም ጄን ሁለተኛው ዓለም ጦርነት ህይወቷን አልነጠቃትም።

እ.አ.አ. 1947 ላይ የፈረንሳይ ሴኔት አባል ሆና ተመርጣ ነበር።

Presentational grey line 1

ሄዲ ላማር : የሆሊውዷ በቷ ገዳይ

Hollywood actress Hedy Lamarr

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ትውልደ ኦስትሪያዋ ሄዲይ ላማር በትወና ስራዋ ዝናዋ የናኘ መልከ መልካም ሴት ነበረች። የሆሊውዷ እንቁ 6 ባሎች ነበሯት።

ሄዲ የመጀመሪያ ትዳሯ ባይጥማት ከቬይና ተነስታ ወደ ፓሪስ ከዛም ወደ ለንደን አቀናች። በለንደንም ዝነኛ የነበረውን የጥበብ ሰው ሉዊስ ሜይር ጋር ተዋወቀች።

በሆሊውድ መስራት እንድትችል የሚያስችላትን ኮንትራትም አስፈረማት። "የዓለማችን ውቧ ሴት" በማለት ያስተዋውቃት ጀመር።

የተሳተፈችባቸው 30 ፊልሞች ዝነኛ አድርጓታል። የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀግና ያስባላት ግን የፊልም ስራዎቿ አልነበሩም። የፈጠራ ሥራዋ እንጂ።

የፈጠራ ሥራዋ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ብሪታኒያ የጠላቶቻቸውን መርከቦች ለማጥቃት ጥቅም ላይ የሚያውሏቸው ተተኳሾች (ቶርፒዶ) ፍሪክዌንሲዎች በጠላት እንዳይጠለፉ የሚያስችል ስርዓት ነበር።

ቶርፒዶዎቹ ፍሪኩዌንሲያቸውን በመቀያየር በጠላት እንዳይታፈኑ ወይም እንዳይጠለፉ አስችላለች።

ምንም እንኳ ለፈጠራ ስራዋ እውቅና ባይቸራትም፤ የፈጠራዋ ግብዓት የሆኑ ሃሳቦች በብሉቱዝ እና ዋይፋይ ቴክኖሎጂዎች ላይ ተንጸባርቀዋል።

Presentational grey line 1

ማይ ዪ: በጎራዴ እና መርዝ

Mya Yi photo portrait

የፎቶው ባለመብት, Ludu collection

የማይ ዪ ትግል የጀመረው ጃፓኖች በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት በርማን ከመውረራቸው በፊት ነበር።

ለአገሯ በርማ ነጻነት ድምጿን ከፍ አድርጋ ትናገር ነበር። የእንግሊዝን ቅኝ ገዢነት ተቃውማለች።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትም በእግሯ በጠላት የተያዙ ስፍራዎችን እያቆራረጠች ጎራዴ እና መርዝ በበልቃጥ ይዛ ትጓዝ ነበር።

በሕንድ ጃፓኖች ምን ያህል በበዛ ጭካኔ ሕዝቡን እያሰቃዩ እንደሆነ የሚገልፅ በራሪ ወረቀቶችን በርማዎች በሚገኙበት ስፍራ ትበትን ነበር።

በፓራሹት መውረድ ስልጠና የወሰደችው ዩ ምንም እንኳ የመጀመሪያ ልጇን ከወለደች በኋላ ከትዳር አጋሯ ጋር ወደ በርማ ለመመለስ ብታቅድም፣ የመጣላትን እድል ለሌላ ተዋጊ አሳልፋ በመስጠት ጦርነቱ ካለቀ በኋላ እ.አ.አ. በጥቅምት 1945 ተመልሳለች።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ቢሆን ለነፃነት እና ከዚያም በኋላ ወታደራዊ መንግሥትን ታግላለች።

Presentational grey line 1

ራሱና ሰይድ፡ ሴቷ አንበሳ

rasuna

የፎቶው ባለመብት, BBC/Davies Surya

ኢንዶኔዢያዊቷ ራሱና ሰይድ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ካሉት ጀግኖች ለየት ያለች ነበረች። በኢንዶኔዢያ የነጻነት ትግል ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደነበራት ይነገርላታል።

ለእሷ ዋነኛ ጠላቷ ወራሪው የጃፓን ኃይል ሳይሆን የደች ቀኝ ገዢዎች ነበሩ። ገና በወጣትነቷ ነበር ወደ ፖለቲካ በመግባት የራሷን ፓርቲ የመሰረተችው። ፓርቲውም የኢንዶኔዢያ ሙስሊም ማህበር የሚባል ሲሆን ኃይማኖትና ህብረ ብሄራዊነትን የሚሰብክ ነበር።

በአንድ ወቅት የቅኝ ገዢው የደች ባለስልጣናትና ወታደራዊ ኃላፊዎችን የሚወርፍ ንግግር በማድረጓ ደግሞ ብዙዎች አይረሷትም። በዚህም ሴቷ አንበሳ የሚል ስያሜ ማግኘት ትችላለች።

ይህንን ንግግር ባደረገችበት ወቅት ወዲያው በቁጥጥር ስር የዋለች ሲሆን ለ 14 ወራትም ታስራ ነበር።

ጃፓኖች በጦርነቱ ተሸንፈው ከኢንዶኔዢያ ከወጡ በኋላም አገሪቱ ነጻነቷን ማግኘት አልቻለችም። የደች ቅን ገዢዎች ተመልሰው መጥተው ነበር። በዚህም ምክንያት ለአራት ዓመታት የዘለቅና ብዙ ደም ያፈሰሰ ጦርነት ተደርጓል።

ታዲያ ራሱና ሰይድ በዚህ ጦርነት ላይ ቁልፍ ሚና እንደነበራት ይነገራል። በዋና ከተማዋ ጃካርታም አንድ መንገድ በእሷ ስም ተሰይሟል።