ሰዎች እጃቸውን የማይታጠቡበትን ሥነ ልቦናዊ ምክንያት ያውቃሉ?

ፒት ሄግሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ለ10 ዓመታት እጁን ታጥቤ አላውቅም ያለው ዜና አንባቢ ፒት ሄግሴት፤ በኋላ ግን ቀልዴን ነው ብሏል

የፎክስ ኒውስ ዜና አንባቢ ፒት ሄግሴት “እጄን ለአስር ዓመታት አልታጠብኩም” ማለቱን ተከትሎ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበር አይዘነጋም።

ከአምስት ዓመት በፊት ተዋናይት ጄኔፈር ሎውረንስ ከመጸዳጃ ቤት ስትወጣ እጇን የመታጠብ ልምድ እንደሌላት መናገሯም ይታወሳል።

ፒት እና ጄኔፈር “እጃችንን አንታጠብም” ካሉ በኋላ መልሰው ደግሞ “ስንቀልድ ነው” ያሉትን አስተባብለዋል።

ሆኖም ግን እጅ መታጠብን አምርረው የሚቃወሙ ሰዎች እንዳሉ ያውቃሉ?

የኖርዝ ኬሮላይናው ሪፐብሊካን የሕዝብ እንደራሴ ቶም ቲልትስ፤ የሬስቶራንት ተቀጣሪዎች እጃቸውን ይታጠቡ መባሉ አላስፈላጊ ድንጋጌ ነው ያሉት ከአምስት ዓመታት በፊት ነበር።

ከመጸዳጃ ቤት ሲወጡ እጃቸውን የማይታጠቡ ሰዎች እንዳሉ ሳትታዘቡ አልቀራችሁም።

እአአ 2015 ላይ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ በመላው ዓለም መጸዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ እጃቸውን የሚታጠቡት 26.2 በመቶ ሰዎች ብቻ ናቸው።

ቀላል ግን በቀላሉ የሚረሳ ልማድ

በለንደን የኅብረተሰብ ጤና ምሁሩ ሮበርት አውገር፤ እጅ መታጠብ “ቀላል ልማድ ይመስላል” ይላሉ።

“እጅ መታጠብ በቀላሉ የሚለመድ ቢመስልም፤ ለ25 ዓመታት ያህል ሰዎች እጃቸውን መታጠብ እንዲያዘወትሩ ለማድረግ ብንሞክርም፤ እጃቸውን የሚታጠቡ ጥቂቶች ናቸው።”

ድህነት በተንሰራፋባቸው አገራት ሳሙናና እጅ መታጠቢያም በስፋት ስለማይገኝ፤ ብዙሃኑ እጃቸውን አለመታጠባቸው ላያስገርም ይችላል።

በታዳጊ አገራት 27 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ብቻ እጅ መታጠቢያ ያገኛል። በተቃራኒው እጅ መታጠቢያ እንደልብ በሚገኝባቸው ያደጉ አገራት፤ ከመጸዳጃ ቤት ሲወጡ እጃቸውን የሚታጠቡ 50 በመቶ ብቻ ናቸው።

ሕይወት አዳኙ እጅ መታጠብ

በሰው ልጅ ታሪክ ከተፈጠሩ ሕይወት አዳኝ ተግባሮች አንዱ እጅ መታጠብ ነው።

እጅ መታጠብ በ1850ዎቹ እውቅናው እየጨመረ ከመጣ ወዲህ፤ ሰዎች ዘለግ ላለ ጊዜ ምድር ላይ መኖር ችለዋል። ወረርሽኞችን ለመከላከልም እጅ መታጠብ አንዱ መንገድ ነው።

እአአ 2006 ላይ የወጣ ጥናት፤ አዘውትሮ እጅ መታጠብ በመተንፈሻ አካላት በሽታ የመያዝ እድልን ከ6 እስከ 44 በመቶ እንደሚቀንስ ያሳያል።

የኮቪድ-19 ስርጭት ከሰዎች እጅ የመታጠብ ልማድ ጋር ግንኙነት እንዳለው ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

ታዲያ ለምን አንዳንድ ሰዎች እጃቸውን አይታጠቡም?

እጅ መታጠብ አለመፈለግ ከሰዎች ሥነ ልቦና ጋር ይተሳሰራል። ቀጣዮቹ ነጥቦች ማብራሪያ ይሰጧችኋል።

እጅን መታጠብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እጅን በተደጋጋሚ በደንብ መታጠብ ኮሮናቫይረስን የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎችን ከመከላከል ይረዳል

1. የ‘ክፉ አይነካኝም’ ተስፋ

መጥፎ ነገር አይደርስብንም የሚል እምነት ያላቸው በርካቶች ናቸው። በብዙ ማኅበረሰቦች ዘንድ ክፉ ነገር የሚመጣው በሌላ ሰው እንጂ በእኔ ላይ አይደለም የሚል እምነት ይስተዋላል።

ይህ አይነቱ አመለካከት ሲጋራ በሚያጨሱ ሰዎች ዘንድም ይታያል። የእኔ ትዳር አይፈርሰም፣ እኔን ካንሰር አይዘኝም የሚሉም ጥቂት አይደሉም።

እጅ አለመታጠብም ከዚሁ ጋር ይገናኛል።

ይህ አመለካከት ያላቸው የህክምና ተማሪዎች እና ምግብ አዘጋጆችም እጃቸውን ከመታጠብ ይቆጠባሉ።

2. ባህል

እጅ መታጠብ ከባህል ጋር የተቆራኘ ነው። በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ እጅ መታጠብ የሚሰጠው ዋጋ ሰዎች እጃቸውን ለመታጠባቸው ወይም ላለመታጠባቸው ምክንያት ይሆናል።

64,002 ሰዎችን ከ63 አገሮች ያሳተፈ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ከቻይና፣ ከጃፓን፣ ከደቡብ ኮርያ እና ከኔዘርላንድስ የተጠየቁ ሰዎች መጸዳጃ ቤት ከተጠቀሙ በኋላ እጃቸውን በሳሙና የመታጠብ ልማድ እንዳላቸው የተናገሩት ከግማሽ በታች ናቸው።

በተቃራኒው 97 በመቶ የሚሆኑ የሳኡዲ አረቢያ ዜጎች እጃቸውን መታጠብ እንደሚያዘወትሩ ተናግረዋል።

የሕብረተሰብ ጤና ምሁሩ ሮበርት እንደሚሉት፤ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ እጃቸውን መታጠብ ያዘወትራሉ።

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፤ 65 በመቶ ሴቶች እና 52 በመቶ ወንዶች እጃቸውን ይታጠባሉ።

“እጅ መታጠብ ከሥነ ልቦና እና ከባህል ጋር ይተሳሰራል። እንድ ነገር የምናከናውነው ሌሎች የሚያደርጉትን እና እኛ እንድናደርግ የሚጠብቁትን በማየት ነው” ይላሉ ተመራማሪው።

እጃቸውን የሚታጠቡ ህጻናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጥናቶች ሴቶች ከወንዶች ይልቅ እጃቸውን ይታጠባሉ

3. ቀልብ እና ሙከራ

እጅ መታጠብን ሀኪሞችም ቸል የሚሉበት ጊዜ አለ።

እአአ 2007 ላይ አውስትራሊያ ውስጥ የተሠራ ጥናት፤ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ህክምና ከመስጠታቸው በፊት እጃቸውን የታጠቡት 10 በመቶ ጊዜ ብቻ እንደሆነና ከህክምና በኋላ እጃቸውን የታጠቡት ደግሞ 30 በመቶ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ያመለክታል።

በቅርቡ የተሠሩ ጥናቶችም ተመሳሳይ ውጤት አሳይተዋል።

በኩቤክ የህክምና ባለሙያዎች እጃቸውን የሚታጠቡት 33 በመቶ ጊዜ ብቻ መሆኑን ባለፈው ዓመት የተሠራ ጥናት ይጠቁማል።

እጅ መታጠብ በስፋት በተለመደበት ሳኡዲ አረቢያ ሳይቀር የህክምና ባለሙያዎች ብዙ ጊዜ እጃቸውን አይታጠቡም።

2008 ላይ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ እጃችንን አንታጠብም ካሉት ሀኪሞች አብዛኞቹ በሙከራ የሚያምኑ ናቸው። በተቃራኒው ቀልባችንን እናምነዋለን ያሉ ሀኪሞች በብዛት እጃቸውን እንደሚታጠቡም ተስተውሏል።

ይህ የሚያሳው አንድ ሰው እጁን እንዲታጠብ ለማሳመን መከራከሪያ ነጥቦች መደርደር እንደማያዋጣ ነው።

ባለፈው ወር ብራዚል ውስጥ የተሠራ ጥናት ይህንን መላ ምት ያጠናክራል። በቀልብ የሚመሩ ወይም ልባም የተባሉ ሰዎች አብዝተው እጃቸውን እንደሚታጠቡና ማኅበራዊ ርቀታቸውን እንደሚጠብቁ ታይቷል።

4. መጠየፍ

አውስትራሊያዊው የሥነ ልቦና ተመራማሪ ዲክ ስቲቨንሰን እንደሚሉት፤ ሰዎች አንድ ነገር ሲቀፋቸው፤ ከዚያ ነገር ጋር ንክኪ ላለማረጋቸው ጥሩ ምክንያት ይሆናል።

ለምሳሌ አንድ ሰው ምግብ ውስጥ ነፍሳት ቢያይ ስለሚቀፈው አይመገበውም።

እንደ ማንኛውም ስሜት አንድን ነገር መጠየፍ ከሰው ሰው ይለያያል።

ጥዩፍ የሆኑ ሰዎች በፖለቲካው መስክ ወግ አጥባቂ የመሆን አዝማሚያ አላቸው።

ብዙም የማይጠየፉ ሰዎች፤ እጃቸውን መታጠብ እንደማያዘወትሩ፣ ቢታጠቡም በቅጡ እጃቸውን እንደማያጸዱ ጥናቶች ያመለክታሉ።

በሄይቲ እና በኢትዮጵያ የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ሰዎች እጃቸውን ለመታጠብ ምክንያት የሚሆናቸው የጤና ጉዳይ ሳይሆን አንድን ነገር የመጠየፍ ወይም ያለመጠየፋቸው ጉዳይ ነው።

ሰዎች እጃቸውን እንዲታጠቡ ምን ይደረግ?

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የጤና ባለሙያዎች፣ በጎ አድራጊዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እጅ የመታጠብ ዘመቻን ሲያበረታተቱ ነበር።

እጅ አለመታጠብ ከሥነ ልቦና ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ተግባር እንደመሆኑ እነዚህ ንቅናቄዎች ምን ያህል ውጤታማ ይሆናሉ?

ከአስራ አንድ ዓመታት በፊት የተሠራ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ሰዎች እጃቸውን እንዲታጠቡ ለማድረግ፤ እጅ መታጠብን ውብ ተግባር አድርጎ ማቅረብ ብዙ አያዋጣም። እንዲያውም ሰዎች እጃቸውን አለመታጠባቸው አስጸያፊ እንደሆነ ማሳየት ውጤታማ ነው።

በጥናቱ ወቅት፤ አስጸያፊ ትምህርታዊ ቪድዮ እንዲመለከቱ የተደረጉ ተማሪዎች ከሳምንት ጊዜ በኋላ፤ ቆሻሻ ነገር ነክተው ምግብ እንዲበሉ ሲጠየቁ፤ ከመመገባቸው በፊት እጃቸውን ለማጽዳት ተነሳሽነት አሳይተዋል።

በጥናቱ ወቅት አስጸያፊውን ቪድዮ ያላዩ ተማሪዎች ግን ቆሻሻ ነገር ከነኩ በኋላ መታጠብ እንፈልጋለን አላሉም።

የሥነ ልቦና ተመራማሪው ዲክ፤ ሰዎች እጃቸውን እንዲታጠቡ የሚያነሳሱ ማስታወቂያዎች መሥራትን ያበረታታሉ።

አንድ ሰው እጁን መታጠን ሲያዘወትር ከልምዶቹ አንዱ ይሆናል።

የኅብረተሰብ ጤና ምሁሩ ሮበርት በበኩላቸው፤ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ብዙዎች እጅ መታጠብ እያዘወተሩ ቢሆንም ምን ያህል ቀጣይነት ይኖረዋል? የሚል ጥያቄ አላቸው።

ምናልባትም ለተወሰነ ጊዜ፤ እንደ ዜና እንባቢው ፒት እና ተዋናይቷ ጄኔፈር፤ እጃችንን አንታጠብም ብለው የሚኩራሩ ታዋቂ ሰዎች አናይ ይሆናል።

ኮሮና
Banner