በሊባኖስ ለሽያጭ የቀረበችው ናይጄሪያዊት ተረፈች

ለሽያጭ የቀረበችው ግለሰብ ማስታወቂያ

የፎቶው ባለመብት, Screengrab of advertisemnt

በሊባኖስ ለሽያጭ ቀርባ የነበረችው ናይጄሪያዊት ከመሸጥና ከመለወጥ ተርፋለች።

የሽያጯ ማስታወቂያ በፌስቡክ ላይ ወጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ከቀናት በኋላም ማስታወቂያውን በመለጠፍ ተሳትፏል የተባለ ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውሏል።

የግለሰቧ የሽያጭ ማስታወቂያ በናይጄሪያውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።

የዲያስፖራ ናይጄሪያውያን ኮሚሽን ሊቀ መንበር አቢኬ ዳቢሪ ኤሬዋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለሽያጭ ቀርባ የነበረችው የ30 አመቷ ናይጄሪያዊት አሁን በደህና ሁኔታ ላይ እንዳለችና ቤይሩት ውስጥ በሚገኘው የናይጄሪያ ኤምባሲም እንደምትገኝ አረጋግጠዋል።

ሊቀመንበሩ አክለውም የሊባኖስ ባለስልጣናት እንዳዳኗት ገልፀው ነገር ግን በምን መንገድ እንደሆነ ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥበዋል። ሆኖም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መዛመትን ለመቆጣጠር የተላለፈው የቤት መቀመጥ ውሳኔ ሴትዮዋን ፈልጎ ለማግኘት እንደረዳ ገልፀዋል።

በቤት ሰራኝነት የምትተዳደረውን ይህችን ግለሰብ በአንድ ሺ ዶላር ለመሸጥም ፌስቡክ ላይ ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር። በማስታወቂያው ላይም የግለሰቧ የፓስፖርት ፎቶ በግልፅ የሚታይ ሲሆን በርካታ ሰዎች መጋራታቸውን ተከትሎም፤ ቁጣና ውግዘትም እየተስተናገደ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያሳየው ከናይጄሪያ እንዲሁም ከሌሎች አፍሪካ አገራት ታዳጊ በተለያየ የእድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች በአዘዋዋሪዎች እንደሚሸጡ ነው።

ብዙዎችም በአውሮፓና በእስያ የተሻለ ስራ ታገኛላችሁ በሚል ከቤታቸው ተታለው ወጥተው በቤት ሰራተኝነት እንዲሁም በወሲብ ንግድ እንደሚሰማሩና ብዙዎችም ለብዝበዛ እንደሚዳረጉ የተገኘው መረጃ ያሳያል።