ኮሮናቫይረስ በኢኳዶር፡ በኮሮና ቫይረስ ሞተዋል የተባሉት "አልሞትኩም እህቴ ጋር ደውሉልኝ" አሉ

ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ቤተሰቦች ሃዘናቸውን ሲገልፁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ክፉኛ በኮሮናቫይረስ በተጠቃችው በላቲን አሜሪካዊቷ አገር ኢኳዶር ሆስፒታሎች በግርግር፣ በተረበሹና ሃዘን በተሞላባቸው ዜጎቿ ተሞልተዋል።

አብዛኞቹ በኮሮናቫይረስ ሞተዋል የተባሉ የቤተሰቦቻቸውንና የወዳጆቻቸውን አስከሬን ለመውሰድ ነው የሚመጡት።

በዚህም መካከልም አንዳንድ አስደንጋጭ ዜናዎች መሰማታቸው አልቀረም። ከሰሞኑ ሞተዋል የተባሉ ሴት ሆስፒታሉ ማንነታቸውን በማሳሳቱ ምክንያት በህይወት መገኘታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

የ74 ዓመቷ የዕድሜ ባለፀጋ አልባ ማሩሪ ቤተሰቦች መሞታቸውን የተረዱት ባለፈው ወር ነበር፤ ጭራሽ ሆስፒታሉ በባህሉ መስረት እንደሚደረገው አስከሬናቸውን አቃጥሎ አመዳቸውንም ለቤተሰብ ልኳል።

ነገር ግን ማሩሪ ለሦስት ሳምንታት እራሳቸውን ስተው [ኮማ] ከቆዩ በኋላ ነቅተው ዶክተሮቹን ለእህታቸው እንዲደውሉላቸው ጠይቀዋል።

የአስከሬኖች መጥፋት

ማሩሪ በኢኳዶር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ማዕከል በምትባለው የጓያኩል ከተማ ወደሚገኘው ሆስፒታል በኮሮናቫይረስ ታመው ነው የገቡት።

በከተማዋ ውስጥ ሆስፒታል ሳይደርሱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በየቤታቸው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ባለስልጣናቱ አስከሬኖችን መሰብሰብ ከብዷቸዋል።

በርታና ቤተሰቦቿ

17 ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት ባላት ኢኳዶር 22 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል፤ ስድስት መቶ ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል።

ይሄ ግን በሆስፒታል ውስጥ የተመዘገበ መረጃ ነው፤ በቤታቸው የሞቱ ሰዎች ቁጥር በሺህዎች የሚቆጠር ነው ተብሏል።

ኢነስ ሳሊናስና ባለቤቷ ፍላደልፊዮ መጋቢት 21/2012 ዓ.ም ነው ህይወታቸው ያለፈው።

ቤተሰቦቻቸው በኮሮናቫይረስ ለሞቱ ሰዎች በሚደረገው ጥንቃቄ መሰረት አስከሬኖቹን እንዲያነሱ ለባለስልጣናቱ ደውለው ቢያሳውቁም አራት ቀናት ያህል መጠበቅ ነበረባቸው።

ከመጡም በኋላ በፕላስቲክ ጠቅልለው ወሰዷቸው፤ እናም ሲቀበሩ እንደሚያሳዉቋቸው እንደነገሯቸውም የሟቿ እህት በርታ ትናገራለች።

ነገር ግን ባለስልጣናቱም ሳይደውሉ የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ።

እናም እነበርታ ግራ ቢገባቸውም ጉዳዩን ለመንግሥት ባለስልጣናት አሳውቀዋል፤ አስከሬኖቹን ምን እንዳረጓቸው እንዲያሳውቋቸውም ደብዳቤ አስገብተው እየጠበቁ ነው።

የጉያኪል ከተማ

የፈራረሰ የጤና

የነበርታ ትግል የአንድ ቤተሰብ ታሪክ ብቻ አይደለም በተቃራኒው በኢኳዶር ውስጥ የብዙ ቤተሰቦችን ታሪክ የሚወክል ነው።

በርካታ ቤተሰቦች አስከሬኖችን ፍለጋ ወደ ሆስፒታሎችና ወደ መካነ መቃብሮች ይሄዳሉ፤ ፖሊስ ጋር ይደውላሉ።

በጓያኩል የተከሰተው ከፍተኛ የሞት አሃዝ ከተማዋ ከምትቋቋመው በላይ በመሆኑ የአገሪቱን የጤና ሥርዓት ፍርስርሱን አውጥቶታል።

በርካታ ሆስፒታሎች አስከሬኖችን ከአገልግሎት ውጭ ወደሆኑ የመጋዘን ቦታዎች ልከዋል። አስከሬኖቹም በመጋዘኖቹ ውስጥ እየበሰበሱ ነው።

የቤተሰቦቻቸውንም አስከሬን ለማግኘት ማገላበጥ ይኖርባቸዋል፤ የተደራረቡ አስከሬኖችን ማንሳትና መጣልም ግዴታ ሆኖባቸዋል።

ዳሪዮ ፊጉኤሮዋ የእናቱን አስከሬን ለማግኘት አሰቃቂ ያለውን በርካታ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን ማገላበጥ ነበረበት።

"ለቀናት ያህል የእናታችንን አስከሬን ለመቀበል ሆስፒታል እየጠበቅን ነበር፤ ምላሽ የሚሰጠን ስናጣ ሌሎች አስከሬን ከሚጠብቁ ሰዎች ጋር በአንድነት ተሰባስበን አንደኛውን ጠባቂ አስከሬኑ ወደተቀመጠበት ቦታ እንዲወስደን ጫና አደረግንበት።"

"የፊት ጭምብልና ጓንት አጠለቅንና አስከሬኖቹ ወደተቀመጡበት ክፍል ገባን። አስከሬኖቹ የተቀመጡበት መንገድ አሰቃቂ ነው፣ በጣም የሚያበሳጭና የሚያሳዝን ነው። አስከሬኖቹ በፕላስቲክ ተጠቅልለው አንዱ ባንዱ ላይ ተደራርቧል" ይላል።

ተአምር

በዚህ ሁሉ ቀውስ መካከል የማሩሪ በህይወት መኖር ብዙዎችን አስደምሟል።

የቤተሰባቸው ደስታ ይህ ነው የሚባል አይደለም፣ በቃላት መግለፅም ከብዷቸዋል። ግራ የገባቸው ቢኖር የማሩሪ ተብሎ የመጣው አመድ የማን ነው የሚለው ጥያቄን መመለስ አለመቻላቸው ነው።

ከፍተኛ ትኩሳትና ለመተንፈስ በመቸገራቸው ሆስፒታል የገቡት ማሩሪ መጋቢት 18/2012 ዓ.ም ሞቱ ተብሎ ሆስፒታሉ ለቤተሰባቸው አረዳቸው።

ቤተሰባቸውም አስከሬን ማስቀመጫ ክፍል ተወስደው በሽታው እንዳይዛመት በሚልም ራቅ ብለው እንዲያዩ ተደረጉ።

"ፊቷን ማየት ፈራሁኝ" የሚለው የእህታቸው ልጅ ጄይሚ ሞርላ "ከአስከሬኑ በአንድ ሜትር ተኩል ርቀት ላይ ነው የነበርኩት። ካየሁት አስከሬን ጋር ፀጉራቸው ተመሳሳይ ነው። የቆዳቸው ቀለምም እንዲሁ" በማለት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግሯል።

የማሩሪ የተባለውም አስከሬን ተወስዶ ተቃጠለ፤ እንዲሁም አመዳቸውም ለቤተሰቡ ተላከ።

በወቅቱ ራሳቸውን የማያውቁት ማሩሪ ከሦስት ሳምንታት እራሳቸውን ስተው ከቆዩ በኋላ እህታቸው ጋር እንዲደውሉ ዶክተሮቹን ጠየቁ።

"ተአምር ነው። ለወር ያህልም ሞታለች ብለን እያዘንን ነበር" ያሉት እህታቸው አሩራ "የማን እንደሆነ የማናውቀው አመድ ቤታችን አለ" ብለዋል።

የጉያኪል ከተማ

ማልቀሻ ሲታጣ

ሆስፒታሉ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ጠይቋል።

ቤተሰባቸው ግን አስከሬኑን ለማቃጠል ላወጡት ገንዘብ መንግሥት ካሳ እንዲከፍላቸው ጠይቀዋል።

ማሩሪ ቤታቸው ተመልሰዋል፤ ለመኖር ሁለተኛ እድል አግኝተው አዲስ ህይወት ጀምረዋል።

እንቅልፍ እንዲመቻቸውም በማለት ቤተሰባቸው አዲስ ፍራሽም ገዝቶላቸዋል።

ምንም እንኳን የማሩሪ ቤተሰቦች በህይወት መኖራቸውን ተረድተው እፎይታ ቢያገኙም ብዙዎች የቤተሰቦቻቸውንና የወዳጆቻቸውን አስከሬን ፍለጋ መባዘናቸውን ቀጥሏል።

ባለው ቀውስና ቫይረሱም ይዛመታል በሚለው ፍራቻ ብዙዎች ቤተሰቦቻቸውን ሳይሰናበቱ ነው ከዚች ዓለም በሞት የተለዩት። ሃዘኑስ እንዴት ይወጣላቸዋል?

ቤተሰቦቿን በኮሮናቫይረስ ያጣችው የሳሊና ትንሿ ልጅ ሁሉም ቤተሰብ ገንዘብ አዋጥቶ መቀበሪያ ቦታ አዘጋጅቶላቸው ነበር ትላለች።

"ነገር ግን አስከሬኑን ሳይሰጡን እንዴት እንቅበራቸው?" ብላም ትጠይቃለች።

"አባቴና እናቴ የት እንዳሉ አለማወቅ ልብ ይሰብራል። የት ሄጄስ ላልቅስ፣ ሃዘኔንስ የት ልወጣ?"በማለትም ሃዘን በሰበረው ድምጿ ትጠይቃለች።

ኮሮና
Banner