ኮሮናቫይረስ፡ስደተኞች የኮቪድ-19 ምርመራን በነፃ እንዲያገኙ የሚተጋው ኢትዮጵያዊ

የፎቶው ባለመብት, Dr Derara Timotiwos
አትላንታ ክላርክስተን በሚባል ስፍራ የኮቪድ-19 ምርመራ እና የሌሎች ህክምናዎችን በነፃ የሚሰጥ ክሊኒክ መዘጋጀቱን ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ደራራ ጢሞቲዎስ ለቢቢሲ ገለፁ።
ክሊኒኩ ኤትኔ የሚል ስም ያለው ሲሆን ማንኛውም በአትላንታ አካባቢ የሚኖርና የጤና መድን ዋስትና ያለውም ሆነ የሌለው ሰው መጥቶ አገልግሎቱን በነፃ ማግኘት ይችላል ሲሉ ያስረዳሉ።
ላለፉት 14 ዓመታት በአሜሪካ የኖሩት ዶ/ር ደራራ ጢሞቲዎስ፤ የአሜሪካ ዜግነታቸውን ያገኙት በቅርቡ ነው።
ከዚህ ቀደም በጆርጂያ ግዛት አትላንታ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው የክላርክስተን ከተማ የምክር ቤት አባል ለመሆን ተወዳድረው ነበር።
እንደ ዶ/ር ደራራ ገለፃ ክላርክስተን 13 ሺህ ሰዎች የሚኖሩበት ትንሽ ከተማ ብትሆንም አብዛኞቹ ነዋሪዎች ስደተኞች ናቸው፤ ከተማውም የሚታወቀውም በዚሁ ነው።
አብዛኞች ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን እና ከተለያዩ አገራት የመጡ ስደተኞች የሚሰሩት ስራ የታክሲ ሹፌር፣ ፋብሪካ እና ሌሎች ለቫይረሱ የሚያጋልጡ ስፍራዎች በመሆኑ መረዳዳት እንደሚያስፈልግ አቶ ደራራ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
"ማንኛውም በአትላንታ አካባቢ የሚኖርና ችግር ያለበት ሰው መጥቶ ሊያነጋግረን ይችላል።"
ኤትኔ ክሊኒክ እርሳቸው በቦርድ አባልነት የሚመሩት ሲሆን ከሌሎች ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት አትላንታ አካባቢ የኮሮናቫይረስ ምልክት የሚታይባቸውን ሰዎች በነፃ እንደሚመረምር ተናግረዋል።
የአትላንታ አካባቢ ነዋሪዎች ሲመረመሩ ኢንሹራንስ ባይኖራቸውም ችግር የለውም የሚሉት አቶ ደራራ፣ በአሁኑ ሰዓት በጣም በርካታ ሰዎች መጥተው አገልግሎቱን እያገኙ መሆኑን ገልፀዋል።
"አሜሪካ ውስጥ አንድ ሰው የጤና ኢንሹራንስ ከሌለው በጣም ይቸገራል። ይህ የአሜሪካ አስቀያሚ ገጽታ ነው። ለኮሮና ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ በሽታዎችም ጭምር"
አቶ ደራራ በቦርድ አባልነት የሚመሩት ክሊኒክ ግን የጤና መድህን ዋስትና የላችሁም ብሎ እንደማይመልስ ያስረዳሉ። ማንኛውም ሰው የኮሮና ምልክት ከታየበት፣ የጤና መታወክ ከገጠመው የክልኒካቸውን ደጃፍ ቢያንኳኳ ያለችግር እንደሚከፈትለት ይናገራሉ።
"ኢንሹራንስ ካለው ጥሩ ። ከሌለውም ችግር የለውም።"
የ40 ዓመቱ ዶ/ር ደራራ በዚህ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የምግብ እጥረት ለሚያጋጥማቸውና ለሚራቡ ሰዎች ደግሞ ኢንቪዥን አትላንታ ከሚባል ድርጅት ጋር በመሆን የምገባ አገልግሎት ላይ እየሰሩ መሆኑን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የምግብ ችግር ያጋጠመው ካለ እነርሱንም መርዳት እንችላለን ብለዋል።















