ከ68 ሺህ በላይ ጥንዶች በጳውሎስ ሆስፒታል የመካንነት ሕክምና እየተከታተሉ ነው

በቴክኖሎጂ በታገዘ ሕክምና የተወለደ ሕፃን

የፎቶው ባለመብት, St.Paul's Hospital

የምስሉ መግለጫ, በቴክኖሎጂ በታገዘ ሕክምና የተወለደ ሕፃን
    • ፀሐፊ, በፍሬህይወት ካሳ
    • የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ አማርኛ

በትዳር ውስጥ ከመካንነት ጋር በተያያዘ በርካታ አሳዛኝ ታሪኮች በየአካባቢያችን ይሰማሉ። ረጅሙን ታሪኳን በአጭሩ ያቀረብንላት ሴት ልጅ ፍለጋ ያስከፈላትን ዋጋ እንደሚከተለው አጫውታናለች . . .

"ሌላ እንዲያገባ ፈቀድኩለት. . . "

"ከምወደው አብሮ አደጌ ጋር ድል ባለ ሠርግ ወዳጅ ዘመድ መርቆን ትዳር መሠረትን። ደስተኞች ነበርን። ዓለማችን ጎጇችን ሆነ። በርካታ ዓመታትን አብረን አሳለፍን። ፍቅራችን በዙሪያችን ያሉትን ሁሉ የሚያስቀና ኑሯችንም የተሳካና የተደላደለ ነበር። ይሁን እንጂ ዓይናችንን በዓይናችን ማየት አልቻልንም። በመጀመሪያ አካባቢ የመደናገጥና ግራ የመጋባት ስሜት ውስጥ ገባን። በኋላ ላይ የተለያዩ ሕክምናዎችን ሞከርን። በእምነታችንም የዘወትር ፀሎታችን "በልጅ ባርከን" ሆነ። ሆኖም ሊሆን አልቻለም።

ፈልገነው የሆነ ይመስል ከቤተሰብና በዙሪያችን ካሉ ሰዎች "ውለዱ እንጅ" የሚለው ምክር የሰላምታ ያህል ተደጋገመ። መሸማቀቅ ጀመርን። ጫናው እንደሚወራው ቀላል አልነበረም። በዚህ ሁኔታ ዓመታትን ገፋን።

በጤና ምርመራው ችግሩ ያለው ከእኔ እንደሆነ ስረዳ ደግሞ እጄ በሌለበት ነገር የባሰ ጥፋተኝነት ይሰማኝ ያዘ። እሱ ግን እኔን ከማበረታታት ባለፈ ምንም ትንፍሽ አይልም። "ፈጣሪ የፈቀደው ነው የሚሆነው" ነበር የሚለኝ።

እኔ ግን "እኔን ብለህ ያለ ልጅ መቅረት የለብህም፤ ሌላ አግባና ውለድ" ስል ሃሳብ አቀረብኩለት፤ ከልቤ ነበር። ነገር ግን "የልጅነት ፍቅረኛዬን ለልጅ ብዬ ጥዬ ለመሄድ ህሊናዬ አይፈቅድልኝም" በማለት በሃሳቤ አልተስማማም። በመካከላችን ውዝግብ ተነሳ።

የኋላ ኋላ አግብቶ ልጅ እንዲወልድና ልጁን ይዞ ወደ እኔ እንዲመጣ አግባብቼው ተስማማ። እርሱም ሌላ አገባ። እኔም ብቻዬን እርሱን መጠባበቅ ጀመርኩ። ሁለት ዓመት ሳይሞላ የሴት ልጅ አባት ሆነ። ደስ አለኝ።

እርሱ ልቡ እኔ ጋ ነበርና ልጅቷ ልክ ከአራስ ቤት ስትወጣ "ካንች ጋር ይበቃናል፤ ልጄን ስጭኝና ልሂድ" የሚል ጥያቄ ያቀርብላታል ለእናትየው። እርሷም እናት ናትና "ከፈለክ አንተ ትሄዳለህ እንጂ፤ ልጄን እንዴትም ብዬ አሳድጋለሁ" የሚል መልስ እንደሰጠችው ነገረኝ። ይህንን እንዴት እንዳላሰብነው ይገርመኛል። ራስ ወዳዶች ሆነን ነበር። አንዱን በድሎ አንዱን ማስደሰት አይቻልምና ያሰብነው ሳይሆን ቀረ።

እርሱም ልጅ ነበርና ያሰደደው፤ እኔን ትቶ ከልጁ እናት ጋር ትዳሩን አፀና። አልፈርድበትም። እኔም ቤት ንብረታችንን ይዤ ብቻዬን ቀረሁ። የምወደውን ባሌን በልጅ ምክንያት አጣሁ . . . "

ግራጫ መስመር

ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ ይህንን የሥነ ተዋልዶ ጤና ችግር ለመፍታት የመካንነት ሕክምና ማዕከል አስመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ሚያዚያ 2011 ዓ. ም ነው።

አገልግሎት መስጠት በጀመረ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ከ60 ሺህ በላይ ጥንዶች የመካንነት ሕክምና እየተከታተሉ መሆናቸውን በሆስፒታሉ የሥነ ተዋልዶ ማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ቶማስ መኩሪያ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከእነዚህ መካከል 1400ዎቹ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመካንነት ሕክምና ለማግኘት ተመዝግበዋል። ቀሪዎቹ ደግሞ ወደዚህ ሕክምና ከመግባታቸው በፊት ሌሎች ሕክምናዎችን በመከታተል ሂደት ላይ ይገኛሉ።

እነዚህ ጥንዶች በተለያየ ኑሮና የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የመጡ ናቸው።

በቴክኖሎጂ በታገዘው በዚህ የመካንነት ሕክምና ከ70 በላይ እናቶች ነፍሰጡር ሆነው በተለያየ የእርግዝና ወራት ላይ ይገኛሉ።

6 ወላጆች ወልደው ስመዋል። 8 ልጆች ተወልደዋል። አንዲት እናት ሦስት የወለደች ሲሆን አንዱ ሞቶባታል፤ መንታዎቹ ግን በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

ጥንዶቹ ከ18 እስከ 4 ዓመታት በትዳር ውስጥ ቢቆዩም፤ ልጅ ሳያፈሩ ቆይተው አሁን ልጅ ያገኙ ናቸው።

"በዚህ መንገድ እናቶች ልጃቸውን ሲያቅፉ በደስታ ያለቅሳሉ። በጋብቻ መሃል ልጅ አላዩም ነበር። ልጅ ይናፍቁ ነበር። ልጅ ለማግኘት በዕምነት ቦታዎችና የባህል መድሃኒት ፍለጋ ሲንከራተቱ ነው የቆዩት። ከማኅበረሰቡ የሚደርስባቸው ጫናም ቀላል አልነበረም። ይህን ሁሉ አልፈው ልጅ ሲያቅፉ የተሰማቸው ሊቆጣጠሩት የማይችሉት የደስታ ስሜት ነው። በደስታ ሲፈነጥዙ ነው ያየነው" ይላሉ የሆስፒታሉ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ንዋይ ፀጋዬ።

ሕክምናው የሚሰጠው የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ባስተማራቸው የአገር ውስጥ የሕክምና ባለሙያዎች ነው። ይህ የሕክምና አገልግሎት መሰጠት ከመጀመሩ በፊት የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጉንም ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

ሕክምናውን ከሚሰጡ የባለሙያዎች ቡድን የተወሰኑ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Dr. Tomas Mekuria

የምስሉ መግለጫ, ሕክምናውን ከሚሰጡ የባለሙያዎች ቡድን የተወሰኑ አባላት

መካንነት ምንድን ነው?

ጥንዶች ለአንድ ዓመት የወሊድ መከላከያ ሳይጠቀሙ ቢያንስ በሳምንት ሁለት ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እየፈጸሙ ፅንስ መፈጠር ካልቻለ መካንነት እንደሚባል ዶ/ር ቶማስ ይናገራሉ።

የሴቷ ዕድሜ ደግሞ ከ35 ዓመት በላይ ከሆነ እና በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ያለ ወሊድ መከላከያ በሳምንት ሁለት ጊዜ እና ከዚያ በላይ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽመው እርግዝና መፈጠር ካልቻለ የመካንነት ችግር ሊኖር ይችላል ተብሎም ይታሰባል። ሳይለያዩ ለአንድ ዓመት የቆዩ ጥንዶች ያለምንም መከላከያ ግንኙነት እያደረጉ ማርገዝ ካልቻሉም እንዲሁ።

መካንነት በሴቶችና በወንዶች ላይ ሊከሰት ይችላል። በሴቶች ላይ ከዕድሜ ጋር ተያይዞም ሆነ ያለዕድሜ የዘር እንቁላል ማለቅ፣ የቱቦ መዘጋት እና በአባላዘር በሽታዎች በተደጋጋሚ መጠቃት እንዲሁም በሌሎች ችግሮች ሊከሰት ይችላል።

የችግሩ መንስዔ እንደ ግለሰቦቹ ስለሚለያይ መንስዔያቸውን በምርመራ በዝርዝር መረዳት እንደሚቻል ዶ/ር ቶማስ ያስረዳሉ።

አንዳንዴ ሁሉም ነገር ጤናማ ሆኖ እርግዝና ላይፈጠር ይችላል። ይህ የማይገለፅ መካንነት [Unexplained Infertility] ይባላል። ይህ ማለት ቴክኖሎጂ ያልደረሰባቸው ችግሮች አሉ ማለት ነው። 20 በመቶ የሚሆኑ ጥንዶችም ይህ ችግር የሚያጋጥማቸው ሲሆን በቴክኖሎጂ የታገዘ ሕክምና ሊደረግላቸው ይችላል።

መካንነት በተለይ አፍሪካ ውስጥ የተለመደ ችግር ነው የሚሉት ዶ/ር ቶማስ በተለይ በአባላዘር በሽታዎችና በሌሎች ኢንፌክሽኖች የመካንነት ችግር እንደተንሰራፋ ይናገራሉ።

ዶ/ር ቶማስ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርትን ጠቅሰው እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ከ15-20 በመቶ ጥንዶች የዚህ ችግር ተጠቂ ናቸው።

ሴቷም ሆነ ወንዱ በእኩል ደረጃ በመካንነት ሊጠቁ ይችላሉ፤ በመሆኑም በማኅበረሰቡ ሴቷ ላይ ብቻ ጣት የሚቀስረው በተሳሳተ አመለካከት መሆኑንም ዶ/ር ቶማስ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በአውሮፓዊያኑ 2016 የወጣው የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው በተለያዩ ምክንያቶች በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የውልደት መጠን እየቀነሰ መሆኑን ያመለክታል። በገጠር የሚኖሩ ሴቶች በ2000 ከነበረው 6.0 የውልደት መጠን በ2016 ወደ 5.2 ወርዷል።

በከተሞች ደግሞ በ2000 ከነበረው 3.0 በ2016 ወደ 2.3 ዝቅ ብሏል።

በአጠቃላይ አንዲት ሴት መውለድ ካለባት አማካይ የውልደት መጠን በ2000 ከነበረው 5.5 በ2016 ወደ 4.6 መቀነሱን የዳሰሳ ጥናቱ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና የጤና ዳሰሳ ጥናት

በቴክኖሎጂ የታገዘ የመካንነት ሕክምና [IVF] ምንድን ነው?

ዶ/ር ቶማስ እንደገለፁልን ይህ የሕክምና ዘዴ ከሴቷ እንቁላል ከወንዱ ደግሞ የዘረ ፈሳሽ በመውሰድ በቤተ ሙከራ እንዲገናኙ ተደርጎ ፅንስ ከተፈጠረ በኋላ ያ ፅንስ ተመልሶ ማህፀን ውስጥ ሲገባ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመካንነት ሕክምና [IVF] ይባላል።

ይህ ሕክምና እንደየ ሰዉ ቢለያይም ከ40-50 በመቶ ሊሳካ የሚችል ሂደት ነው።

እስካሁን ይህን አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ ከሄዱት ውስጥ 200 ለሚሆኑ ጥንዶች አገልግሎቱ ተሰጥቷል። ከእነዚህ መካከል 95ቱ ነፍሰጡር ሆነዋል።

መጀመሪያ አገልግሎቱን ካገኙት 8 ሴቶች 5ቱ ነፍሰ ጡር የነበሩ ሲሆን 3ቱ ወልደዋል። ሁለቱ ግን በመካከል ውርጃ አጋጥሟቸዋል። ይህም የሕክምናው ውጤታማነት ከ50 በመቶ በላይ መሆኑን ያሳያል።

ከተፈጥሯዊው መንገድ በምን ይለያል?

  • የሴቷ እንቁላል ከወንዱ የዘረ ፈሳሽ ጋር የሚገናኝበት ሂደት በቤተ ሙከራ መሆኑ
  • በቤተ ሙከራው ተፈጥሯዊውን ማህፀን በሚመስል ሁኔታ በተዘጋጀ 'ኢንኩቤተር' ፅንሱ ለአምስት ቀናት እንዲቆይ መደረጉ
  • ፅንሱ ወደ ማህፀን ተመልሶ ከገባ በኋላ ማህፀን ውስጥ እንዲያድግ መደረጉ።
  • ከተፈጥሯዊው በበለጠ አደጋዎች ሊኖሩት መቻላቸው
  • ከተለመደውና በተፈጥሯዊ እርግዝና ወቅት ከሚወሰዱት በተጨማሪ ሌሎች መድሃኒቶች ማስፈለጋቸው
  • ለጨቅላ ህፃናቱ በተፈጥሯዊ መንገድ ከተወለዱት ይልቅ ከፍተኛ ክትትል ማስፈለጉ
  • በተለይ የሴት ልጅ ዕድሜ ከ40 ዓመት በላይ ከሆነ የመሳካት ዕድሉ ይቀንሳል
  • አገልግሎቱን ለመስጠት የዕድሜ ገደብ ባይኖርም፤ ከ42 ዓመት በላይ ለሆኑ ሴቶች ሕክምናው ባይሰጥ ይመረጣል።

የእርግዝናው ወራቶች ግን ተመሳሳይ ሲሆን እንደ ሁኔታው አሊያም እንደ እናትየውና ፅንሱ የጤና ሁኔታ በቀዶ ሕክምናም ሆነ በምጥ ሊወልዱም ይችላሉ።

ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ይህንን በቴክኖሎጂ የታገዘ ሕክምና ሲሰጥ በአገር ውስጥ የመጀመሪያው የመንግሥት ተቋም ሲሆን አሊክማ የተሰኘ አንድ የግል ተቋም አገልግሎቱን ሲሰጥ መቆቱን ዶ/ር ቶማስ ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ምንም እንኳን ማኅበረሰቡ ከእምነትና ከባህል ጋር ጥብቅ ቁርኝት ቢኖረውም፤ ሰዎች አሁን አሁን ለመረጃ ቅርብ በመሆናቸው በቴክኖሎጂው ለመደገፍ ፈቃደኛ ናቸው።

ይሁን እንጂ በሌሎች አገራት እየተሠራበት ያለው እና ከጥንዶቹ ውጭ ከሌላ ሴት እንቁላል አሊያም ከሌላ ወንድ የዘረ ፈሳሽ ወስዶ፤ ልጅ ከተፈጠረ በኋላ እንደገና ወደ ማህፀን የመመለሱ ሕክምና የእንቁላል ወይም የዘር ፈሳሽ ልገሳ [Egg or Sperm donation] የተለመደ አይደለም።

አንዳንዴም ደግሞ የእናት ማህፀን ጽንስ መያዝ አልችል ሲል የማህፀን ኪራይ ይኖራል። እነዚህ ሕክምናዎች የሕግ ማዕቀፍ ስለሚያስፈልጋቸውና ግንዛቤ መፍጠር ስለሚያስፈልግ አሁን ላይ እየተሠራበት አለመሆኑን ዶ/ር ቶማስ ገልጸዋል።

ውጭ አገር በመሄድ በከፍተኛ ወጪ ሕክምናውን የሚያደርጉ እንዳሉ የገለጹት ዶ/ር ቶማስ፤ ለወደፊቱ ሕክምናውን ለመስጠት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንዲህ ዓይነቱን የሕክምና አገልግሎት ለመጀመር ግን ማኅበረሰቡ ላይ ግንዛቤ መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም አስምረውበታል።

"በማኅበረሰቡ ልጅ መውለድ፣ ቤተሰብ መመሥረት አንደ ሕይወት ግብ ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ፤ መካንነት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ያስከትላል" የሚሉት ዶ/ር ቶማስ፤ "በዚህ ቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩም ሆነ በሌላ መልኩ መፍትሔ ሲያገኙ ጥንዶች ደስተኛ ይሆናሉ" ይላሉ። ይህ የሕክምና አገልግሎት መጀመሩም መልካም ጅምር መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ቢሆንም ባለው የባለሞያና ተቋማዊ አቅም ውስንነት መድረስ የሚቻሉትን ጥንዶች ያህል መድረስ አለመቻሉንም አስረድተዋል። በአንድ ዓመት ከ1500 በላይ ለሆኑ ጥንዶች አገልግሎቱን መስጠት የሚያስችል አቅም የለም ብለዋል።

ዶ/ር ቶማስ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ68 ሺህ በላይ ጥንዶች ወደ አንድ ሆስፒታል ብቻ መምጣቱ የሚያስደነግጥ ቁጥር መሆኑን በመግለጽ ቀጠሮዬ ረዘመ የሚሉ ቅሬታዎችን የሚያቀርቡ ሰዎች በርካቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል።