የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝ ደቡብ አፍሪካውያን እናቶች ያለእውቅናቸው እንዲመክኑ ተደርገዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝባቸው በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን እናቶች ለመውለድ ባቀኑበት የጤና ተቋም ከእውቅናቸው ውጪ ወይም ተገደው ዳግም እንዳይወልዱ እንዲመክኑ መደረጋቸውን መንግሥት ያደረገው ምረመራ አጋለጠ።
በበርካታ የመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሃኪሞች ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ እናቶች የሚያረግዙ ከሆነ የሚወለደውን ልጅ ህይወት አደጋ ላይ ይጥላሉ በማለት "እናቶችን በማስገደድ ሰብዓዊ ባልሆነ መንገድ መካን እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል" ተብሏል።
የደቡብ አፍሪካ የጾታ እኩልነት ኮሚሽን ላለፉት አምስት ዓመታት የ48 እናቶችን ጉዳይ ሲመረምር ቆይቷል።
ኮሚሽኑ ባደረገው ምረመራ እናቶቹ በሙሉ ቀዶ ህክምና ለመውለድ ወደ የመንግሥት ሆስፒታሎች ከሄዱ በኋላ፤ ሃኪሞች ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ እናቶች ማርገዝ እንደሌለባቸው እና የሚያረግዙ ከሆነ ደግሞ የሚወለደውን ልጅ ህይወቱ እንዲያልፍ እያደረጉ እንደሆነ እንደተነገራቸው ተረጋግጧል።
"የተወሰኑት እናቶች ደግሞ ላለመውለድ በፊርማቸው እንዲያረጋግጡ የተደረጉት በምጥ ህመም ላይ ሳሉ እንደሆነ እና ፍቃደኛነታቸውን ያልገለጹ እናቶች ደግሞ በቅጾቹ ላይ ፊርማቸውን ካላኖሩ የህክምና እርዳታ እንደማይደረግላቸው ተነግሯቸዋል"
ኮሚሽኑ ጨምሮ ከሆስፒታሎቹ የወላድ እናቶች ዶሴዎች እንዲሰወሩ ስለተደረጉ የጀመረውን ምረመራ አጥጋቢ በሆነ መልኩ መጨረስ አልቻልኩም ብሏል።
የደቡብ አፍሪካ የጤና ሚንስቴር ከጾታ እኩልነት ኮሚሽን ጋር አስቸኳይ ስብሰባ ለማድረግ ቀጠሮ መያዙን ሬውተርስ ዘግቧል።









