ኮሮናቫይረስ፡ "በኮሮናቫይረስ አጎቴን አጥቻለሁ፤ አሁን ደግሞ እኔ ተይዣለሁ" ሃና ገብረሥላሴ፡

ሃና

የፎቶው ባለመብት, HANA

ሃና ጆይ ገብረሥላሴ የተወለደችው በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ደቡባዊ ግዛት ነው። ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አትላንታ ያቀናችው የአራት ዓመት ልጅ ሳለች ነበር።

ሃና ጋዜጠኛ ናት። የቴሌቪዥን ሪፖርተር ሆና ሠርታለች። ነገር ግን ከአንድ ዓመት ከግማሽ በፊት የራሷን መንገድ መከተል መረጠች። ከቴሌቪዥን ሪፖርተርነት ራሷን ካገለለች ወዲህ በኅብረተሰብ አገልግሎት ሥራ ላይ ተሰማርታ ትገኛለች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጥቁር አሜሪካውያን ላይ የሚደርሰውን ጭቆና በመቃወም የመብት ተሟጋችነት መድረክን ተቀላቅላለች። ከዚያም አልፎ ለእናትና ለአባቷ አገራት ኢትዮጵያና ኤርትራ የተለያዩ የእርዳታ ሥራዎችን እንደምትሰራ ትናገራለች። በአሁኑ ወቅት በዩትዩብና ፌስቡክ ገፆቿ ሥራዎቿን ታስተዋውቃለች።

ሃና ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኮሮናቫይረስ የቅርብ ዘመዷን እንዳጣች በትዊተር ገጿ ላይ አስፍራ ነበር። ከዚህም አልፎ እሷም ተመርምራ ኮቪድ-19 እንዳለባት ማወቋን በይፋ በመናገር ሌሎች በእሷ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ በተደጋጋሚ መክራለች።

ለመሆኑ ሃና ኮሮናቫይረስ እንዴት ሊያገኛት ቻለ?

የበሽታውምልክት

የበሽታው ምልክት የጀመረኝ ሰኔ 23 [ጁን 30] ገደማ ነው። ከዚያ በፊት ባሉት ሳምንታት የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ስሳተፍ ነበር። ነገር ግን በዚህ ወቅት ምንም ዓይነት የቫይረሱ ምልክት አልታየብኝም። ሁሌም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እጠቀም ነበር። ሳኒታይዘርም ይዤ ነበር የምንቀሳቀሰው።

ምልክቱ መጀመሪያ ሲጀምረኝ መካከለኛ የሚባል ነበር። ከዚያ ግን ወዲያው በጣም እየከፋ መጣ። የመጀመሪያው ምልክት ራስ ምታት ነበር። በጣም ከባድ ራስ ምታት። ከዚያ ያቅለሸልሸኝ ጀመር። ጥርሴን ለመፋቅ ብሩሽ ስጠቀም ይሁን አሊያም ምግብ ልመገብ ስል ወደላይ ይለኛል ግን አያስመልሰኝም። ይህ ሁሉ ስሜት የተሰማኝ በአንድ ሌሊት ነው።

ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት የተለያዩ ስሜቶችን አስተናግጃለሁ። ሌላኛው ስሜት ደግሞ መፍዘዝ ነበር፤ በጣም ይደክመኝም ነበር። የምግብ ፍላጎቴም እጅጉን ቀንሶ ነበር። አስታውሳለሁ ቁጭ ብዬ ምግብ እየላሁ ከትንሽ ጉርሻ በኋላ የምግቡ ጣዕም እየጠፋብኝ መጣ።

ከእነዚህ ሁሉ ምልክቶች ግን የከፋ የነበረው ድንገት ሌሊት ላይ የጀመረኝ ምልክት ነው። ይህም የትንፋሽ ማጠር ነው። በጣም ያስደነገጠኝ እሱ ነበር።

ይህን ጊዜ ነው ወደ ሕክምና ተቋም ሄጄ የተመረመርኩት።

ከዚያ በፊት ግን የተለያዩ ተቃውሞዎች ላይ ተሳትፌ ስለነበር ምልክቱ ባይኖረኝም ጥቂት ጊዜያት ተመርምሬ ነበር። በዚህኛው ዙር ግን ከተመርመርኩ በኋላ ራሴን አግልዬ ተቀመጥኩ። ይህንን ያደረግኩት ከሰኔ 24 ጀምሮ ነው።

ሃና

የፎቶው ባለመብት, HANA

ውጤትጥበቃ

ከተመረመርኩ በኋላ ያለው ጊዜ በጣም አስጨናቂ ነበር። በተለይ ውጤቱ መጠበቅ እጅግ ግራ አጋቢ ስሜት ነበረው። ምንም እንኳ በሽታው እንደሚኖርብኝ ብጠረጥርም፤ ቢኖርብኝስ የሚል ጥያቄ ሃሳብ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ከየት ይሆን ያገኘሁት? ለሰው አስተላልፌውስ ቢሆን? አለብሽ ከተባልኩ ምን እሆናለሁ? ብቻ የተለያዩ ሃሳቦች ወደ አእምሮዬ ይመጡ ነበር።

የበሽታው ምልክት ሳይታይብኝ የተመረመርኩ ጊዜ ውጤት የመጣልኝ ወዲያው ነበር። ነገር ግን በሁለተኛው ዙር ይመስለኛል ከአምስት ቀናት በኋላ ነው ውጤቴን የሰማሁት።

በጆርጂያ ግዛት ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ውጤት ይፋ የሚሆንበት ቀንም እየጨመረ መጥቶ ነበር።

በስተመጨረሻ የተመረመርኩ ጊዜ ውጤቴን በፅሑፍ መልዕክት የነገሩኝ ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ነው። ደውለው ውጤትሽ 'ፖዘቲቭ' ነው እና ራስሽይን አግልይ አሉኝ። እንግዲህ ይሄ የሆነው እኔ ራሴን አግልዬ ከቆየሁ በኋላ ነው።

ቫይረሱ ሊይዘኝ ይችላል ብለሽ አስበሽ ታውቂያለሽ? ብባል፤ መልሴ "አዎ" ነው። ምክንያቱም በየትኛውም ጊዜ ከቤቴ ከወጣሁ ሊይዘኝ እንደሚችል አስባለሁ።

እንዲያውም ወረርሽኙ የገባ ሰሞን ለሦስት ሳምንታት ያክል ከቤቴ ንቅንቅ አላልኩም። በዚያ ላይ ደግሞ ኤፕሪል [ሚያዚያ] ላይ ቺካጎ የሚኖር አጎታችን በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወቱ አለፈ። ይሄ ቫይረሱ የምር እንደሆነ፤ ወዳጅ ዘመድ እንደሚነጥቅ አሳውቆኝ ስለነበር ሁሌም እጠነቀቃለሁ።

እኔን ቢይዘኝ ለቤተሰቦቼ አስተላልፋለሁ የሚለው ነገር ያስጨንቀኝ ስለነበር በጣም እጠነቀቃለሁ። ቢሆንም ውጤቴ 'ፖዘቲቭ' ሆኖ ሲመጣ በጣም ደንግጬ እንደነበር አስታውሳለሁ።

'ኮሮናቫይረስየምርነው'

በቅርቡ የሆነ ሰው 'የምር ግን ኮቪድ-19 ነው የያዘሽ?' ሲል ጠየቀኝ። ሌላ ሰው ደግሞ ምንም እንኳ አንድ ዘመድ በበሽታው ቢያጣም ቫይረሱ ገዳይ እንደሆነ ሊያምን አልፈለገም። ይህ የብዙ ሰዎች እይታ ነው። ነገር ግን በሽታው የምር ነው።

እኔ የቅርብ ዘመዴን አጥቻለሁ። እኔም በቫይረሱ ተይዣለሁ። ለዚህ ነው የምር ነው የምለው። ወጣቶች በሽታው አይዛቸውም ወይም ምልክቱን አያሳዩም የሚል ፅንሰ-ሐሳብ አለ። ነገር ግን አኔ ወጣቶች እንደሚያዙ ምስክር ነኝ።

እርግጥ ነው እኔ በርካታ ተቃውሞዎች ላይ ስሳተፍ ነበር። ምንም እንኳ ጥንቃቄ ለማድረግ ብሞክርም ፍፁም አይደለሁም። በእኔ ዕድሜ ያሉ ሰዎች ላይያዙ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን ምልክቱን ሳያሳዩ ለሌሎች ሊያስተላልፉ ይችላሉ። የእኔ ትልቁ ፍራቻዬ የነበረው ለእናቴ እንዳላስተላልፍ ነበር።

ስለዚህ ወጣቶች ተጨማሪ የጤና እክል ላለባቸው ሰዎች ሊያስተላልፉ ስለሚችሉ መጠንቀቅ የግድ ነው። ሌላው ቢቀር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንጠቀም፤ ሰላም ስንባባል ንክኪ አይኑረን። እየተሳሳሙ ሰላምታ መለዋወጥ ኢትዮጵያና ኤርትራ ውስጥ የተለመደ እንደሆነ አውቃለሁ። ነገር ግን ይሄ ሊቆም ይገባል።

ሃና

የፎቶው ባለመብት, HANA

'አዲስሕይወት'

ወረርሽኙ የሰዎችን የአኗኗር ዘይቤ እጅጉን ቀይሯል። ኮቪድ-19 እንዳለበት ሰው በእኔም ሕይወት ላይ ብዙ ለውጦች አምጥቷል ብዬ አስባለሁ። በጣም ብናፍቃቸው እንኳ ቤተሰቦቼን ማየት አልችልም። አብሬያቸው እንኳን ቢሆንም ያለሁት እኔ በመኖሪያ ቤቱ ሌላ አቅጣጫ ነው ስለሆነ አንተያይም።

ወደ መኝታዬ ሳመራ እፈራለሁ። አንዳንዴ ባልነቃስ ብዬ እፈራለሁ። ምክንያቱም አንዳንዴ ጊዜ ትንፋሽ አጥሮኝ ድንገት የምነቃባቸው ሌሊቶች ነበሩ። ሁሌም ወደ መኝታ ከማምራቴ በፊት ጠዋት እንድነቃ እፀልያለሁ።

ሌላኛው ፍርሃቴ እናቴ ቢይዛትስ? አባቴ ቢይዘውስ? ወይም ሌላ የቤተሰብ አባል ቢይዘስ? የሚለው ነው። ቤተሰባችን ሐይማኖተኛ ነው። እናቴ ሁሌም ፀበል እንድጠጣ ታደርገኛለች።

ምንም እንኳ ቫይረሱ ቢፈትነኝም ብቻዬን አይደለሁም የሚለው እውነታ ይታደገኛል። በዚያ ላይ ሚሊዮኖች ተይዘው ድነዋል። ከቤተሰቦቼ ጋር ቁጭ ብዬ መቼ ነው ምግብ የምቋደሰው? የሚለውን ባላውቅም ሁሉም እንደሚያልፍ አምናለሁ። እስከዚያው ግን ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ይሁንና በዚያ በኩል እየተገናኘን ነው።

ሃና

የፎቶው ባለመብት, HANA

ምግብናእንቅስቃሴ

አሁን ላይ በጣም እየተሻለኝ ነው። መካከለኛ የሚባሉት ስሜቶች ከሞላ ጎደል ጠፍተዋል። ማሳልና ሌሎች ምልክቶችን በተለያዩ መድኃኒቶች መቋቋም ችያለሁ።

ከበሽታው ከባዱ ነገር የትንፋሽ እጥረት ነው። እሱን ደግሞ የትንፋሽ ስፖርት በመሥራት እያሻሻልኩት ነው። ለምሳሌ ሆዴ [በደረት] እንድተኛ ተመክሬ እሱን በማድረጌ በጣም ለውጥ አይቻለሁ። ከዚያም አልፎ ትንፋሽን እያመቁ መልቀቅም ረድቶኛል።

ያልጠጣሁት ዓይነት ጭማቂ [ጁስ] የለም ማለት ይቻላል። በተለይ ደግሞ የብርቱካን ጭማቂ። እንዲሁም በርካታ ቫይታሚኖች ወስጃለሁ። ፈሳሽ ነገር፤ በተለይ ውሃ እንዲሁም ረዘም ያለ እረፍት ማድረግ ይመከራሉ፤ እኔንም እጅጉን አግዘውኛል።

የእናቴ ሙያም የሚረሳ አይደለም። ከአገር ቤት የመጡ ቅመማ ቅመሞችን በመደባለቅ ትኩስ ነገር ትሠራልኛለች። እሱም በጣም አግዞኛል። ከዚያ ባሻገር ከቤታችን ጓሮ ወጣ ብዬ እንቅስቃሴ አደርጋለሁ።

አሁን ተመርምሬ ውጤቴን እየጠበቅኩ እገኛለሁ። በዚህኛው ዙሪያ እንኳ ምንም ዓይነት ፍርሃት የለብኝም። ውጤቱ 'ኔጌቲቭ' ሆኖ ከመጣ እፎይ ብዬ ድጋሚ እንዳይዘኝ መጠንቀቅ ነው የምፈልገው። ለሁለተኛ ጊዜ የያዛቸው ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ። እንደውም ሁለተኛው ዙር ህመሙ የባሰ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ።

ለዚህም ነው በቻልኩት መጠን አገር ቤት ላሉ ሰዎች በጣም ተጠንቀቁ ማለት የምፈልገው። ምናልባት አስፈላጊው አቅርቦት ላይኖር ይችላል ግን ባለው ነገር ራስን መከላከል ይበጃል። በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት የምናደርገው ጥንቃቄ መፃዒ ዕድላችንን ሊወስን ይችላል።

እዚህ አሜሪካ መጀመሪያ አንድ ሰው ነው የተያዘው። ከዚያ በኋላ ይኸው ብዙዎችን አጥተናል። ሁሉም ነገር ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ ነገር ግን እያንዳንዷ ጥንቃቄ ዋጋ አላት።

ውጤት

ሃና ጆይ ገብረሥላሴ ከቢቢሲ ጋር ይህንን ቃለ-ምልልስ ካደረገች በኋላ የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤቷ ኔጌቲቭ መሆኑንና ከበሽታው ማገገሟን ነግራናለች። እንኳን ደስ ያለሽ !