ማኅበረሰቡ ከኮቪድ-19 ራሱን ከመጠበቅ ተዘናግቷል፡ የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎች

የጤና በለሙያ

የፎቶው ባለመብት, AMANUEL SILESHI

ማኅበረሰቡ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ እንዳልሆነና ከጊዜ ወደ ጊዜ ቸልተኝነት እየጨመረ መምጣቱን የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከሦስት ቀናት በፊት በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 704 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ከተገለጸ በኋላ፤ የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ማኅበረሰቡ እራሱንና ቤተሰቡን ከወረርሽኙ ለመከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በትዊተር ገጻቸው አሳስበዋል።

ኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ሪፖርት በተደረገበት ወቅት፤ በሕዝቡ ዘንድ አሁን ካለው በተሻለ ሁኔታ ጥንቃቄዎች ይደረጉ እንደነበረ በርካቶች ይስማማሉ።

አካላዊ ርቀት ይጠበቅ ነበር፤ ሰዎች ወደ ንግድ እና የመንግሥት ተቋማት ከመግባታቸው በፊት እጃቸውን እንዲታጠቡ ይገደዱም ነበር።

አሁን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ በመጣበት ወቅት የበርካቶች መዘናጋት እስጨናቂ መሆኑን የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነዋሪዎች ምን ይላሉ?

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዋ አስቴር ቶላ “ሰዉ ተዘናግቷል፤ መጀመሪያ አካባቢ ጥንቃቄ ይደረግ ነበር። አሁን ግን እንዲያም ሰው እየተላመደው መጥቷል ማለት ይቻላል” ትላለች።

ሰው እየተዘናጋ መምጣቱን ያስተዋለችው አስቴር፤ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ብቻ ከመግለጽ ይልቅ፤ ህሙማንን በቴሌቭዥን ማቅረብ ሰው ለበሽታው ትኩረት እንዲሰጥ ያግዛል ብላ ታምናለች።

“ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አድርገው በቴሌቭዥን ቢታዩ፣ ታመው የተኙ ሰዎችም ቢታዩ ጥሩ ነው። ሰው ከቁጥር ይልቅ ሁኔታውን በአይኑ ማየት ያሳምነዋል” ስትልም ታስረዳለች

ሌላው የአዲስ አበባ ነዋሪ አክሊሉ ዓለማየሁም የአስቴርን ሀሳብ ይጋራል። “ዳቦ ቤት፣ አውቶብስ ላይ፣ ቀበሌ ስኳር ስንገዛም ተቃቅፈን ነው” ይላል።

በርካቶች አካላዊ ርቀት መጠበቅን እየዘነጉ መሆኑን ይናገራል። ቀድሞ እጅ መታጠቢያ በየመንገዱ እንዲሁም በምግብ ቤቶች መግቢያ ላይ ይቀመጥ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ግን ውሃና ሳሙና ማስቀመጥ መቅረቱን አክሊሉ ታዝቧል።

የምዕራብ ሃረርጌ ነዋሪው አቶ አፈንዲ መሐመድ በሐረር እና አከባቢዋ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ሕዝቡ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር እየተገበረ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

"ከአንድ ወር ወዲህ 'መንግሥት ኮሮናቫይረስን የፖለቲካ አጀንዳ አድርጎታል' የሚል አመለካከት በመምጣቱ ሕዝቡ ከዚህ ቀደም ያደርግ የነበረውን ጥንቃቄ ትቶታል" ይላሉ።

አቶ አፈንዲ እንደሚሉት፤ አሁን ላይ ሰዎች ሰላምታ ሲለዋወጡ እጅ መጨባበት ጀምረዋል። ይህ ልማድ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ቀንሶ ነበር።

የአምቦ ከተማ ነዋሪው አቶ መረራ ፋና፤ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ባለበት ወቅት በሕብረተሰቡ ዘንድ የጥንቃቄ እርምጃዎች እየላሉ መምጣታቸው አሳሳቢ እንደሆነ ይናገራሉ።

"የትራንስፖርት ዋጋ በእጥፍ ቢጭምርም በአንድ መኪና የሚጫነው ቁጥር አልቀነሰም። የሚቆጣጠር ሰው የለም። የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የወጣው አዋጅ አምቦ ከተማ ላይ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ እየሆነ አይደለም ማለት ይቻላል" ይላሉ።

የቢቢሲ ሪፖርተር በአደማ፣ በዱከም እና በቢሾፍቱ ከተሞችም በተመሳሳይ ሁኔታ የጥንቃቄ ጉድለቶች መኖራቸውን ታዝቧል።

በአዳማ ከተማ በቡድን ሆኖ መዝናናት፣ መጠጥ መጠጣት እና በስጋ ቤቶች ጥሬ ስጋ መመገብ በስፋት ይታያል።

በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 11 ሺህ 933 ደርሷል። 197 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።

ኮሮና
Banner