ቻይና በቼንግዱ የሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ እንዲዘጋ አዘዘች

በቻይና የሚገኘው የአሜሪካ ቆንስላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ በሂውስተን የሚገኘውን የቻይና ቆንስላ እንዲዘጋ ውሳኔ ማስተላለፏን ተከትሎ፤ ቻይናም በተመሳሳይ ሁኔታ በቼንግዱ ከተማ የሚገኘውን የአሜሪካ ቆንስላ እንዲዘጋ አዛለች።

ከሁለት ቀናት በፊት አሜሪካ የቻይናን ቆንስላ ለመዝጋት መወሰኗን ይፋ ስታደርግ፤ ቤጂንግ የአሜሪካ ውሳኔ “ፖለቲካዊ ፍላጎት የታየበት” ነው ብላለች።

የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ቆንስላውን ለመዝጋት የወሰንኩት “የአሜሪካን አዕምሯዊ ንብረት ለመጠበቅ ሲባል ነው” ማለቱ ይታወሳል።

አሜሪካ ቆንስላው እንዲዘጋ ስለመወሰኗ የተነገረው፤ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች በቆንስላው ቅጥር ግቢ ውስጥ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ ወረቀት ሲያቃጥሉ መታየታቸውን ተከትሎ ነው።

በወቅቱ የቻይና የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን አሜሪካ ቆንስላው እንዲዘጋ መወሰኗ “እጅጉን የሚያስቆጣ ነው፤ ለውሳኔው ትክክለኛነት መከራከሪያ ማቅረብ እንኳ አያስችልም” ካሉ በኋላ ቻይና የመልስ መት እንደምትሰጥ ተናግረው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ቻይና የአሜሪካን ቆንስላ ለመዝጋት ወስናለች።

የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከቤጂንግ መንግሥት ጋር በንግድ፣ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና በሆንግ ኮንግ ጉዳዮች በተደጋጋሚ ሲነታረክ ይስተዋላል።

በቅርቡ ድግሞ ቻይና የኮቪድ-19 ክትባት ምርምር የሚያካሂዱ ቤተ ሙከራዎች ላይ ስለላ እያደረገች ነው ሲል የአሜሪካ የፍትህ ተቋም ከሷል።

በኮሮናቫይረስ ላይ የሚደረግ ምርምርን ሰልለዋል የተባሉ ሁለት ቻይናውያን ላይም ክስ ተመስርቷል።

በክሱ ላይ በስም የተጠቀሱት ሁለት ግለሰቦች በአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ስላላ ሲያካሂዱ፤ የቻይና መንግሥት የደህንነት ተቋም ድርጋፍ አድርጎላቸዋል ተብሏል።ቻይና በበኩሏ አሜሪካ ከመሰል ተግባሯ እንድትቆጠብ ጠይቃለች።