አሜሪካ በቴክሳስ ሂዩስተን የሚገኘውን የቻይና ቆንስላ እንዲዘጋ አዘዘች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ በቴክሳስ ግዛት ሂውስተን ከተማ የሚገኘው የቻይና ቆንስላ እስከ ዓብር ድረስ እንዲዘጋ አዘዘች።
ቤጂንግ የአሜሪካ ውሳኔ “ፖለቲካዊ ፍላጎት የታየበት” ነው ብላለች።
የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ከዚህ ውሳኔ የተደረሰው “የአሜሪካን አዕምሯዊ ንብረት ለመጠበቅ ሲባል ነው” ብሏል።
የቻይና የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን በበኩላቸው አሜሪካ ቆንስላው እንዲዘጋ መወሰኗ “እጅጉን የሚያስቆጣ ነው፤ ለውሳኔው ትክክለኛነት መከራከሪያ ማቅረብ እንኳ አያስችልም” ብለዋል።
አሜሪካ ቆንስላው እንዲዘጋ ስለመወሰኗ የተነገረው፤ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች በቆንስላው ቅጥር ግቢ ውስጥ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ ወረቀት ሲያቃጥሉ መታየታቸውን ተከትሎ ነው።
በአሜሪካ እና ቻይና መካከል ያለው ውጥረት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያየለ መጥቷል።
የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከቤጂንግ መንግሥት ጋር በንግድ፣ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና በሆንግ ኮንግ ጉዳዮች በተደጋጋሚ ሲነታረክ ይስተዋላል።
ትናንት ድግሞ ቻይና የኮቪድ-19 ክትባት ምርምር የሚያካሂዱ ቤተ ሙከራዎች ላይ ስለላ እያደረገች ነው ሲል የአሜሪካ የፍትህ ተቋም ከሷል።
በኮሮናቫይረስ ላይ የሚደረግ ምርምርን ሰልለዋል የተባሉ ሁለት ቻይናውያን ላይም ክስ መስርቷል።
በክሱ ላይ በስም የተጠቀሱት ሁለት ግለሰቦች በአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ስላላ ሲያካሂዱ፤ የቻይና መንግሥት የደህንነት ተቋም ድርጋፍ አድርጎላቸዋል ተብሏል።
ቻይና በበኩሏ አሜሪካ ከመሰል ተግባሯ እንድትቆጠብ የጠየቀች ሲሆን፤ “ይህ ሳይሆን ቀርቶ አሜሪካ በዚህ መንገድ መቀጠልን የምትሻ ከሆነ፤ ቻይና ጠንካራ ምላሽ ትሰጣለች” ብላለች።












